ፈልግ

ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የ2014 ዓ/ም የልደት በዓልን በማስመልከት ለመላው ምዕምናን ያስተላለፉት መልዕክት  ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የ2014 ዓ/ም የልደት በዓልን በማስመልከት ለመላው ምዕምናን ያስተላለፉት መልዕክት  

ካርዲናል ብርሃነየሱስ የልደት በዓልን በማስመልከት ለመላው ምዕምናን ያስተላለፉት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን “እርሱ የእግዚአብሔር ባሕርይ ኖሮት ሳለ እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር እኩልነትን እንደመነጠቅ አድርጐ አልቆጠረውም፤ ነገር ግን እንደ ሰው ሆኖ በመወለድ የባርያን መልክ ይዞ ራሱን ባዶ አደረገ” (ፊሊ. 2፡6-7)

ብፁዓን ጳጰሳት

ክቡራን ካህናት፤ገዳማውያንና/ውያት

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ምእመናንና ሕዝበ እግዚአብሔር

በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ

ክቡራትና ክቡራን

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  ክርስቲያኖች በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የ2014 ዓ.ም የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን።

ዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ደህንነት ሲል ራሱን በማዋረድ መለኮታዊ ክብሩን ትቶ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ለብሶ፣ ሰው ሆኖ ተወልዷል ። በእግዚአብሔርና በሰው መሐል ድልድይ ሆኖ መጣ። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ በሰው ምሳሌ ሆኖ ሰለተወለደ አስታራቂያችን ሆኖልናል ።

“ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡን የሚመሰክር መንፈስ የእግዚብሔር መንፈስ ነው” (1ዮሐ. 4፡2)። እግዚአብሔር እኛን ልጆቹን ስላፈቀረን ልጁን ላከልን፣ በእርሱም አማካኝነት ሕይወት እንድናገኝ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል። እኛም  በእግዚአብሔር መንፈስ ተጎበኘን፣ ፍቅርንና መንፈሳዊ ሃብትን በልባችን አፈሰሰ፣ እርሱ ስለወደደን ኃጢያታችን እንዲደመሰስ ልጁን ላከልን በእርሱም በኩል ልጆቹ አደረገን ።

የእግዚአብሔር ብርሃን የሆነው ክርስቶስ አዳኛችን ነው። እርሱ በመምጣቱ የሰማይን ቤት ለሰዎች ሁሉ ከፍቷል፣ ማረፊያውም ክቡር ነው። እርሱ የአዳምን ኃጢያት በመደምሰስ የሰማይ የገነትን በር ከፍቶልናል፣ ምሕረቱም ታላቅ ነው። ሰዎችን ሁሉ ከተበተኑበት ለመሰብሰብና  ለማዳን መጥቷል። ከልብ የሚቀበሉትም ከእርሱ ጋር የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ክርስቶስን የተቀበሉትና ዛሬም የሚቀበሉት ከልብ የዋህና ትሑት የሆኑት ሕዝቦች ናቸው። እነርሱ በእርሱ ብቻ ይታመናሉ ትእዛዙንም ይፈፅማሉ።  ነብዩ ሶፎንያስ  “በምድር የምትኖሩ እናንተ ትሑታን ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ ደግ ሥራ ሥሩ በእግዚአብሔርም ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ ይላል” (ሶፎ. 2፡3)። እኛም ነብዩ እንደ መከረን፣ ከልብ የዋህና ትሁት የሆነው ክርስቶስ መልካም ሰዎች እንዲያደርገን አጥብቀን እንለምነው።

ቅዱስ ጳውሎስ ስለክርስቶስ ሲያስተምረን “ክርስቶስ ለማይታየው እግዚአብሔር እውነተኛ ምሳሌ ነው ይላል“። (ቆላ. 1፡15) አያይዞም የእግዚአብሔር የበኩር ልጅ፣ ከሁሉ ነገር በፊት የነበረ፣ የማዕዘን ራስ፣ የሰላም ንጉስ የሚሉና የመሳሰሉ ስሞችን ሰጥቶታል።

ክርስቶስ የመጣው ለእኛ ነው እንጂ ለእርሱ ጥቅም አይደለም። ይልቁንም እኛ ከእርሱ ጋር የሰማይ አባታችን ልጆች እንድንሆንና ምሕረትንም ከእኛ ጋር ለማካፈል ይፈልጋል። ስለዚህ ልባችን በደግነትና በምሕረት እንዲሞላን በሙሉ ልባችን ወደእርሱ እንጠጋ፣ እራሳችንንም እናቅርብለት፤ የይቅርታ፣ የሰላም መንፈስን እንዲሰጠን እንለምነው።

እኛ ሰዎች በሕይወት ብርሃን ለመኖር ማንንም ሳንጠላ ሁላችንም እርስ በእርሳችን ልንዋደድ ያስፈልገናል። እግዚአብሔር በመልኩ የፈጠረን ሰዎች ሁሉ በተፈጥሮ አንድ በመሆናችን እያንዳንዱ ሰው የተፈጥሮ ወንድሙንና እኅቱን እንደራሱ አድርጎ እዲወድ ታዞአል። 

የፍቅር አምላክ አገራችንንና ሕዝቧን በምሕረቱ ተመልክቶ ችግሮች ተወግደው ሰላማዊ ኑሮ ለመኖር ከመጥፎና ከክፋት ሥራ በመራቅ አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ ይገባናል። ሰላምና ደስታ የሚገኘው በጸሎት ነውና ለጸሎት ተግተን እንቁም። ይህንን ስንፈፅም እግዚአብሔርን በመፍራትና ከክፉ ሥራ ሁሉ በመራቅ ነው። እኛ ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን። ሐዋርያው ጳውሎስ  “ሰላማችን ክርስቶስ ነው ሁላችንም በአንድ መንፈስ ተመርተን ወደ አብ እንቀርባለን ይላል”። (ኤፌ. 2፡17-18)  የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ በልባችን ሰላምን ይፈጥራል።  ሰላም ወርቅ ነው፤ እንደ ወርቅም ተጠንቅቀን መጠበቅ አለብን።  በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በኢትዮጵያ ሰላም የደፈረሰ ቢሆንም እና ጦርነትን ቢያስከትልም ጌታ በቸርነቱ በቃ ብሎ እንዲያቆምልንና ሰላሙን እንዲሰጠን በመማፀን እኛም የሰላምን ሰንሰለት ከሚበጥሱት ከትዕቢት፣ ከጥላቻ፣ ከኩራትና ከቁጣ መንፈስ መራቅ ያስፈልገናል። የእነዚህ ነገሮች ደግሞ መድኃኒት በትሕትና፣ በየዋህነትና በትዕግስት ክፉውን ማለፍ መቻል ነው። በእነዚህ ስንደገፍ ነው መፈቃቀር የምንችለው። በይቅር ባይነት መንፈስ አብረን መጓዝ እንድንችል በሙሉ ልባችን ወደ እርሱ እንመለስ።

መላዕክት እግዚአብሔርንም እያመሰግኑ፣ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፣ ሰላምም ደስ በሚሰኝባቸው ሰዎች መካካል በምድር ይሁን” አሉ (ሉቃ. 2፡13-14)።           

የተወደዳችሁ ምዕመናን በዚህ የልደት ጊዜ ከመላዕክት ጋር በኢየሱስ ልደት ስንደሰት በጦርነት፣ በስቃይና በመከራ ላይ ያሉትን፣ የተጨነቁትንና የሞራል ስብራት የደረሰባቸውን፣ ከቤታቸው የተፈናቀሉትንና ጉዳት የደረሰባቸውን፣ ወላጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡትን በማሰብ ስቃይና ሐዘናቸውን በመካፈል የአምላካችንን አብነት እንፈፅም።  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ

“ከእነዚህ ከወንደሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁ ነው ይላልና።” (ማቴ. 25፡40) ።

በመጨረሻም ለማላው ኢትዮጲያዊያንና በጎ ፈቃድ ላላችሁ በሙሉ፣ በህመም ደዌ ተይዛችሁ በየሆሰፒታሉና በየቤታችሁ የምትገኙ ህሙማን፣ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ የሕግ ታራሚዎች፣ በተለያየ ደረጃና መስክ አገርንና ህዝብን የምታገለግሉ፣ እንደዚሁም በጦርነትና በግጭት ቀጠና መካከል ያላችሁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ በሀገር ውስጥና በውጭ በስደት ላይ የምትገኙ ወገኖች፣ እንዲሁም ከቤታችሁና ከአካባቢያችሁ የተፈናቀላችሁ በሙሉ እንኳን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን እገልጽላችኋለሁ።

  እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን አገራችንን ይባርክልን ይጠብቅልን !

የሰላሙ ንጉሥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላሙን ይስጠን ! አሜን !!

 

† ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሰቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት

06 January 2022, 20:54