ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ፣ ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ፣  

ቤተ ክርስቲያን ለአቅመ ደካሞች ትኩረት እየሰጠች ወንጌልን መስበክ ትቀጥላለች!

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደትን ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ፣ መጋቢት 21/2014 ዓ. ም. በጣሊያ ውስጥ ፔስካራ ከተማ በተደረገው “ኦፔራ ዶን ኦርዮኔ” በሚል ስም በሚታወቅ የዕርዳታ መስጫ ማዕከል ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል። ብጹዕነታቸው በዕለቱ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ ቤተ ክርስቲያን ለአቅመ ደካሞች ትኩረትን እየሰጠች ወንጌል መስበክን እንደምትቀጥል ተናግረው፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል የሚቀርበውን የስደተኞች መስተንግዶ ዕቅዶችን ለማስካት ምዕመናን የዕርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ አሳስበው፣ ይህም ቤተክርስቲያኗ የወንጌል ኃይልን የምትገልጽበት መንገድ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ከቤተክርስቲያን ተልዕኮ መካከል የመጀመሪያው የእግዚአብሔርን ቃል ማወጅ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ቅዱሳት ምስጢራትን በመስጠት የሚገልጽ የወንጌል ስርጭት መኖሩን አስታውሰው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን የበጎ አድራጎት ሥራን ማከናወን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በጣሊያን ውስጥ ፔስካራ በተባለ አካባቢ ተገንብቶ አገልግሎት እንዲሰጥ የተዘጋጀው መጠለያ ማዕከሉ፣ በችግር ውስጥ ለወደቁት የተስፋ መሠረት እንደሆነ ገልጸው፣ በአካባቢው ለሚገኝ በርካታ ተጋላጭ ማኅበረሰብ ተጨባጭ የፍቅር መግለጫ መሆኑን አስረድተዋል።

የእግዚአብሔር ፍቅር ከእናት ፍቅር ይበልጣል

በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ከትንቢተ ኢሳይያስ መጽሐፍ ተውስዶ ተነበበውን የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ በእግዚአብሔር ጸጋ የታደሰ ዓለም፣ መከራና ሥቃይ መሸነፉን እንድንመለከት፣ የወደፊቱን አዲስ ጊዜ በእምነት እንድንጠባበቅ ያግዘናል ብለው፣ የእግዚአብሔር ፍቅር ከሰው ፍቅር እንደሚበልጥ አስገንዝበዋል።

“እናት ለልጆቿ ካላት ፍቅር የበለጠ ምን ሌላ ጠንካራ ሊኖር ይችላል?” ያሉት ብጽዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል በመካሄድ ላይ ባለ ጦርነት የዩክሬን እናቶች ንብረታቸውን እና ባሎቻቸውን ትተው ልጆቻቸውን ብቻ ይዘው በመሸሽ ከቦምብ ጥቃት ለማዳን የሚያሰርጉትን ጥረት አስታውሰው፣ የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ከዚህ በላይ እንደሆነና የሞትን ኃይል እንኳ ማሸነፍ እንደሚችል አስረድተዋል። ሁኔታው እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እንድንገነዘብ ይጋብዘናል ብለው፣ በጎ ሥራችንም ከዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር የሚመነጭ መሆን አለበት ብለዋል።

ወንጌልን በቃል እና በተግባር ማወጅ

“የብዙ ሰዎችን ጥያቄ የሚመልስ መጠለያ ማዕከሉ የቤተ ክርስቲያናችንን መልካም ገጽታን ያሳያል" ብለው፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት በርካታ ምዕመናን ባቀረቡት ስብከት፣ “በዚህ ስፍራ ጥንካሬውን የሚገልጽ፣ ፍሬውንም የሚያፈራ ቅዱስ ወንጌል በቃል ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ በምሕረት ሕይወትና በሥራ ይገለጽ ዘንድ” ምዕመናኑ ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋናቸውን በማቅረብ፣ በጸሎትም እንዲተባበሩ በመጋበዝ፣ የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደትን ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ ስብከታቸውን ደምድመዋል።

31 Mar 2022, 16:14