ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ የኢትየጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ የኢትየጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት 

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ  ለ2014 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ያስተላለፉት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።  

 "እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ" (ዮሐ 11፡25)  

 ብፁዓን ጳጳሳት   

ክቡራን ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት   

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ምዕመናንና ሕዝበ እግዚአብሔር    

  ከሁሉ በፊት ለመላ ኢትዮጲያውያንና ትውልደ ኢትዮጲያዊያን ክርስቲያን ወገኖች በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የ2014 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።    

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የክርስቲያናዊ እምነታችን  መሠረት ዋናው ምሰሶ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለን “ክርስቶስ ከሙታን ባይነሣ ኖር እምነታችን ከንቱ በሆነ ነበር። ከሁሉ በላይ ሊታዘንልን የምንገባ ሰዎች ነበርን፣ ነገር ግን እምነታችን ኃይላችንና ተስፋችን የሆነልን ክርስቶስ ከሙታን ስለተነሳ ነው።"    

(1 ቆሮ 15፥14-15) ለሰው ልጅ ሞት ከባድ አሉታዊ ሃይል ነው። እንደዚሁም ሞት አስፈሪ የማይለመድ የሚከብድ ነገር ነው። ሆኖም እነዚህን ነገሮች የክርስቶስ ትንሣኤ በሌላ መንገድ እንድንመለከተው አደረገ፤ የሚያስፈራውን ነገር ክርስቶስ በሞት ጥላ ውስጥ በማለፍ ሊጋፈጡት የሚችሉት ነገር እንደሆነ አሳየ። የማይለመደውን ሞት ሰዎች በሌላ ዓይን እንዲመለከቱ የክርስቶስ ትንሣኤ አዲስ ምዕራፍ ከፈተ በክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት ሰዎች ሲሞቱ በክርስቶስ አረፉ እንላለን። በክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት ፃድቃን ሲሞቱ ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ተሻገሩ እንላለን። በክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት ሰማዕታት ሲሞቱ ለአዲስ ሕይወት ተወለዱ እንላለን።    

ስለሙታን ትንሣኤ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የምናገኘው እንደ አዲስ ኪዳን ብዙ አይደለም። ለዕብራዊያን ትልቁ ይፈራ የነበረው ነገር ከማህኅበረሰቡ መገለል ነበር። ሆኖም የትንሣኤን ምስጢር የሚያመለክቱ ብዙ መልዕክቶችንም ማስተዋል እንችላለን። አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር መልእክት ይልቅ የእባቢቱን አሳሳች ሃሳብ ተቀብለው ከእግዚአብሔር ቢሸሹም አምላክ አልተዋቸውም። ከገነት ቢወጡም በኋላም ተስፋ መስጠቱ፣ ልብስ ማልበሱ ትልቅ መልእክት  ያዘለ ነው።  ሞትን  የሚያመጣውንም ፍሬ ቢበሉም እግዚአብሔር ለሕይወታቸው ለመዳናቸው መቆሙ የትንሣኤ ትንቢት ነው ለማለት ይቻላል።    

አቤል በሞተ ጊዜ የአቤል ደም ወደ እግዚአብሔር መጮሁ  ትልቅ ትርጉም አለው። በዚህም ለሰው ልጅ ሞት የመጨረሻ ቃል ሊሆን እንደማይችል ይጠቁማል። ዘመናትን የሚያቋርጠው የንፁህ ተበዳይ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የሚያስተላልፈው ኃይለኛ መልእክት እንዳለ ያሳያል። ከዚህም የተነሳ ክቡር የሆው የሰው ልጅ ሕይወት በሞት ሊያቆም እንደማይችል ያሳያል። በተለይም የንፁህ ሰው ደም ትልቅ ቦታ እንዳለው ያመለክታል። ስለሆነም የክርስቶስ ትንሣኤ የአቤልንና እንደ አቤል የተበደሉትን የሰው ልጆችን ጥያቄ በሙሉ ይመልሳል።    

በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ የኖኅ ቅድመ አያት የነበረው ከአዳምም ሰባተኛ የነበረው ሔኖክ ከዚህ ምድር ወደ መላዕክት ዓለም እንደተወሰደ ተገልጿል። እግዚአብሔር ሄኖክና ኢልያስ ሞትን ሳያዩ ወደ ራሱ ምጡቅ ዓለም ወሰዳቸው። ይህም ሕይወት አሁን በምናያት ምድራዊ ዓለም ብቻ እንደማትወሰን ያመለክታል።    

እግዚአብሔር ለኖኅ የገባለት ቃል ኪዳን የጥፋትንና የሞትን አደጋ የሚከላከል፣ ለፍጥረታት ሁሉ የትንሣኤን ተስፋ የሚያመለክት ነው። እንዲሁም የኖኅ መርከብ የሰው ልጅን ከጥፋት እንዳዳነች ሁሉ የክርስቶስ መስቀልና ትንሣኤም የተጠመቁትን ከሞትና ከኃጢአት ያድናል።    

ፃድቁ ኢዮብ በፈለገው ሁኔታ ውስጥም እንኳ ቢሆን እግዚአብሔር እንደሚታደገው ተስፋ ያደርግ ነበር። ኢዮብ ይህንን ተስፋ የሚገልጸው እጅግ በሚከብድ ኀዘን ውስጥ ሆኖ ነው። ማንም የሚረዳው ሰው ባልነበረበት ወቅት ነው። ወዳጆቹም በማይገባው መልኩ ፈጣሪን አሳዝነሃል እያሉ በወቀሱበት ጊዜ ልጆቹን፣ ጤናውን፣ ክብሩንና ሃብቱን ላጣ ሰው የወዳጆቹ መፅናኛ በጠቀመው ነበር። ነገር ግን ይልቁንም ቁስሉ ይበልጥ እንዲያመረቅዝ የሚያደርግ ውትወታ ከወዳጆቹ በኩል ደረሰበት። ኢዮብ ያንን ያህል መከራ ለምን እንደሚቀበል አልገባውም ነበር። የመከራውን ምክንያት አለመረዳቱ ራሱ ሌላ ትልቅ ቁምነገር ነው። ምክንያቱም ሰይጣን ይጠብቀው የነበረው ኢዮብ እግዚአብሔርን እንዲሰድብ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ኢዮብ ሕማሙን አልደበቀም እያመመውም አላመመኝም አላለም፤  ያልተረዳውን ተረድቻለው አላለም። የኢዮብ ሰቆቃውን መግለጽ እግዚአብሔርን አላስቆጣውም። እንዲያውም እግዚአብሔር የኢዮብን ግልጽነት መረጠ ስለ እግዚአብሔር መልካም የሚናገሩ የሚመሰሉት የኢዮብ ወዳጆች ግን ተወቀሱ።  ምክንያቱም በኢዮብ ላይ ፈርደውበት ነበርና። መሰቃየቱን ሃጢያቱ ውጤት አድርገው ተርጉመውት ነበርና። ዳሩ ግን ኢዮብ ፃድቅ እንደነበረ እግዚአብሔር እራሱ መስክሮ ነበር። በታሪኩ መጨረሻም ኢዮብ እንደሚገባው እግዚአብሔርን እንደማያውቀው ተማረ። በመጨረሻ የተገለፀለት የእግዚአብሔር መልእክት ስለ ሕይወት ምስጢር ብዙ የማያውቀው እንዳለ አሳየው። ኢዮብ በትሕትና ተሞላ። የሕይወትንም ሆነ የሞትን ምስጢር፣ የመልካምንና የክፋትን ሚስጢር በሙላት እንደሚረዳ ተገነዘበ። በዚያን ጊዜም ለትንሣኤ ትንቢት የሚሆን ጉዳይ በኢዮብ ሕይወት ውስጥ ተከሠተ። እግዚአብሔር አዲስ ሕይወትን ሰጠው። ያጣውን ከበፊቱ በበለጠ መንገድ አገኘ።    

የኢዮብ ሕይወት የትንሣኤ ተምሳሌት ሆነ። ኢዮብ ንፁህ ሰው ሊሰቃይ እንደሚችል በማሳየት ሊመጣ የነበረውን የክርስቶስ የፃድቅ ሰው ሰቃይ አመለከተ። በሞት ሸለቆም ያለፈው ክርስቶስ ሞትን ድል በማድረጉ የሞት ምስጢር ተቀየረ፤ ሞት ተሸነፈ።   

በክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት እኛ  ሁላችንም አዲስ ፍጥረት ስለምንሆን በእምነትና በተስፋ የመጨረሻውን በረከት ለመቀበል ከአሁኑ መትጋት ይኖርብናል። በዕብራውያን በተጻፈው መልእክት ላይ እንኳን እንደ ደመና የከበቡን ሰማዕታትና ቅዱሳን የድል አክሊልን የሚቀዳጁት በክርስቶስ ትንሣኤ መሆኑን ያበሥራል። ስለሆነም የክርስቶስ ትንሣኤ የግለሰብም የማኅበረሰብም ትንሣኤ ነውና።  

 የተወደዳችሁ ምዕመናን፤ 

 የክርቶስ ትንሣኤ በዛሬ የግልና የማኅበረሰብ ሕይወታችን ምን መልእክትና ኃይል ይዞ ይመጣልናል? የክርስቶስ ትንሣኤ ለእያንዳንዱ ክርስቲያንና የሰው ልጅ መጥፎ ነገርን ክፋትንና ኃጢአትን ያሸንፍ ዘንድ ኃይል ይሰጠዋል።    

ዛሬ ጥላቻን በፍቅር፣ ቂም በቀልን በይቅርታ፣ ሐዘንን በደስታ፣ ቅራኔን በሰላም፣ ተስፋ መቁረጥን በጽናትና በክርስቲያናዊ ተስፋ ማሸነፍ የምንችለው በክርስቶስ መስቀል ነው፡፡ ”ገብረ ሰላም በመስቀሉ”፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ የሰላሙ ንጉሥ ጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ብቻ ሊሰጠው የሚችለውን እውነተኛ ሰላም ለአገራችን ኢትዮጵያ እንዲሰጣት  ለምኑ ብለው አውጀዋል፡፡  ስለዚህ በፊታችን ዓርብ ስቅለት ዕለት የምናደርገውን ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ንስሐ፣ ተጋድሎና ለቅሶ ለምንወዳት አገራችን ኢትዮጵያ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሥር በማኖር ምሕረቱን፣ እርቁን፣ ሰላሙን እንዲያወርድልን መላው ካቶሊካውያን እንዲማፀኑ አደራ እንላለን፡፡ በቃ ይበልን! ሕዝቡ ተጨነቀ፣ ተሰቃየ! ኪርያላይሶን! ኪርያላይሶን! እግዚኦ መሐረን ክርስቶስ! ብለን በመስገድ ምሕረቱን እንማፀን፡፡  

ክርስቶስ የትንሣኤ ኃይልና ጸጋ ነው። ክርስቶስ በትንሣኤው ኃጢአትንና ሞትን አሸንፎ በእኛ ሕይወትም ውስጥ የግል ሃጢያቶችን የጥላቻን፣ የመለያየትን፣ የትዕቢትንና የክፋትን መንፈስ ማሸነፍ የምንችለው ከሞት በተነሳውና ባሸነፊው ኢየሱስ ክርሰቶስ ኃይል ነው።    

ሰላማችንና ዕርቃችን የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአገራችን ውስጥ ሰላሙን ያውርድልንና እርቁን ያመጣልን ዘንድ በጸሎት እንትጋ። በጦርነት በድርቅ ለተፈናቀሉ ለተጎዱ ወገኖቻችን ሁሉ የክርስቶስ የትንሣኤ በረከት የመፅናናት ምልክት የሚያስፈልጋቸው ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው ከሞት በተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንለምናለን። እንዲሁም በጦርነትና በሰብአዊ ቀውስ የሞቱትን ሰዎች ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ በመንግስቱ ይቀበላቸው፤ ያዘኑትንም ያጽናናልን። ይህን የትንሣኤ በዓል  ስናከብር ሁላችንም በምንችለው አቅም ችግረኞችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉትን፣ ከስደት ተመላሾችን፣ ሕመምተኞችን በመርዳት፣ በማገዝና በማጽናናት ስቃይ ሀዘናቸውንና ችግራቸውን አብረን በመካፈል በዓሉንና ከበዓሉ በኋላ ያሉትን ጊዜያቶች በጎ ምግባር በመፈፀም እንድናከብረውና እንድንፈፅመው አደራ ማለት እወዳለሁ።    

በመጨረሻም ለመላው የአገራችን ሕዝቦች በሙሉ በየቤታችሁና በሆስፒታሎች ለምትገኙ ህሙማን ሁሉ ምሕረትን፣ በየማረሚያ ቤት ለምትገኙ የህግ ታራሚዎች መፈታትን፣ በስደት ላይ ያላችሁ ወደ አገራችሁና ወደ ቀያችሁ መመለስን፣ በጦርነትና በግጭት ቀጠናዎች መካከል ላላችሁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሰላምን እየተመኘሁ ለሁላችሁም ክርስቲያን ወገኖች በድጋሚ እንኳን ለመድኃኒችን ለኢየሱስ ክርስቶስ  የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን እገልጽላችሃለሁ።    

እግዚአብሔር አምላካችን አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክልን፤ ይጠብቅልንም።    

ክርስቶስ በትንሣኤው ሰላሙን ይስጠን ! 

† ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል    

ሊቀጳጳሳት ዘካቶለካውያን   

የኢትዮጲያ ካቶሊካት ቤተክርስቲያን    

ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚደንት  

   

ይህንን ዝግጅት በድምጽ መስማት ከፈለጉ ተጫወት የሚለውን ቁልፍ ይጫኑ

 

 

23 April 2022, 11:12