ፈልግ

ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር በቫቲካን በተገናኙበት ወቅት ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር በቫቲካን በተገናኙበት ወቅት  

ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በድርድር በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንደሚያመጣ ተስፋ አድርጋለሁ አሉ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፊኤል ከቫቲካን ዜና ጋር በሚያዝያ 6/2014 ዓ.ም ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በእርስ በርስ ጦርነትና በረሃብ እየተሰቃየ ባለው ሕዝብ ላይ ስላጋጠመው ሰብዓዊ ቀውስ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፊኤል ቤተክርስቲያናቸው “የተጀመረው ድርድር ዘላቂ ሰላም ያመጣ” ዘንድ ጽሎቷ እንደ ሆነ ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፊኤል ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ አገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነትና በረሃብ እየተሰቃየችበት ስላለው ቀውስ አስረድተዋል።

ድርድር በመካሄድ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለሰላም ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ሁኔታው በመጠኑ  ​​መሻሻሉን ብፁዕ ካርዲናሉ ቢያምኑም፣ የሰብአዊ ቀውሱ አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚፈልግ አክለው ገልጸዋል።

በህወሓት እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ  የመከላከያ ሰራዊት መካከል በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት እና በክልሉ ረሃብ በመከሰቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሞተዋል። ውጥረቱ የብሄር ብሄረሰቦችን ግጭት በማባባስ ክልላዊ መንግስታት ትግራይ፣ አማራ እና አፋር በከፋ ደረጃ ተጠቃሽ ሆነዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

ፋሲካ 'የቤተሰብ በዓል ነው'

በአሁኑ ወቅት በዐብይ ጾም ወቅት የሚገኙት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እ.አ.አ በሚያዝያ 24/2022 ዓ.ም የትንሳኤ በዓልን ሲያከብሩ፣ ምእመናን ለቅዱሱ ለሕማማት ሳምንት አምልኮ እንዴት እየተዘጋጁ እንዳሉ ብጽዕነታቸው ተናግረዋል።  

የትንሣኤን በዓል ቀድመው በመመልከት፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ የመስቀልን መንገድ እየጸለየ፣ እየጾመ፣ በቤተሰባቸውም ውስጥ ፋሲካን በጋራ ለማክበር እየተዘጋጁ እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን ምክንያቱም “ፋሲካ የቤተሰብ በዓል ነው” በማለት ያስታውሰናል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስለሰላም ግንባታ እና የጦርነትን አስከፊነት በተመለከተ በቅርቡ ባደረጉት ጥሪ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፊኤል ኢትዮጵያን በተለይ አስታውሰዋል ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በ2021 ዓ.ም የገና በዓል በተከበረበት ወቅት በላትን ቋንቋ “Urbi et Orbi” (ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም) በተሰኘው መልእክታቸው “የሕዝቦችን ፍላጎት ከምንም በላይ በሚያስቀድም ግልጽ በሆነ ግንኙነት ኢትዮጵያ እንደገና የእርቅና የሰላም መንገድ እንድታገኝ ጌታ ይርዳት” በማለት መጸለያቸውን አስታውሰዋል።

እ.አ.አ በየካቲት 27/2022 ዓ.ም በቫቲካን የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበትን ጸሎት ካደረጉ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዓለም "የተረሱ ጦርነቶችን" እንዲያስታውስ ማሳሰባቸው ይታወሳል።  በዩክሬን እየሆነ ያለው ነገር ልባቸውን እንደ ሰበረ በመግለጽ “በሌሎች የዓለም ክፍሎች እንደ የመን፣ በሶሪያ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ጦርነቶችን እንዳንረሳው... — እደግመዋለሁ፡ ሁሉንም የጦር መሳሪያዎች ጸጥ ይበሉ! እግዚአብሔር ሰላምን ከሚያስፍኑ ሰዎች ጋር ነው ያለው እንጂ ሁከት ከሚፈጥሩ ሰዎች ጋር ግን አይደልም ማለታቸው ይታወሳል።

ጥያቄ፡- የተከበሩ ካርዲናል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጦርነት ላይ ብዙ አቤቱታዎችን አቅርበዋል በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ሀገርዎ ጸልየዋል። የጳጳሱ ጥሪ ምን ያህል ዋጋ አለው?

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ለዚህ ጥያቄ ሲመልሱ “ትልቅ ዋጋ አለው” በማለት ነበር የጀመሩት። ቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እዚህ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግጭቶች እና የውስጥ ጦርነቶች ስላስታወሱ እናመሰግናለን። ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ስላሳሰባቸው እና ለጸሎታቸው በጣም እናመሰግናለን።

ጥያቄ፡ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?

በአሁኑ ጊዜ ቢያንስ ከጥቂት ወራት በፊት እንደነበረው ጦርነትም ሆነ ግጭት በእዚያው መጠን እየተካሄደ አይደለም። አሁን ትንሽ የተሻለ ነው ምክንያቱም በፌዴራል መንግስት እና በክልሉ መንግስት ወይም በፖለቲካ ባለስልጣናት መካከል ድርድር እንደቀጠለ ስለተነገረን ነው። ከሁሉም በላይ በአብዛኛው ግጭቱ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የተንጠለጠለ ነው። ይህ እየተካሄደ ያለው ድርድር ዘላቂ ሰላም ያመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። አሁን ያለው ሁኔታ ይህ ነው። ሆኖም ጦርነቶች እና ግጭቶች በሚከሰቱበት ጊዜ ብዙ የሚሰቃየው ህዝቡ ነው። ተራው ህዝብ ብዙ ስቃይ ሲደርስበት የቆየው ባብዛኛው በትግራይ ክልል ቢሆንም ከትግራይ ጀምሮ ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች እንደ አማራ ክልል እና አፋር ክልል ዘልቋል። በነዚህ የመፈናቀል፣ የረሃብ እና የውድመት አካባቢዎች ሰዎች አሁንም እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ትምህርት ቤቶች፣ የጤና አጠባበቅ ተቋማት እና ድልድዮችን ጨምሮ ብዙ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል።

እነዚህ እንደገና መገንባት አለባቸው። ልጆች ሁል ጊዜ ቤት ውስጥ እንዳይቆዩ ለማድረግ ብቻ ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ የሚጠየቁባቸውን አንዳንድ አካባቢዎች አይቻለሁ። ወደ ትምህርት ቤቶቻቸው መመለስ ሲችሉ፣ ትምህርት ቤቶቻቸው ፈርሰዋል። እነሱ ስለዚህ ወለሉ ላይ ተቀምጠዋል ወይም ድንጋይ ወይም የእንጨት ግንድ ላይ ተቀምጠው ነው የሚማሩት። ነገር ግን የተማሪዎቹ አንድነት በጣም አስፈላጊ ነው።

የህዝቡ ስቃይ እንደቀጠለ ነው። የተባበሩት መንግስታት የአለም ምግብ ፕሮግራም፣ አለም አቀፍ ቀይ መስቀል እና ሌሎች በርካታ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ በካሪታስ፣ በኦርቶዶክስ፣ በሙስሊሞች እና በፕሮቴስታንቶች በኩል በተቻለ መጠን ምግብን እና መድሃኒትን ለማዳረስ እየሞከሩ ነው። ይህ አሁን ያለው ሁኔታ ረሃቡ ወደ ከፋ ረሃብ እንዳይሻገር ለመታደግ ይቀጥላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

ጥያቄ፡- በትግራይ ክልል  ያለው ሰብአዊ ሁኔታ ብዙ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል። ይህንን በተመለከተ የሚሉን ነገር ካለ?

የተባበሩት መንግስታት ወይም መንግስት ወይም ሌሎች ኤጀንሲዎች ምግብ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚሞክሩትን የሰብአዊነት ኮሪደሮችን ማመቻቸት አንዳንድ ጊዜ ማንነታቸው በማይታወቅ አካላት እየታገዱ በመሆናቸው በትግራይ ያለው ሰብአዊ ሁኔታ እየተባባሰ ሄዷል። በዚህ ምክንያት የህዝቡ ስቃይ እየከፋ መጥቷል። እንደ ኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ያደረግነው በዓለም ላይ ላለው የካቶሊክ ኔትወርክ በተለይም በካሪታስ ኢንተርናሽናልስ በኩል አቤቱታ ማቅረብ ነው። የዛሬ ሁለት ሳምንት ብቻ እነዚህን ወገኖች መርዳት ይችሉ ዘንድ፣ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በአጎራባች ክልሎች ለሚኖሩ ሰዎች እንዲደርስ የ100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ድጋፍ ጥሪ ማቅረብ ችለናል። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የድርቁ ሁኔታም ተባብሷል። ሰዎች እርዳታ የሚፈልጉበት ይህ ታላቅ የሰብአዊ ቀውስ አለን።

ጥያቄ፡ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፊኤል፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዩክሬን ለሚካሄደው ጦርነት የትንሳኤ ዕርቅ እንዲደረግ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ምን አስፈላጊ ነገር አዩ?

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነት በመፈጠሩ አዝነናል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወደ 75 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ በአውሮፓ ጦርነት እንደማይኖር አስቤ ነበር። የዩክሬንን ጦርነት እና የህዝቡን ስቃይ ስናይ በጣም ያማል። ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከአገራቸው ውጭ ስደተኞች መሆናቸውን በዜና እንሰማለን። ስደተኛ መሆን ምን ማለት እንደሆነ እናውቃለን ምክንያቱም ኢትዮጵያ ስደተኞችን ከሚንከባከቡ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ነች። ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የሶማሊያ ስደተኞች፣ ወደ 300,000 የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች፣ እና ወደ 430,000 የሚሆኑ ተጨማሪ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች አሉን። በሚያስገርም ሁኔታ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የሶሪያ ስደተኞች አሉን። እንዴት እዚህ እንደደረሱ ባላውቅም ሰዎች በየቦታው እየተጓዙ ነው። ጦርነት ስለሚያወድም በዩክሬን ያለው ጦርነት እንደማይባባስ ተስፋ እናደርጋለን።

በቴሌቭዥን ፣ ሥዕሎች ፣ የዩክሬን ብቻ ሳይሆን የኢራቅ እና የሶሪያ ፣ የሊባኖስ ፣ እና አሁን የመንንም እናያለን። ብፁዓን ጳጳሳት ስለ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት፣ እዚህም እዚያም እየተከሰቱ ስላለ በየጊዜው ያስጠነቅቃሉ። ይህ በቁም ነገር መታየት እና በተቻለ ፍጥነት ማቆም ያስፈልጋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በፋሲካ በዓል የጦር መሣሪያዎች ጸጥ እንዲሉ በመግለጽ ለሰላም ያቀረቡት ጥሪ በጣም በጣም ወቅታዊ ነው። ይህ የቅዱስ አባታችን የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ድምጽ ብቻ ሳይሆን ሩሲያ እና ዩክሬን ክርስቲያን ስለሆኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህ ጥሪ ይመለከታቸዋል። ከሞስኮ ፓትርያርክ የቀረበው ተመሳሳይ አቤቱታ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን የእርቅ ስምምነት እውን ለማድረግ የበለጠ ያግዛል። አሁን በየመን በረመዳን ፆም ምክንያት ህዝበ ሙስሊሙ ለአንድ ወር ትግሉን አቁሟል። ለፋሲካ ሰላም የቅዱስ አባታችንን ያቀረቡትን ጥሪ እደግፋለሁ።

ጥያቄ፡ ካርዲናል ኢትዮጵያ ውስጥ ድርድር በመካሄድ ላይ ባለበት ወቅት ሁኔታው ​​በመጠኑ መሻሻል ላይ እንደሚገኝ ተናግረው ነበር። የቅዱስ አባታችን የገና በዓልን አስመልክቶ በላትን ቋንቋ “Urbi et Orbi” (ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም) በተሰኘው መልእክታቸው እና በቅርቡ ደግሞ እ.አ.አ በየካቲት 27/2022 ዓ.ም የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካደረጉ በኋላ  ባስተላለፉት መልእክት የተናገሯቸው ቃላት በሆነ መንገድ ለዚህ እድገት አስተዋጽኦ አድርጓል ብለው ያምናሉ?

አዎ! የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች፣ የፕሮቴስታንት አመራር አባላት፣ እንዲሁም የሀገሪቱ ሙስሊሞች ለቅዱስ አባታችን ትልቅ ክብር አላቸው።

እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ተራው ሕዝብ ሁሉ ስለ ሰላም እየጸለየ ነው። ህዝቡ ስለ ሰላምና አንድነት እየጸለየ ነው ለማለት እችላለሁ።

ለዘመናት አብረን ኖረናል። ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ብቻ የታየችው ኢትዮጵያ የግጭት ወይም የጦርነት አገር ሆና መታየት የለባትም ይህም የሆነው በተለያዩ አተረጓጎሞች ወይም ፖለቲካዊ ፍላጎቶች የተነሳ ነው። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ፈተናዎች አሉብን፡ ግን አምናለሁ እናም ለዘመናት አንድ ሆነው የኖሩ፣ ተጋብተው እና ኢትዮጵያዊ ሆነው የሚኖሩ ህዝቦች ጸሎታቸውን አምናለሁ። ህዝቡ ወደ አንድነቱ ተመልሶ ወደ አንድነት እንዲመጣ አንዳንድ መፍትሄዎች እንደሚኖሩን ተስፋ እናደርጋለን። እኛ ክርስቲያኖች ስለ ሁላችን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በሞተው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እይታ ሥር ሆነን እንጸልያለን።

 

14 April 2022, 19:12