ፈልግ

እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰማይ መሰላል ናት እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰማይ መሰላል ናት  (©CURAphotography - stock.adobe.com)

እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰማይ መሰላል ናት

“ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርሺ መሰላል ሆይ! ፍጥረት ሁሉ በአንቺ ታድሶአል” (አኰ. ቁር. ዘአግዚ ጐሥዓ)።“አንቺ ያዕቆብ ሌሊት በሕልም ያያት ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርስና የእግዚአብሔር መላአክት የሚወጡባትና የሚወርዱባት መሰላል ነሽ” (ውዳሴ ማር. ዘሠሎስ (የማክሰኞ ውዳ. ማር.)።

ኃጢአት ሳይመጣ በፊት በፍቅርና በወዳጅነት ጊዜ ወደ እግዚአብሔር መውጣትና ከእርሱ ጋር እንደ አባት መገናኝት ቀላል ነበር። እግዚአብሔር ራሱ በአትክልት ወደ ተሞላው ምድረ ገነት ወርዶ ከአዳምና ከሔዋን ጋር ይገናኝና ይወያይ ነበረ፡፡ በዚህ አስደሳች ሁኔታ የአዳምና የሔዋን ሕይወት በጣም የሚያስደስት መንፈሳቸውና ሐሳባቸው ከእግዚብሔር አምላካቸው ጋር ብቻ ነበረ። በእንደዚህ ያለ አስደሳች ኑሮ ምድራዊ ያልሆነ ሰማያዊ ሕይወት ያሳልፉ ነበረ፡፡ ኃጢአት ከመጣ በኋላ ግን እግዚአብሔር መጣላት፣ መራራቅ፣ መለያየት ጀመሩ፡፡

እግዚአብሔር ከአምላክ በመጀመሪያ ልጆቹ በደል እጅግ አዝኖ ከእርሱ አራቅቸው፣ ከምድረ ገነት አባረራቸው፣ ፊቱን አዞረባቸው። አዳምና ሔዋን ከአምላካቸው ጋር ተጣልተው ከአትክልት ምድረ ገነት ከተባረሩ በኋላ ይህ ነው የማይባል ጭንቀትና መከራ በተሞላበት አሳዛኝ ኑሮ ወደቁ፣ እንደገና ከፊጣሪያቸው ጋር ለመገናኘት ቸገራቸው።

ይህ በዚህ አንዳለ ግን እግዚብሔር ዘወትር መሐሪ ስለሆነና ሰውን በጣም ስለሚወደው ለሁልጊዜ ከእርሱ ርቆና ተለይቶ እንዲኖር አልፈቀደም፡፡ ለዘለዓለም ተሰውረው እንዲቀሩ አልፈለገም፡፡ ከእርሱ ጋር እንዲታረቁ ፈለገ፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ሁለቱንም የተጣሉ ወገኖች ሊያገናኝ የሚችል መካከለኛ አስተራቂ መንገድ መርጦ ማርያምን ፈጠረ። ሰው እንግዲህ በማርያም አማካይነት መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርስ እርሱም በዚህች የታደለች ጸጋ የሞላባት ፍጥረት ወደ ምድር እንዲወርድ የተቀደሰ ፈቃዱ ሆነ። በልዩ የአምላክ ብያኔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰማይንና ምድርን በፍቅር አንድ አድርጋ የምታገኝ ተአምራዊት መሰላል ሆነች። ፈጣሪና ፍጡር በእርስዋ አማካይነት ተቀራርበው፣ ተቃቅፈው ተሳስመው ለአንዴና ለመጨረሻ ዕርቅ ለማድረግ ተዘጋጁ፣ በዚህ ጥሩ አጋጣሚ በማርያም አማካይነት ከሰማይ ምሕረት ወረደ፡፡

በዚህች ምስጢራዊትና ተአምራዊ መሰላል በደለኛ የአዳም ልጆች አዳኝ ኢየሱስ በመካከላችን ተገኘ። “በኪሩቤልና በሱራፌል ላይ የሚኖር አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ ከማህጸንዋ ገብቶ ተቀመጠ። የሰው ወዳጅ በመሆን ወደ እርሱ አቀረበን፣ ሞታችንን ወስዶ ሕይወትን ሰጠን” (ውዳ. ማር. ዘዓርብ)።

ከምድር ወደ ሰማይ የምትደርሽ መሰላል በአንቺ ሁሉ ፍጥረት ታድሶአል፡፡ ሰማያዊት መሰላል በሆነች በእመቤታችን ድንግል ማርያም አማካይነት የአዳም ተስፋ ወደ ሰማይ ደረሰ፡፡ የሰው ፍጥረት ከኃጢአት ጉድጓድና አዘቅት ወጥቶ ወደ ላይ ከፍ አለ፡፡ ተመልሶ ሰማያዊ ሕይወትን በመልበስ ከአምላኩና ከፈጣሪው የሰላምን ድርድር አደረገ፤ እስከ ዘለቄታው ቋሚ ሰላምን መሠረተ። በማርያም አማካይነት እውነተኛ መድኃኒት መጣልን፡፡ እርሱም መንፈሱን ሰጠን፤ በማርያም በኩል የሰማይ ደጃፍ ተከፈተልን። ይህችን የደኀንነት መሰላል ምን ጊዜም ቢሆን እንርሳ፡፡ በእርስዋ በኩል ተረማምደን ወደ ተወደደው ልጅዋ እንውጣ፣ ምሕረትንና ጸጋን አለምን፣ በእርስዋ ጸሎታችንን ወደ ሰማይ እናሳርግ፡፡ እንግዲህ ወደ ሰማይ መድረስና መንግሠተ ሰማያትን ለመውረስ ከፈለግን በሰማያዊት መሰላል በማርያም እንውጣ፡፡

24 January 2022, 11:49