ፈልግ

እግዚአብሔር ሰውን ፍለጋ ይመጣል እግዚአብሔር ሰውን ፍለጋ ይመጣል 

እግዚአብሔር ሰውን ፍለጋ ይመጣል

የእግዚአብሔር መገለጥ

እግዚአብሔር ለሰው ምን ይገልጣል?

እግዚአብሔር በቸርነቱና በጥበቡ ራሱን ይገልጣል፡፡ ራሱንና ከጥንት ጀምሮ በክርስቶስ የወሰነውን የፍቅር ዕቅድን በሥራም በቃላትም ይገልጣል፡፡ በዚህ ዕቅድ መሠረት ሰዎች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ እንደተገኙ “ልጆች” በአንድያ በእግዚአብሔር ልጅ መለኮታዊ ሕይወት ይካፈላሉ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የእግዚአብሔር መገለጥ የመጀመሪያ ደረጃዎች ምንድናቸው? ከመጀመሪያ አንሥቶ፣ እግዚአብሔር  ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ራሱን ገለጠ፣ ከእርሱ ጋር ህብረት እንዲኖራቸውም ጠራቸው። እነርሱ በኃጢአት ከወደቁም በኋላ፣ መገለጡን አላቋረጠም፣ ለዘሮቻቸውም ሁሉ ደኀንነትን እንደሚሰጣቸው የተስፋ ቃል ገባ፡፡ በውሃ ጥፋት በኋላ ከኖህ ጋር እንዲሁም በራሱና በሁሉም ሕያዋን ፍጥረታት መካከል ቃል ኪዳን አቆመ።

የእግዚአብሔር መገለጥ ቀጣይ ደረጃዎች ምንድናቸው?

እግዚአብሔር አብራምን መረጠ፣ ከአገሩም ጠራው፣ “የብዙ አሕዛብ አባት አደረገው” (ዘፍ. 17፡5) በእርሱም በኩል “የምድርን አሕዛብ ሁሉ” እንደሚባርክ ቃል ገባለት (ዘፍ. 12፡3)፡፡ የአብርሃም ዘሮች ለአበው የተገባውን መለኮታዊ ቃል መጋቢዎች ሆኑ፡፡ እግዙአበሐር እስራኤልን የራሱ ሕዝብ አድርጎ መረጣቸው፣ ከእነርሱም ጋር በሲና ተራራ ላይ ቃል ኪዳን አቆመ፣ በሙሴም አማካይነት ሕጉን ሰጣቸው፡፡ ነቢያት ስለ ሕዝቡ መሠረታዊ መዳንና ሁሉንም ሕዝቦች በአዲስና ዘላለማዊ ቃል ክዳን ውስጥ ስለሚያካትተው ደኀንነት ሰበኩ፡፡ ከሕዝበ እሰራአልና ከንጉሥ ዳዊት ቤት ኢየሱስ መስሕ ተወለደ፡፡

የእግዚአብሔር መገለጥ የመጨረሻና ወሳኝ ደረጃ ምንድነው? 

የእግዚአብሔር መገለጥ የመጨረሻና ወሳኝ ደረጃ የፈጸመው ሥጋ በሆነው ቃሉ፣ መካከለኛና የመገለጥ ሙላት በሆነው በኢየስስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ሰው የሆነ የእገዚአበሐር አንድያ ልጅ ነው፣ የአብ ፍጹምና የመጨረሻ ቃል ነው፡፡ የዚህን ቁምነገር የቤተክርስትያን እምነት በዘመናት ሂደት ቀስ በቀስ የሚገነዘበው ቢሆንም በወልድ መምጣትና በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተነሣ የእግዚአብሔር መገለጥ አሁን ሙሉ በሙሉ ተፈጽሞአል፡፡ “ልጁን፣ አንድያና የመጨረሻ ቃሉን፣ ለእኛ በመስጠት እግዚአበሐር ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ በዚህ አንድያ ቃሉ ተናገረን፤ ስለዚህ ሌላ የሚናገረው ነገር የለም፡፡” (ቅዱስ ዮሐንስ ዘመስቀል)

የግል መገለጦች ዋጋ ምንድነው?

የእምነት ሀብት አካል ባይሆኑም፣ የግል ራእዮች ወደ ክርስቶስ እስከመሩን ድረስ ሰውን በእምነት እንዲኖር ሊረዱ ይችላሉ፡፡ እነዚህነ የመሰሉ የግል ራእዮችን የመመርመር ኃላፊነት ያለበት የብተክርስያን የላይ አመራር ወሳኝ መገለጥ የሆነውን ክርስቶስን እንልቃለን ወይም እናርማለን የሚሉትን የግል ራእዮች አይቀበልም።

የመለኮታዊ መገለጥ መነገር

የመለኮት መገለጥ የሚነገረው ለምንና እንዴት ነው?

እግዚአብሔር “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ይፈልጋል” (1ኛ ጢሞ. 2፡4)፡፡ እርሱም ኢየስስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ” (ማቴ. 28፡19) በሚለው በራሱ ትእዛዝ መሠረት ክርስቶስ ሊሰበክ ይገባል። ይህም የሚፈጸመው በሐዋርያዊ ትውፊት ነው።

ሐዋርያዊ ትውፊት ምንድነው?

ሐዋርያዊ ትውፊት ከክርስትና እምነት መጀመሪያ አንሥቶ በስብከት፣ በምስክርነት፣ በተቋማት፣ በአምልኮ እና በመንፈሳዊ ጽሑፎች አማካይነት የክርስቶስን መልእክት ማስተላለፍ ነው፡፡ ሐዋርያት ከክርስቶስ የተቀበሉትንና ከመንፈስ ቅዱስ የተማሩትን ሁሉ ለተከታዮቻቸው፣ ለጳጳሳት፣ በእነርሱም በኩል ለትውልዶች በሙሉ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ አስተላለፉ፡፡

ሐዋርያዊ ትውፊት የሚገኘው በምን ዐይነት መንገድ ነው?

ሐዋርያዊ ትውፊት የሚገኘው በሁለት መንገዶች ነው፤ እነርሱመ ቃለ እግዚአብሔርን ሕያው በሆነ መንገድ (በአጭሩ በትውፊት) ማስተላለፍና በጽሑፍ መልክ ድኀነትን መስበክ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት ነው።

በትውፊትና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከለ ያለው ግንኙነት ምንድነው?

ትውፊትና መጽሐፍ ቅዱስ በቅርብ የተሳሰሩና እርስ በርስ የሚገናኙ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸውም በቤተክርስትያን ውስጥ የክርስቶስን ምስጢር ሕያውና ፍሬያማ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ከአንድ መለኮታዊ ምንጭ የሚነሡና ቤተክርስያን ስለራእይ እርግጠኛነትዋን የምታገኝበት የእምነት የተቀደሰ ሀብት መሠረት ናቸው፡፡

የእምነት መዝገብ አደራ የተሰጠው ማን ነው?

ሐዋርያት የእምነትን መዝገብ ለመላዋ ቤተክርስቲያን አደራ ሰጥተዋል፡፡ ሕዝበ እግዚአብሔር በሙሉ ለእምነት ካለው የላቀ ስሜት የተነሣ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታና በቤተክርስቲያን የበላይ አመራር መሪነት መለኮታዊ የመገለጥ ስጦታን ከመቀበል፣ ወደ ሥራ ጠልቆ ከመግባትና በሙላት ከመኖር አያቋርጥም፡፡

የእምነት ቅርስ በሐቅ የመተርጐም ሥራ የተሰጠው ለማን ነው? 

የእምነትን ቅርስ በሐቅ የመተርጎም ሥራ የተሰጠው ለቤተክርስቲያን ሕያው የማስተማር ሥልጣን ላላቸው ማለትም የጴጥሮስ ተከታይ ለሆኑት ለሮም ጳጳስ እና ከእርሳቸውም ጋር ለጳጳሳት ነው፡፡ በመለኮት መገለጥ ውስጥ የሚገኙ እውነቶችና ድንጋጌዎች የሆኑትን ቀኖናዎች የማስረዳት ሥራም የዚህ በቃለ እግዚአብሔር አገልጋይነቱ የተወሰነ የእውነት ጸጋ የተሰጠው የቤተክርስቲያን የበላይ አመራር ነው፡፡ ይህ የቤተክርስቲያን የበላይ አመራር ሥልጣን ከራእይ ጋር የተገናኙ እውነቶችንም ያካትታል።

በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በትውፊትና በቤተክርስቲያን የበላይ አመራር መካከል ያለው ግንኙነት ምንድነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ትውፊትና የቤተክርስቲያን የበላይ አመራር እርስ በርሳቸው በቅርብ የተሣሠሩ ከመሆናቸው የተነሣ አንዱ ያለ ሌላው ሊቆም አይችልም፡፡ በአንዱ በመንፈስ ቅዱስ ሥር ሆነው እያንዳንዳቸው በራሳቸው መንገድ በጋራ በመሥራት ለነፍሳት ደኀንነት ሁሉም ውጤታማ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ምንጭ፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በአጭሩ ከተሰኘው በ2001 ዓ.ም ይፋ ከሆነው ሁለተኛ እትም መጽሐፍ ላይ ከአንቀጽ 50 እስከ 90 ላይ ከተጠቀሰው የተወሰደ።

24 January 2022, 13:21