ፈልግ

በሮም ከተማ በመገኝ የሳሲያ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ የመለኮታዊ ምሕረት ቅዱስ ምስል በሮም ከተማ በመገኝ የሳሲያ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ የመለኮታዊ ምሕረት ቅዱስ ምስል  

መለኮታዊ ምሕረት ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ ነው!

ክፋት የተቆጣጠረው በሚመስል በዚህ አስቸጋሪ ዘመን ምሕረት ያስፈልገናል። እግዚአብሔር በርኅራሄ እንዲመለከተን እንፈልጋለን። ቤተ ክርስቲያን የመለኮታዊ ምሕረት በዓልን በምታከብርበት ቀን፣ የእግዚአብሔርን መልክ በአዲስ ዓይን በቁርጠኝነት ትመለከተዋለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የመለኮታዊ ምሕረት በዓል መከበር የጀመረው፣ እ. አ. አ. በ1931 ዓ. ም. የኢየሱስ ክርስቶስ ራዕይ የተገለጠላት የእህት ፋውስቲና ቅድስና ይፋ በሆነበት እ. አ. አ. በ2000 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳዎሎስ ዳግማዊ ካስጀመሩበት ጀምሮ ነው። ርዕስሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በዕለቱ ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው፣ ከፋሲካ እሑድ በኋላ የሚውለው እሑድ፣ የመለኮታዊ ምሕረት በዓል የሚከበርበት ዕለት እንዲሆን መወሰናቸው ይታወሳል። 

ከምዕመናን ጋር ያለው ጥልቅ ግንኙነት

የመለኮታዊ ምሕረት በዓል ከፋሲካ በዓል ጋር በቅርበት መከበሩ በአጋጣሚ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር የማዳን እቅድ እንዲፈጸም እና በሰዎች ልብ ውስጥ የድነት ምስጢር ዘልቆ እንዲገባ ዕድል የሚሰጥ ነው። ምሕረት ተጨማሪ የእግዚአብሔር ስጦታ ሲሆን፣ በምድራዊ ሕይወትም ጥበቃን የማግኘት ተስፋ የሚሰጥ ነው። በአማኞች ቤት ውስጥ የመሃሪውን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል ከተለመዱት እና ከሚታወቁት ምስሎች መካከል አንዱ ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ መገለጥ

እህት ፋውስቲና በማስታወሻ ደብተሯ ባሰፈረችው ጽሑፍ እንዲህ በማለት ገልጻለች፡- አመሻሹ ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነጭ ልብስ ለብሶ እኔ ክፍል ውስጥ ቆሞ አየሁት። አንድ እጁን ለቡራኬ ወደ ላይ ሲያነሳ፣ በሌላኛው እጁ በደረቱ ላይ ያለውን መጎናጸፊያ ሲነካ ተመለከትኩ። ሁለት ትላልቅ ጨረሮች፣ አንዱ ቀይ ሌላው ወደ ሰማያዊ ቀለም የቀረበ ነበር። ዓይኖቼን በጌታ ላይ አደረግሁ፤ ነፍሴም በፍርሃት ተሞላች፤ ነገር ግን ደግሞ በታላቅ ደስታም ተሞልታ ነበር። ከትንሽ ጊዜ ቆይታ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለኝ፡- "በምታየው ምሳሌ መሠረት ስዕል ሳዪ፥ ኢየሱስ ሆይ፥ በአንተ ታምኛለሁ! ይህ ምስል በመጀመሪያ በቤተ መቅደስ፣ ከዚያም በዓለም ሁሉ እንዲከበር እፈልጋለሁ። ይህንን ምስል የምታከብር ነፍስ አትጠፋም፤ እኔም በዚህ ምድር ላይ ቃል እገባለሁ፤ በተለይ በሞት ሰዓት ​​በጠላቶች ላይ ድልን እቀዳጃለሁ።"

የመለኮታዊ ምሕረት ቅዱስ ሥዕሎች

የመጀመሪያው ምስል የተሳለው ኢዩጂኒየስ ካዚሚሮቭስክ በተባለ ሠዓሊ ነበር። እህት ፋውስቲና በምስሉ ላይ የሚደረጉ እርማቶችን ለመጠቆምና ዝርዝር ነገሮችን ለመጨመር ወደ ሠዓሊው ዘንድ ሄደች። የስዕል ሥራው አልቆ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕይታ የተቀመጠው፣ እ. አ. አ በሚያዝያ ወር 1935 ዓ. ም. በሊቱዌኒያ አገር በቪልኒየስ ከተማ ውስጥ በሚገኘ የ "አውስሮስ ቫርቱ" ጸሎት ቤት መስኮት ላይ ነበር። በጊዜው በአካባቢው በነበረው የኮሚኒስት አገዛዝ በኩል ጥቃት እንዳይደርስበት ተሰግቶ ቅዱስ ምስሉ ለብዙ ዓመታት ያህል ተደብቆ እንዲቆይ ተደረገ። ይህ ቅዱስ ምስል ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ምስል በታማኝነት እንዲሳል የጠየቀበት የመጀመሪያ እና ብቸኛ ጊዜ ነበር። ስለ ግርማው ወይም ስለ ውበቱ እውነተኛ ይዘት እና ቅርጽ ለመስጠት በነበረው ፍላጎት ሳይሆን እርሱ ራሱ በራዕው ወቅት የተናገረው የጸጋ ስጦታ ይፈጸም ዘንድ ነበር።

ለሰው ልጆች በሙሉ እንደ መያዣነት በማቅረብ፣ ከምሕረት ምንጭ ጸጋዎችን ማግኘት እንዲችል፣ “ኢየሱስ ሆይ! በአንተ ታምኛለሁ” የሚል ጽሑፍ ያለበት ምስል ነው። ነገር ግን፣ የቪልኒየስ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጊንታራስ ሊናስ ግሩሻስ እንዳሉት፣ የቪልኒየስ መሐሪ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ በተገንዘብት ጨርቅ ላይ ካለው ምስል ጋር ፍጹም ተቀራራቢነት ያለው ነበር። ከአሥር ዓመታት በኋላ፣ እ. አ. አ በ1943 ዓ. ም. በአዶልፍ ሃይላ የተሳለው ሁለተኛው ምስልና በክራኮቪያ በሚገኘው የመለኮታዊ ምሕረት ቤተ መቅደስ ውስጥ የተቀመጠ ነበር። ይህ ምስል በቀድሞ ስማቸው ካሮል ዎይቲላ በመባል የሚታወቁት፣ በኋላም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ወደ ፋብሪካ ውስጥ ሥራ ከመሄዳቸው በፊት ጸሎታቸውን የሚያቀርቡበት ምስል ነው። ሁለቱ ሥራዎች በአካላዊ ባህሪያት ተመሳሳይ የላቸውም። በአቀማመጣቸው ግን ተመሳሳይ ናቸው።

ከልብ የሚመነጩ የብርሃን ጨረሮች

እህት ፋውስቲና በማስታወሻ ደብተሯ እንደፃፈችው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ እጁ ሲባርክ፣ ሌላኛውን እጅ ደግሞ ልቡ በሚገኝበት በኩል ደረቱ ላይ ማስቀመጡን ይጠቁማል። ከልቡ ሁለት የብርሃን ጨረሮች፣ አንዱ ነጭ እና ሌላኛው ቀይ የብርሃን ጨረሮች ሲፈነጥቁ ይታያል። እህት ፋውስቲና ይህን በማስታወሻ ደብተሯ ቁጥር 299 ላይ እንዲህ በማለት ጽፋዋለች፥ 

በምስሉ ላይ የሚታዩ ሁለቱ ጨረሮች ደም እና ውሃን ያመለክታሉ። ፈዘዝ ያለው ሰማያዊ ጨረር ነፍሳትን የሚያጸድቅ ውሃን የሚወክል ሲሆን፣ ቀይ ጨረር የነፍሳት ሕይወት የሆነውን ደም ይወክላል። ሁለቱም ጨረሮች ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ፣ ልቡ በሥቃይ በነበረበት ጊዜ በጦር ሲወጋ፣ "በጻድቅ የእግዚአብሔር እጅ ጥላ ሥር የሚኖር የተባረከ ነው” የሚል ነው። መሐሪ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ደምና ውኃ የፈሰሰበት የጎን ቁስሉን ይጠቅሳል (ዮሐ. 19፡31-34)። በውኃ እና በደም የመጣው ይህ ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃው ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን በውኃ እና በደም ነው። የሚመሰክረውም መንፈሱ ነው፥ መንፈሱ እውነት ነውና። መንፈስ፣ ውኃና ደም አንድ ናቸው። (1ኛ ዮሐንስ ምዕ. 5: 6,8)

ምሕረት ምንድን ነው?

ምሕረት የሚለው ቃል በላቲን ሥርወ-ቃል፣ “miserere” ወይም የልብን ርኅራኄ የሚያመለክት ቃል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 138 ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በብሉይ ኪዳን ውስጥ 97 ጊዜ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥም 41 ጊዜ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። መሐሪ ኃይሉን በሙላት የሚገልጥ የእግዚአብሔር እጅግ አስፈላጊ ባሕርይ ነው። ምሕረት የእግዚአብሔር መሐሪ ኃይሉ በሙላት የሚገለጥበት እጅግ አስፈላጊ ባሕርይ ነው። ለሰው ልጅ በሙሉ ከተሰጠው ፍቅር ጋር አይገናኝም። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚያድናቸው ለእነዚያ ሰዎች ያለውን ስሜት ያመለክታል። የእግዚአብሔርን ምሕረት ጠፍቶ ከተገኘው ልጅ ምሳሌ ሙሉ በሙሉ መረዳት ይቻላል (ሉቃ. 15:11-32)። አባቱ፣ ጠፍቶ የተገኘ ልጁን ወሰን በሌለው ርኅራሄ ተቀብሎታል። በእውነተኛ ንስሐ ወደ አባት ዘንድ በፈቃድ መመለስ በቂ ነው። እህት በፋውስቲና በማስታወሻ ደብተሯ ውስጥ፡- “ኃጢአተኛው ወደ እኔ ለመቅረብ መፍራት የለበትም።” በማለት የጻፈችውን እናገኛለን።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ እ. አ. አ በ2002 የምሕረት ዓመት በፖላንድ ክራኮቪያ “መለኮታዊ ምሕረት” በሚል አርዕስት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ በመለኮታዊ ምህረት ዓለምን ለመቀደስ ባቀረቡት ጸሎት፥

መሐር አምላካችን ሆይ! ፍቅርህን በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ገልጠህልናል። አጽናኙን መንፈስ ቅዱስህንም በእኛ ላይ አፈሰስክ። ዓለምን እና እያንዳንዱን ሰው ለአንተ በአደራ እንሰጥሃለን። ፊትህን ወደ እኛ ወደ ኃጢአተኞች መልስ፤ ክፋትን እንድናሸንፍ ድክመታችንን ፈውስ፣ በምድር የሚኖሩት በሙሉ ያንተን ምሕረት ቀምሰው እንዲያዩ፣ የቅዱስ ሥላሴ አምላክ ከሆንከው አንተ ተስፋን እንዲያገኝ ሁል ጊዜ ዕርዳቸው። ዘለዓለማዊ አባት ሆይ! በልጅህ ሕማማት እና ትንሣኤ፣ ለኛ እና ለዓለም በሙሉ ምሕረትን እንድታደርግልን እንለምንሃለን!

25 April 2022, 17:53