ፈልግ

የሲቪል መብቶች መሪ የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ የሲቪል መብቶች መሪ የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ  

የአሜሪካ ጳጳሳት የማርቲን ሉተር ኪንግን ትንቢታዊ ምስክርነት መከተል እደሚያስፈልግ አሳሰቡ

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ሰኞ ጥር 9/2014 ዓ. ም. ታስቦ የዋለውን የሲቪል መብቶች መሪ የማርቲን ሉተር ኪንግን መታሰቢያ ዕለትን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ አሜሪካውያን የማርቲን ሉተር ኪንግን ትንቢታዊ ምስክርነት መከተል እደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጳጳሳቱ አክለውም በጎ ፈቃድ ያላቸው ሁሉ ከእርሱ አርአያነት በመነሳት ለአሜሪካ ማኅበረሰብ የእኩልነት እና የፍትህ ሥራ ማሳየትን መቀጠል እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከአውሮፓዊያኑ 1983 ዓ. ም. ጀምሮ የሲቪል መብቶች መሪ የማርቲን ሉተር ኪንግ ሕይወት እና ትሩፋትን እንዲታሰብ መወሰኑ ሲታወስ፣ ዕለቱን በማስታወስ የአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ትናንት ሰኞ ጥር 9/2014 ዓ. ም. መግለጫቸው ማውጣታቸው ታውቋል። የጳጳሳቱን መግለጫ ይፋ ያደረጉትን የጉባኤው ፕሬዚደንት እና የሎሳንጀለስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎሜዝ፣ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ የወንድማማችነት እና ዓመፅ የሌለበት ትንቢታዊ ምስክርነት እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል። ታዋቂው አክቲቪስት ሊታወስ የሚገባው በተከተለው የፍትህ መንገድ ብቻ ሳይሆን “እንዴት እንደተከተለው” ሊታውስ ይገባል ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጎሜዝ ጥር 15/2014 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት መግለጫው ላይ እንደገለጹት፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የጽድቅ እና የእውነት ራዕይ መመራቱን ገልጸው፣ ይህ ራዕይ የአሜርካንን ምስረታ ሰነዶች የሚያንጸባርቅ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም "ሁሉም ሰው እኩል የተፈጠረ፣ በእግዚአብሔር የተቀደሰ ክብር እና የማይካድ የሕይወት፣ የነፃነት እና የእኩልነት መብቶች እንዳሉት በመስራቾቻችን የተገለጸውን የአሜሪካን የእምነት መግለጫን ያምን ነበር ብለዋል።

አሜሪካ ዛሬ ብዙ ፈተናዎች ገጥሟታል

ማርቲን ሉተር ኪንግ የተገደለው እ. አ. አ ሚያዝያ 4/1968 ዓ. ም. በሜምፊስ፣ ቴነሲ ውስጥ ብቻውን እያለ በታጣቂው ጄምስ አርል ሬይ ሊሆን እንደሚችል ይጠረጠራል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ በመልዕክታቸው፣ የሲቪል መብቶች መሪ ማርቲን ሉተር ኪንግ   ከሞቱ ከ54 ዓመታት በኋላም “አሜሪካ ብዙ ፈተናዎች ከፊቷ ተጋርጦባታል” ብለው፣ ከፈተናዎች መካከል አንዳንዶቹ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በሃብት መጠን ልዩነት እና የዘር መድልዎ ጉዳዮች፣ በማህበረሰቦች ውስጥ የሚፈጠር ብጥብጥ እና ስደተኞችን ለመቀበል የሚደረገውን ትግል እንደሚጨም አስረድተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱ ይበልጥ እየተከፋፈለች በዜጎች መካከል ልዩነት እያደገ መምጣቱን በማከል አስረድተዋል።

ከሉተር ማርቲን ጥበብን ማግኘት

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ የወደፊት ጊዜ በመልከት እንደተናገሩት፣ የአሜሪካ ሕዝብ ከማርቲን ሉተር ኪንግ ጥበብ በመማር፣ በተለይም የኢየሱስ ክርስቶስን በረከቶች ለመከተል ካለው ቁርጠኝነት፣ ሰላማዊ ትግል ማካሄድን እና ጠላትን የመውደድ መርሆዎችን መጠቀም ዘላቂ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ወንድማማችነት እና አመጽ አልባነት

የመጥምቃዊያን ቤተክርስቲያን አገላጋይ እና የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ ማርቲን ሉተር ኪንግ እ. አ. አ ሚያዝያ 16/1963 ዓ. ም. የጻፉትን የ "በርሚንግሃም እስር ቤት" ደብዳቤን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ በሚኖሩበት ከተማ የጥቁር አሜሪካውያን አያያዝ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጉ ምክንያት ተይዞ መታሰሩን አስታውሰዋል። በዚህ ደብዳቤው የሲቪል መብቶች መሪ ማርቲን ሉተር ኪንግ “እኛ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ነን” ማለቱን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ጎሜዝ አስታውሰው፣ በጋራ መተሳሰብ እና ግንኙነት እያንዳንዳችን በሌሎች ላይ እንደምንመካ ሁሉ ሌሎችም በኛ ላይ ይመካሉ በማለት ሊቀ ጳጳስ ጎሜዝ ተናግረው፣ “በዚህ የወንድማማችነት እና የመተሳሰብ መንፈስ ወደ ፊት በመጓዝ ለእኩልነት እና ለፍትህ መሥራትን መቀጠል ይኖርብናል” በማለት አሳስበዋል።

ጆ ባይደን ለማርቲን ሉተር ኪንግ ያላቸውን ክብር ገልጸዋል

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን እና ምክትላቸው ወ/ሮ ካማላ ሃሪስ ማክሰኞ ጥር 3/2014 ዓ. ም. ለማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ያላቸውን ክብር የአትላንታውን ታሪካዊ የአቤኔዘር መጥምቃዊያን ቤተክርስቲያንን በመጎብኘት የገለጹ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኗ ማርቲን ሉተር ኪንግ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በሐዋርያነት ያገለገላት መሆኗ ታውቋል። ፕሬዚደንቶቹ በመካነ መቃብሩ ላይ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ አክብሮታቸውን ገልጸውለታል። የማርቲን ሉተር ኪንግ ባለቤት ወ/ሮ ኮርታም በተመሳሳይ መካነ መቃብሩ መቀበራቸው ታውቋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ ሁለቱ የማርቲን ሉተር ኪንግ ልጆች፣ ዶ/ር በርኒስ ኪንግ እና ማርቲን ሉተር ኪንግ ሳልሳዊ መገኘታቸው ተነግሯል።  

18 January 2022, 16:12