ፈልግ

ሊባኖስ ለክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት በተጀመረበት ወቅት፣ ሊባኖስ ለክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት በተጀመረበት ወቅት፣ 

ፓትርያርክ ሚናሴ፣ በሊባኖስ ውስጥ የክርስቲያኖች አንድነት ታላቅ ምስክርነት መሆኑን ገለጹ

የአርመንያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሩፋኤል ቤድሮስ ሚናሴ 21ኛ፣ ጥር 8/2014 ዓ. ም. በቤይሩት በሚገኘው በቅዱሳን ኤሊያስ እና ጊዮርጊስ ካቴድራል ተገኝተው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ባስጀመሩበት ወቅት፣ በአርመኒያ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት አወድሰው፣ ራስ ወዳድነት በክርስቲያኖች መካከል ያለውን አንድነት የሚያደናቅፍ ከባድ ኃጢአት መሆኑን ገልጸው፣ በሊባኖስ ውስጥ የታየው የክርስቲያኖች አንድነት በሌሎች አገራት ለሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ትልቅ ምስክርነት መስጠቱን ገልጸዋል። ብጹዕ ፓትርያርክ ሚናሴ አክለውም "እርስ በእርስ እንድንቀራረብ የሚረዳን ብቸኛው መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር የምንነጋገርበት የጸሎት መንገድ ነው" ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ክርስቲያኖች በምድራችን ውስጥ ተበታትነው፣ በግል እና በቡድን ራስ ወዳድነት ውስጥ በመውደቅ ጌታቸውን እየረሱ ይገኛሉ” በማለት የአርመንያው ካቶሊካዊ ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ሩፋኤል ቤድሮስ ሚናሴ 22ኛ ባለፈው እሁድ በቤይሩት በሚገኘው የቅዱሳን ኤልያስ እና ጊዮርጊስ ካቴድራል ተገኝተው በክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ንግግራቸው ገልጸዋል።

አንድነትን የሚከለክሉ ጥልቅ ቁስሎች

አብያተ ክርስቲያናቱ ዛሬም ቢሆን እየኖሩት ላለው መከራ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ፓትሪያርኩ፣ ለዘመናት የዘለቁ ጥልቅ ቁስሎች በክርስቲያኖች መካከል ከባድ ህመምን እንዳስከተሉ ገልጸው፣ እግዚአብሔር ወደ ፈቀደው አንድነት ለመመለስ በጸሎት መተባበር  እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በቤይሩት ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው የፓትርያርኩን ንግግር ከተከታተሉት ፓትርያርኮች፣ ጳጳሳት፣ ካህናት እና በቤይሩት የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች መካከል የማሮናውያን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ቡትሮስ ፒየር ራኢ፣ የመልቃውያን ፓትርያርክ ሊቀ ጳጳሳት ዩሱፍ አብሲ፣ በአንጾኪያ የሶርያ-ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ዩሱፍ ዮናን እና በሊባኖስ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ሊቀ ጳጳስ ሞንሲኞር ጆሴፍ ስፒተሪ መሆናቸው ታውቋል።

የሳምንቱ አስተንትኖ ሃሳብ

ዋና ጽሕፈት ቤቱ በቤይሩት ከተማ የሚገኝ የመካከለኛው ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ለዘንድሮ ዓመት የመረጠው የአስተንትኖ መሪ ሃሳብ ከማቴ. 2:2 የተወሰደ እና ሰብአ ሰገል፣ “ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ለእርሱ ልንሰግድለት መጣን” የሚል መሆኑ ታውቋል። ለክርስቲያኖች አንድነት ጸሎት የተመረጠው ጭብጥ እውነት ነው ያሉት ብጹዕ ፓትርያርክ ሚናሴ፣ “ዛሬ እኛ ሰብአ ሰገል ስለሆንን ክርስቶስን በመፈለግ ላይ እንገኛለን” ብለው፣ ሕፃኑ ኢየሱስን፣ ፈጣሪያችንን፣ መለኮታዊ ክብሩን ትቶ ወደ ዓለም በመምጣት እኛን ሊያድነን እና ከእግዚአብሔር ጋር ሊያስታርቀን መፈለጉን አስረድተዋል። በመሆኑም ኮከቡ መንገዳችንን እንዲያበራ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ብርሃን አንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለዋል። አክለውም “እኛ ይህንን መንገድ፣ ይህንን እውነት እና ይህንን ሕይወት ስንፈልግ ጌታ በቤተክርስቲያን በኩል በሰጠን ብርሃን የምንመላለስ ሰብአ ሰገል ነን” ብለዋል።

ኃጢአታችን ሁል ጊዜ በፊታችን እና በዓይናችን ፊት ይገኛል ያሉት ብጹዕ ፓትርያርክ ሚናሴ፣ የክርስቲያኖችን አንድነት የሚያሳድጉ ብዙ መልካም ሀሳቦችን ማቅረብ እና መናገር የሚቻል መሆኑን አስረድተው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሉት ወደ እግዚአብሔር የምናቀርባቸው መስዋዕትነቶች፣ ክፋቶች፣ እና የምናሳያቸው ትዕግስቶች እንደ መንገዶች በብሉይ ኪዳን ለእግዚአብሔር እንደቀረቡ መስዋዕቶች ናቸው ብለዋል። ህመሞቻችን እና ስቃዮቻችን በሙሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን የምንቀበልባቸው ስጦታዎች ናቸው ብለው፣  ደካማነታችንን ስለምናውቅ፣ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን አንዳችን ለሌላው መኖር እንድንችል ጌታ እንዲረዳን እንጠይቃለን ብለዋል።

ስለዚህ ጌታን በጸሎት ልንጠይቀው እና በፊቱ ግልጽ አድርገን በትህትና፡- እኔ ኃጢአተኛ ነኝ፣ ደካማ ነኝ፣ ለወንድሜ ግልጽ መሆን እንድችል ያንተን እርዳታ እጠይቃለሁ፣ ወንድሜም ራሱን ግልጽ የሚያደርግበት ድፍረት እንዲኖረው እና የሕይወት ግባችን ወደ ሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅር እንቀርባለን ብለዋል። ብጹዕ ፓትርያርክ ሚናሴ በአስተንትኖአቸው ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት፣ “ሁሉም ፓትርያርኮች፣ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በተገኙበት በዚህ የጋራ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ መናገር የፈለኩት ሃሳብ፣ በእነዚህ ዘመናት ውስጥ አንዳችን ወደ ሌላው መቅረብ አለመቻላችንን ነው” ብለዋል።

በሊባኖስ ውስጥ በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ አዎንታዊ ድምጽ መሰማቱ የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሆነ ብጹዕ ፓትርያርክ ሚናሴ ገልጸው፣ ለዚህ ብርሃን እና አንድነት እግዚአብሔርን አመስግነዋል። በሊባኖስ የሚገኙት ቀሳውስት እና የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮችን ብቻ በተጋበዙበት ሥነ ሥርዓት ላይ ምእመናንም መገኘታቸውን ገልጸው፣ በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው የሊባኖስ ሕዝብ ​​በሚገኝበት የስቃይ ወቅት ይህ መከናወኑ እንደ ተአምር ሊታይ እንደሚችል ካስረዱ በኋላ በተጨማሪም በመካከላችን የእግዚአብሔር መገኘት ለሌሎች ምስክርነት ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

20 January 2022, 16:13