ፈልግ

ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ለማየት በኮከብ እየተመሩ ከአገራቸው ወጥተው ሄዱ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ለማየት በኮከብ እየተመሩ ከአገራቸው ወጥተው ሄዱ   (©zatletic - stock.adobe.com)

ሰብአ ሰገል

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማሕበረሰቦች ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን የተወለደበት ቀን የሚከበርበት የገና በዓል በታሕሳስ 16/2014 ዓ.ም ተክብሮ ማለፉ የሚታወቅ ሲሆን አሁንም የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማሕበረሰቦች ዘንድ  በታኅሳስ 28/2014 ዓ.ም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አህዛብን ለሚወክሉ ለሰብአ ሰገል የተገለጠበት እለት እንደ ሚከብር ይታወቃል። በማቴዎስ ወንጌል 2፡1-12 ስለዚህ መገለጽ እንዲህ በማለት ያቀርባል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።  ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤ የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። 

እነርሱም “አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና” ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት።  ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፥ ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው።

እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር።  ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም ቀረቡለት።  ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ (ማቴ 2፡1-12)። 

ሰብአ ሰገል

ሰብአ ሰገል ከምስራቅ የመጡ የከዋክብት ተመራማሪዎች ጠቢባን ናቸው። ከክርስቶስ ልደት በፊት ብዙ ዘመናት ነቢዩ ኢሳይያስ ክርስቶስ ከተወለደ አይሁዳውያን ብቻ ሳይሆኑ አረማውያንም ጭምር እንደሚሰግዱለት በትንቢት ቃሉ አብራርቶ ተናግሮ ነበር፡፡ “ኢየሩሳሌም ሆይ ተነሺ መብራትሽን አብሪ ብርሃንሽ መጥቶአልና፡፡ የእግዜአብሔር ክብር በአንቺ ላይ በራ፡፡ ሕዝቦችና ነገሥታት በብርሃንሽ ይራመዳሉ፤ ከሳባ ወርቅና ከርቤ ይዘው ሊመጡ ነው፤ የእግዚብሔርን ደኀንነት ሊናገሩ ነው እያለ እየሩሳሌምን በተስፋ መድኃኒት ያጽናናት ነበረ (ኢሳያስ 60፡ 1-3)። ኢየሱስ ተወልዶ እንደ ሙሴ ሕግ ወደ ቤተመቅደስ እንዲቀርብ በሄደ ጊዜ ቅዱስ ስምኦን ይህ ሕፃን ለዓለም ሕዝቦች ብርሃን እንደሚሆን አስቀድሞ በትንቢት ተናገረ (ሉቃ. 2፣32)። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ መጀመሪያ እረኞች ቀጥሎም ሰብአ ሰገል የተባሉ የክዋክብት ተመራማሪዎች ጠቢባንና አዋቂ ሰዎች የዓለምን ንጉሥ እጅ እንዲነሱ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መጡ (ማቴ. 2.1-12)።

እረኞቹ በመልአኩ ቃል ሰብአ ሰገል ግን በተአምራዊው ኮከብ ተጠርተውና ተመርተው መጡ። እነርሱ እግዚአብሔር ከጠራቸው በኋላ የመንገዳቸውን ችግር ሳያስቡ ቤተሰቦቻቸውን፣ አገራቸውንና ጉዳያቸውን ትተው ትልቅነታቸውን ረስተው የአምላክን ልጅ ለማክበር ይሉኝታ ሳይፈሩ በፍጥነት ከአገራቸው ተነስተው ወደ ሩቅ አገር ሄዱ፡፡ ሰብአ ሰገል ራስህንና ጉዳይህን ትተህ እንዴት አድርገህ አምላክን እንደምታስብና እንደምታገለግል እርሱ ሲጠራህ በጥፍነት መልስ መስጠት እንሚያስፈልግ ያስተምሩናል፡፡ እግዚአብሔርን የሚወዱ የማያደርጉትና የማይደርሱበት የላቸውም፡፡ እርሱን ለማስደሰት ሲሆን ችግር ምን መሆኑን አያውቁም፡፡

እግዚአብሔር በብዙ መንገድ ቃሉን ሲያሰማን በሹክሹክታ ሲነግረንና ሲገልጥልን ፈቃዱን ሲያስታውቀን እንዴት አድርገን ተቀብለን እንመልስለታለን? እንደ ሰብአ ሰገል በደስታና በፍጥነት ወይስ በሃኬትና በመዘንጋት ወይም የባሰ አውቀን ዝም እንላለን? እዚህ ላይ ተመልሰን ያለፈ ሕይወታችንን እንመርምርና ተገቢውን መልስ እንስጥበት፡፡ የከዋክብት ተመራማሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም እንደገቡ ወደያው “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት አለ፣ በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጣን እያሉ ስለ ኢየሱስ ጠየቁ (ማቴ 2፣2)፡፡ በሁሉ ዘንድ ፈለጉት የእግዚአብሔርን ፍላጐትና ምኞት ያላቸው ስለሆኑ ሁሉን ነገር ረስተው በልባቸው ይፈልጉታል፣ ሳያገኙተም አያርፉም፡፡ እኛስ እንደዚህ ያለ የአምላክ ምኞት አለን ወይ? እስቲ ረጋ ብለን እናስተውል ልባችንን ጠንቀቅ ብለን እንመርመር።

ሰብአ ሰገል በግንበራቸው ተደፍተው ሰገዱለት፡፡ ያመጡትንም እጅ መንሻ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ አቀረቡለት። እኛስ ኢየሱስን ሰናገኝ እንደዚህ እንደሰታለን ወይስ እንደ ድሮአችን ቀዝቃዛዎች ሆነን እንቀራለን? በቅዱስ ቁርባን ስንቀበለው ስንት ጊዜ በቀዝቃዛነትና በቸልተኛነት እንቀበለዋለን? ይህን የሚያሳዝን መንፈስ ጐዶሎነት ይዘን እንጠብቀዋለን። እንዴት ያለ የሰብአ ሰገል መንፈሳዊነትን እንልበስ፤ አንደ እነርሱ የሚቃጠል የአምላክን ፍቅር በልባችን ውስጥ እናሳድር በፍቅሩ ተስበን በሁሉም ስፍራ በታላቅ ምኞች እንፈልገው።

05 January 2022, 12:33