ፈልግ

በግብጽ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓል በተከበረ ዕለት በግብጽ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓል በተከበረ ዕለት  

የግብጽ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳዊ ሂደት ወደፊት መጓዟ ተገለጸ

በግብጽ-አሌሳንድሪያ፣ የኮፕት ሥርዓት አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ባኩም ሐኒ ኪሩሎስ፣ በሮም የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የጠራውን ስብሰባ መሳተፋቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያስጀመሩት ሲኖዶሳዊ ሂደት በተለያዩ የግብጽ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ኪሩሎስ፣ በጋራ መነጋገር እና መደማመጥ ትርጉም ለመረዳት ለብዙ ወራት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በግብጽ በሚገኙት ካቶሊካዊት ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ከተደረጉ የግል እና ማኅበራዊ ለውጥ ተነስተው እርስ በእርስ በመደማመጥ፣ አብሮ በመኖር እና በማስተንተን ሲኖዶሳዊ ጉዞ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን፣ በቅርብ ቀናት በሮም በተዘጋጀው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ላይ የተሳተፉት በግብጽ አሌክሳንደሪያ የኮፕት ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኪሩሎስ ገልጸዋል። ባሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ካቶሊካዊ ምዕመናን በመንፈስ ቅዱስ በመመራት እርስ በእርስ በመደማመጥ እና በጋራ በማስተንተን ላይ መሆናቸው ይታወቃል። የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ባዋቀራቸው አራት ምክር ቤቶች እነርሱም የነገረ-መለኮታዊ፣ የመንፈሳዊነት፣ የስልት እና ማኅበራዊ መገናኛ ጽሕፈት ቤት አባላት፣ የሲኖዶሱን የጋራ ሰነድ በጋራ ለማጥናት መሰብሰባቸው ታውቋል። 

ሃሳብን መጋራት እና ጸሎት

አምስት ቀናትን በወሰደው የስብሰባ ቀናት ውስጥ ተሳታፊዎቹ እስካሁን በተካሄደው የሲኖዶስ ጉዞ ወቅት በተነሱ ቁልፍ ነጥቦች ላይ በመወያየት በጸሎት መተባበራቸው ታውቋል። የጋራ ውይይቱን እና የጸሎት ሥነ ሥርዓቱን የተካፈሉት ብጹዕ አቡነ ኪሩሎስ ከቫቲካን ዜና እገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ አምስቱ የውይይት እና የጸሎት ቀናት ፍሬያማ እንደ ነበሩ ገልጸው፣ ለሲኖዶሱ ሂደት ጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ ርዕሠ ጉዳዮች፣ በተለይም እምነትን በሚመለከት፣ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን እና የቤተ ክርስቲያን ተዋረድ በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች፣ በተጨማሪም ስለ ወንጌል አገልግሎት እና ተልእኮ በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን አስረድተዋል።

አብሮ መሥራት

በተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ያሉ ሥራዎች የሚገኙበትን ደረጃ በተመለከተ መወያየታቸውን የተናገሩት ብጹዕ አቡነ ኪሩሎስ፣ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ኮሚሽኑ ባካሄዳቸው ተግባራት እና በደረሰበት ደረጃ ላይ በመወያየት መጠናከር ያለባቸው ነጥቦችን፣ በምን ላይ ተባብረው መሥራት እንደሚያስፈልግ እና አንዳንድ ጉዳዮችን ለመፍታት በሚያግዙ የመፍትሄ መንገዶች ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል። "ሁሉም ሰው የራሱን ሥራ መሥራት ብቻ ሳይሆን አብሮ የመሥራት አስፈላጊነት መመልከታቸውን አስታውሰው፣ የሲኖዶሳዊ ጉዞ ዋና ዓላማም መተባበር፣ በኅብረት መወያየት፣ ማሰብ እና መደማመጥ እንደሆነ አስረድተዋል።

የሲኖዶስ ቅድመ ዝግጅት

ግብጽ በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሱ ሂደት በሁለት መንገዶች እየተካሄደ እንደሆነ ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ኪሩሎስ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በተከናወኑ ሥራዎች መደሰታቸውን ገልጸው፣ ባለፉት ወራት የተካሄደው፣ ማለትም የመጀመሪያው እርምጃ፣ በግብጽ የኮፕት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ኮሚሽን መፍጠር እንደሆነ አስረድተዋል። በየሀገረ ስብከቱ ሁለት የኮሚሽኑ አባላት መሰየማቸውን ገልጸው፣ የሲኖዶሱ ሰነዶች ወደ አረብኛ ቋንቋ መተርጎሙ፣ እንዲሁም ሌሎች የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናትም በራሳቸው ቋንቋ ማዘጋጀት ጠቃሚ መሆኑን ተመልክተናል ብለው፣ ይህም ጭብጦችን እና ፅንሰ-ሀሳቦችን የበለጠ ለመረዳት ያግዛል ብለዋል።

የተሰጡ መልሶች

በተለያዩ ሀገረ ስብከቶች በመጀመሪያ ዙር በተደረጉ የሲኖዶሱ መንፈሳዊ ዝግጅት ወቅት ከአምስት እስከ ስድስት የሚደርሱ ሀገረ ስብከቶችን እንደጎበኙ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ኪሩሎስ፣ በሁለተኛው ምዕራፍ፣ ከብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ለማሰባሰብ ስብሰባዎች መካሄዳቸውን አስታውሰዋል።

የዩክሬን ጦርነት በሲኖዶሳዊ ሂደት ያመጣው ፈተና

በዩክሬን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ጦርነቶች ከቅርብ ወራት ወዲህ በሲኖዶሳዊ ሂደት ላይ ተጽዕኖን ማሳደሩን ብጹዕ አቡነ ኪሩሎስ ገልጸው፣ እነዚህ ጦርነቶች በሰው ልጆች ላይ አደጋን የሚያስከትሉ፣ ከሲኖዶሳዊነት ጋር የሚጋጩ ፈተናዎች እንደሆኑ፣ የሲኖዶሳዊ ጉዞ ዓላማ አንድነትን ለማምጣት ሲሆን፣ ጦርነቱ በሕዝቦች መካከል መከፋፈልን የሚያመጣ በመሆኑ፣ ይህ እንዳሆን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ መጸለያቸውን እንደሚቀጥሉ፣ በግብጽ-አሌሳንድሪያ፣ የኮፕት ሥርዓት አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ባኩም ሐኒ ኪሩሎስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።  

30 April 2022, 17:02