ፈልግ

ከግብፅ ወደ ናዝሬት ከግብፅ ወደ ናዝሬት 

የጥር 8/2014 ዓ.ም ሰንበት ዘናዝሬት ዕለተ ሰንበት አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.    ሮሜ. 15፥1-13

2.    1ዮሐ. 4፥14-21

3.   ሐዋ.ሥ. 13፥32-43

4.   ማቴ.2፥19-23

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ከግብፅ ወደ ናዝሬት

ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው። ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘናዝሬት የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን። በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተነበቡት ንባባት አማካኝነት ለእያንዳንዳችን የሚሆን የሕይወት ስንቅ ይሰጠናል የሕይወት ምግብ ይመግበናል። የእግዚአብሔር ቃል እንደ ወትሮው ዛሬም ወደ እያንዳንዳችን ይሠርፃል፣ እኛም ወደ እኛ የመጣውን ቃል ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን በተግባር እንድናውለው ያስፈልጋል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ራሳችንን ማስደሰት አይገባንም በማለት በዕለቱ መልዕክት ላይ የጌታችንን እየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ምሳሌ በማድረግ ይመክረናል። እንዲሁም 1ኛ ዮሐ. 3፥16 ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ስለእኛ አሳልፎ ስለሰጠ፣ ፍቅር ምን እንደ ሆነ በዚህ እናውቃለን፤ እኛም ሕይወታችንን ስለ ባልንጀራዎቻችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባል።”  የሚለውን ሃሳብ ይሰጠናል።

እንዲሁም በገላ. 2 ላይ እርስ በርሳችሁ ከእናንተ እያንዳንዱ የሌላውን ሸክም ይሸከም። ሸክም የተባለው ምንድን ነው? የአንዳንድ ሰው ሸክም ምክንያት የአንድ ሰው ሥራና ኅላፊነት መብዛት ሊሆን ይችላል ምን አልባት የባለእንጀራችን ሥራ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ የድካም ስሜት ሲኖር እኛ የሥራውን ሸክም ማገዝ ይኖርብናል። ሌሎችም ሸክሞች ሊኖሩ ይችላሉ፥ እንደ ጭንቀት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ሐዘን፣ ድካም፣ ሕመም የመሳሰሉት ይሆናሉ። እነዚህንና የመሳሰሉትን የአካልና የመንፈስ ሸክሞች በመተጋገዝ በዮሐ. 15፥ 12 እንደተጻፈው “እኔ እንደወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” የሚለውን የወንጌል ብሥራት አብሳሪዎች እንድንሆን በቃሉ ምክሩን ይለግሰናል።   

ራሳችንን ከሌሎች ሰዎች ሕይወት ጋር ማወዳደር የለብንም ይልቁንም ሕይወታችንን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ጋር በንጽጽር በየዕለቱ መመልከት የቻልን እንደሆነ የበለጠ ትሑታን እንሆናለን።

ምክንያቱም ትሕትና ከራስ ይልቅ የሌላውን ሰው መሻት መገመት ራስን ዝቅ በማድረግ ከምድራዊ የበላይነት ውድድር ራስህን መቆጠብ እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ያብራራል። የብሉይ ኪዳን የመጨረሻ ነቢይ የሚባለው አጥማቂው ዮሐንስ እንደሁም ድንግል ማርያምና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትሕትና መምህራኖቻችን ናቸው። ማር. 1፥7፣ ሉቃ. 1፥38

የቤተክርስቲያን ቅድሳን ታሪክ መለስ ብለን ስንመለከት ብዙዎች እንደ ጳውሎስና እንደ መጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ለወንጌል ተልእኮ ከሀገር ወደ ሀገር በመሄድ አገልግለዋል። አንዳንዶቹ በበረሐ በጾም፣ በጸሎትና በተጋድሎ አሳልፈዋል። እንዳንዶቹ ደግሞ በተጋድሎና በብቸኝነት ሲያሳልፉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሰምተው በመኖር ብቻ ተቀድሰዋል።

እነዚህ ሁሉ የጽድቅ አክሊል የተካፈሉት ራሳቸውን ለፈጣሪያቸው በማስገዛትና የእግዚአብሔር ፈቃድ በትሕትና በመጠበቃቸው ነበር። በመሠረቱ ሰው ሁሉ የተጠራው ለቅድስና ነው። የቅድስናን ሕይወት ለመለማመድ የክርስቶስን ሕይወት እያንዳንዱ ሰው መለማመድ የግድ ያስፈልጋል። የክርስቶስን ሕይወት ለመለማመድ ደግሞ ከክርስቶስ መማር ወሳኝ ነገር ነው። “እናንተ ደካሞች ወደ እኔ ኑ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ ... ከእኔም ተማሩ የዋህና ትሑት ነኝ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” ማቴ. 11፥28-29። የነፍስ ዕረፍት ለማግኘት የክርስቶስን ትሕትና መማር አስፈላጊ መሆን ይገልጻል። የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ተልእኮአችን እንዲሰምር የትሕትና መምህር ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ መቅረብ ያስፈልጋል።

ትሑታንንና ትዕዛዝ የሚፈጽሙትን እግዚአብሔር በእውነትና በፍቅር እንደሚመራቸው ዳዊት ከራሱ የሕይወት ልምዱ በመነሣት ገልጾልናል። ትሕትና በእግዚአብሔር ፊት ጥበብ እንደሆነ በመጽሐፈ ምሳሌ እንደሚከተለው ተገልጿል። “እግዚአብሔርን ብትፈራና ትሑት ብትሆን ሀብት፣ ክብርና ረዥም ዕድሜ ታገኛለህ” ምሳ. 22፥4 ሁሉም ሰው የሚመኘውን መንግሥተ ሰማያት የሚወርሰው “በመንፈስ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ” እንደሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጾልናል። ማቴ. 5፥3 ይህንኑ ሐሳብ ለማጠናከር ሐዋርያት በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን እንደሆነ በጠየቁት ጊዜ አንድ ሕፃን በመካከላቸው አቁሞ “እንደዚህ ህፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይሆናል” በማለት አስተምሮአቸው ነበር። ማቴ. 18፥4 በዚህ አባባል መሠረት ትሕትና ወደ መንግሥተ ሰማያት መግቢያ ወሳኝ በር እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

የሐዋርያት ጥያቄ የሁላችን ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ክርስቲያን ሆኖ በክርስቶስ ተስፋ የተሰጠውን መንግሥተ ሰማያት የማይመኝ አይኖርም። በክርስቶስ የማመንና ክትስቶስን የመከተል ትልቁ ዓላማ ለመንግሥተ ሰማያት ሕይወት ነውና። በሥጋዊ ዐይን ስንመለከት የምድራዊ ሕይወት ጉጉት ማለትም የሀብት፣ የሥልጣን፣ የክብርና ዝና የማትረፍ ፍላጐት በክርስቶስ መንፈስ እንዲገራ ጊዜ ይወስዳል።

እግዚአብሔር በሁሉም ነገር ፍጹምና ሙሉ በመሆኑ ካለበት ደረጃ ከፍ ለማለት አይጓጓም። ጌታችን ኢየሱሰ ክርስርቶስ የእግዚአብሔር ፍጹም ፍቅር ለእኛ ሊያካፍል ሲመጣ በገዛ ፈቃዱ አምላካዊነቱን ሳይተው በልደቱ እንደ እኛ ሰው መሆንን የመረጠው ትሕትናን ለማስተማር ነበር። ዕብ. 4፥15

የማቴዎስ ወንጌል 2፥19-23 ላይም ፍጹም ትሑት የሆነ እግዚአብሔርን የሚወድና በእርሱ ፈቃድ የሚመላለስ ሰው እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ እንደሚረዳው፣ እንደሚመራውና እንደሚያግዘው ያስተምረናል።

የፃድቁ የቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት የሚያመላክተን ይህንኑ ነው ፤ ገና ከጅምሩ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከፀነሰችበት ጊዜ አንስቶ እግዚአብሔር ምን ማድረግ እንዳለበት ይነግረው ነበር በሕልሙ ይገልፅለት ነበር።  እርሱም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመላለስ ነበር።

ወደ ግብፅ እናቱንና ሕፃኑን ይዞ እንዲሄድ እንደነገረው አሁን ደግሞ ከግብፅ ወደ እስራኤል እንዲመለስ ነገረው። በዚህም በትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፈ 11፥1 ላይ ያለው የትንቢት ቃል ተፈፀመ ልጄን ከግብፅ እነዲወጣ ጠራሁት ይላል።

እኛም በሕይወታችን ለእግዚአብሔር ታማኞችና ታዛዦች ከሆንን እርሱን ከልባችን በማፍቀር በእርሱ እቅድ የምንመላለስ ከሆንን እሱ ሁሌም ከእኛ ጋር ይሆናል በለመለመው መስክም ይመራናል። መዝሙር 34፥7 ጀምሮ እንዲህ ይላል እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል ያድናቸዋልም እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው እናንተ ቅዱሳን እግዚአብሔርን ፍሩት እርሱን የሚፈሩት አንዳች አያጡምና አንበሶች ሊያጡ ሊራቡም ይችላሉ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጎድልባቸውም የላል። እንግዲህ እኛም ሁል ጊዜ ከእርሱ ጋር ድምፁን በመስማት በትሕትና የምንጓዝ ከሆንን የእርሱ በረከት ከእኛ ጋር ይሆናል። ለዚህም ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የብዙኃን እናት የሆነች ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ይህን የማያልቀውን ፀጋና በረከትን ታማልደን።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን 

15 January 2022, 18:27