ፈልግ

የመቁጠሪያ ጸሎት የመቁጠሪያ ጸሎት  

ትልቁ ግብዣ

አንድ ሰውዬ በሚገባ ምሳ አዘጋጅቶ ብዙ ሰዎችን ጠራ፡፡ የምሳ ሰዓት ሲደርስ አገልጋዮቹን ልኮ ለተጋባዦቹ «ሁሉ ነገር ተሰናድቷል ኑ!´ በማለት አስጠራቸው፡፡ እነርሱ ግን ምክንያት ፈጥረው ቀሩ አንዱ «መሬት ገዝቻለሁና ሄጄ ማየት ስላለብኝ መምጣት አልችልምና ይቅርታ አድርግልኝ´ አለው፡፡ አንዱ ደግሞ «አምስት ጥንድ በሬዎች ስለገዛሁ እነርሱን መፈተን አለብኝ ስለዚህ መምጣት አልችልምና ይቅርታ አድርግልኝ´ እንደገና አንደኛው ደግሞ «ሚስት አግብቼ ሙሽራ ስለሆንኩ ልመጣ አልችልም ስለዚህ ይቅርታ አድረግልኝ´ እያሉ በየምክንያታቸው ከግብዣው ቀሩ፡፡

አገልጋዩም ተመልሶ ለጌታው ተጋቦዦቹ ያሉትን ነገረው፡፡ ጌታውም ይህን በሰማ ጊዜ በጣም ተናዶ «ቶሎ ብለህ ወደ ከተማው ጐዳናዎችና በየሥርቻው መንገዶች ሂድ፡፡ ድኻዎችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ዕውሮችን፣ አንካሶችንም ጠርተህ ወዲህ አምጣልኝ፣ ከተጋበዙት ውስጥ አንድ ስንኳ ምሳዬን እንደማይበላ ይወቅ” (ሉቃ. 14፣16-241) አለው፡፡

 ምሳውን አዘጋጅቶ የጠራው ሰውዬ እግዚብሔር ነው፡፡ የተጋበዙት ሰዎች ደግሞ ለገብዣው እግዚአብሔርን የሚተው ሲጠራቸው የማይመለሱለት ሰዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ሊደረስ በማይቻለው ውሳኔው ለብዙ ሰዎች ከመንፈሳዊ ገበታው እንዲሳተፉ ይጋብዛቸዋል፡፡ ለሁሉም ሰዎች አዳኝ ልጁን እንዲቀበሉት፣ እርሱ ወደ ሠራት የደኀንንት መርከብ ወደሆነችው ቤተክርስቲያን ገብተው ደኀንነት እንዲያገኙ፣ በእርሷ ውስጥ የሚገኙትን ምስጢራት እንዲሳተፉ ይጠራቸዋል፡፡ ይህን ሁሉ መንፈሳዊ ምግብና ሀብት አቅርቦ «ኑ እንጀራዬን ብሉ ወይን ጠጄን ጠጡ፣ ሞኝነትን ተውት ሕይወትን ታገኛላችሁ´ እያለ ሰማዊ ግብዣውን ለሁሉ ያቀርባል፡፡ ሁሉም መጥቶ የደህንነትን ማዕድ እንዲሳተፍ ለደኀንነት የሚያስፈልገው ጸጋ እንዲቀበል ይፈልጋል፡፡

የአምላክ ግብዣ ለሰዎች ሁሉ ተትረፍርፎ የሚደረስ ቢሆንም ብዙዎች ግን መለኮታዊውን ግብዣ መቀበል አይፈልጉም፣ በዚህ መለኮታዊ ገበታ ጥቂቶች ብቻ ይሳተፋሉ፣ የሚበዙት ሳይሳተፉ ይቀራሉ፡፡ እነዚያ የእግዚአብሔርን ግብዣ የሚበቀበሉ የዋሆችና ጥሩ ነገር ፈላጊዎች ናቸው፡፡ ለነፍሳቸው የሚያስቡ ሰዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር «ኑ ምግቤን ብሉ ወይን ጠጄን ጠጡ´ ሲላቸው «ይኸው መጥተናል´ እያሉ ሰማያዊውን ሀብቱን በመቀበል በጸጋው ይጠግባሉ፣ ደኀንነት ያገኛሉ፡፡ ሌሎች ግን ለዚህ መንፈሳዊ ግብዣ ግድ የላቸውም፡፡

«ሥራ አለብኝ፣ ጊዜ የለኝም፣ አይቻለኝም፣ አይስማማኝም፣ ፀሎት ላድርግ፣ ሚስጥራትን ልሳተፍ ለነፍሴ የሚያስፈልግ መንፈሳዊ ተግባር ልፈጽም ቤተክርስቲያን ለመሄድ አይመቸኝም´ እያሉ ያመካኛሉ፡፡ ከመንፈሳዊ ነገር ይርቃሉ፣ በደኀንነታቸው ይቀልዳሉ፣ ለሥጋቸው ሲያስቡ በነፍሳቸው ይጫወታሉ፡፡ የነፍሳቸውም ደኀንነት ሲበላሽ ዝም ብለው ያያሉ፡፡

ግብዣ ያለመቀበል ወይም ከጋባዡ መሸሽ ክህደት ስለሆነ ጥል ያስከትላል፡፡ የሰው ግብዣ እንደዚህ ከሆነ የአምላክ ግብዣ እንዴት ይሆን; እግዚአብሔር በመጀመሪያ አይሁዳውያንን ለደኀንነት ጠራቸው፡፡ እነርሱ እምቢ ሲሉት ግን ሌሎችን ጋበዘ፡፡ እነዚህ ግብዣውን ተቀበሉት እግዚአብሔር ሲጠራን ወደ መንፈሳዊ ገበታው ሲጋብዘን እምቢ ካልን ተቆጥቶ ሊተወንና ሊቀጣን ነው፡፡

 

21 Feb 2022, 11:35