ፈልግ

የጥላቻ ንግግር የጥላቻ ንግግር 

“የጥላቻ ንግግር”

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መዝገበ-ቃላትን እና የጥላቻ ንግግርን በማስመልከት በተለያዩ ጊዜያት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያስተላለፉት መልዕክቶችን በመጥቀስ፣ የሥነ-ትምህርት መምህርት ሚሌና ሳንቴሪኒ፣ ስለ ጥላቻ ንግግር ወይም “hate speech” የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጥላቻ ወይም የጥላቻ ስሜት ከጥንት ጀምሮ፣ ከቃየል እና ከአቤል ዘመን ጀምሮ በሰው ልጆች መካከል ሲገለጽ የቆየ ቢሆንም ዛሬ ግን የጥላቻ ንግግር አዲስ መልክ ይዞ ይገኛል። ጠላትነት ወይም የጥላቻ ንግግር በአንድ ግለሰብ ወይም በቡድን ላይ፣ ብዙ ጊዜ ደግሞ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ በቁጥር ዝቅተኛ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ሊፈጸም ይችላል። ስለዚህ ከዘረኝነት፣ ከጭፍን ጥላቻ፣ ከፀረ-ሴማዊነት፣ ከአድልዎ እና ከአንዳንድ መሰል ርዕሠ ጉዳዮች ጋር በመዛመድ ሕዝባዊ ገጽታ በመያዝ፣ በሌላ ላይ ጉዳትን ለማድረስ ከሚመነጭ ፍላጎት ጋር ሁከትን ከሚቀሰቅስ ጭብጥ ጋር የተያያዘ ነው። የጥላቻ ንግግር ጎጂነት የተረጋገጠ ቢሆንም ሁልጊዜ እንደ ወንጀል መቆጠር የለበትም። ምክንያቱም ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ ከሚያስችል መብት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስላለው። ነገር ግን የጥላቻ ንግግር የሰውን ክብር የሚሸረሽር እና ማኅበራዊ አብሮነትን የሚጎዱ በመሆኑ ጎጂነቱ መካድ የለበትም።

የጥላቻ ንግግር በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ዘንድ ተስማሚ እና ምቹ ሥፍራን ያገኘ ይመስላል። በቀላሉ በመሰራጨቱ፣ በፍጥነት መጓዙ፣ በድንገተኛነቱ እና የተናጋሪውን ማንነት በመደበቅ የተነሳበእርግጥ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችን አደገኛ የሚያደርጉ ልዩ ባህሪያት አሉ። ድረ-ገጽ ወይም “Internet” በዘመናችን የተለመደ የመገናኛ ዘዴ ብቻ ሳይሆን የግጭት እና የጥቃት ቦታ ስለመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ፣ ለችግሩ ትኩረት በመስጠት ይገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም የጥላቻ ንግግርን በማስመልከት የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው እ. አ. አ. በ2016 ዓ. ም.  ባስተላለፉት መልዕክት ክርስቲያናዊ ንግግር ኅብረትን እና አንድነትን የሚያሳድግ መሆን እንዳለበት፣ (50ኛው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀን መልዕክታቸው) ገልጸው፣ በይነ-መረብ ዓለምን ለማየት የሚያስችል መስኮት ከማድረግ ይልቅ ግለኝነትን የሚያሳድግ የጭፍን ጥላቻ መድረግ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል (የቅዱስነታቸው የ53ኛ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀን መልዕክት)። ጥፋትን ለሚያስከትሉ ንግግሮች እና የውሸት መረጃዎች ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ እና አብሮነትን የሚያሳድጉ ንግግሮችን መናገር እንዳለብን አሳስበዋል (የቅዱስነታቸው የ54ኛ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀን መልዕክት)።

ከሁሉም በላይ "ሁላችንም ወንድማማቾች ነን" በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ፣ የጥላቻ ንግግር በማኅበረሰቦች መካከል ብቸኝነትን እና አመጽን እንደሚያስከትል ተብራርቷል። አሁን ያለው የዲጂታል ሚዲያ ግንኙነት እና የመረጃ ልውውጥ፣ ሰላማዊ ያልሆኑ የሻከሩ ግንኙነቶችን በማስፋፋት ላይ ይገኛል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህ እንዳይሆን፣ የሚከፋፍል ምናባዊ የመገናኛ መንገድ ከመከተል ይልቅ ሌላ የመገናኛ ዘዴን እንደ አማራጭ አቅርበዋል። የሰውን ልጅ እውነተኛ የእርስ በእርስ ግንኙነት ባህሪን የተከተለ፣ የመልካም አቀባበል ምሳሌ የሚገለጽበትን መንገድ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

12 Apr 2022, 18:24