ፈልግ

ወደ 9 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍጋኒስታኖች ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል ወደ 9 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍጋኒስታኖች ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል 

የአውስትራሊያ ብጹዓን ጳጳሳት መንግሥት ተጨማሪ ስደተኞችን እንዲቀበል አሳሰቡ

የአውስትራሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በአገሪቱ ከሚገኙ ሌሎች የእምነት ተቋማት እና ሕዝባዊ ማኅበራት ጋር በመተባበር፣ መንግሥታቸው በአሁኑ ጊዜ ስደተኞችን ለማገዝ የሚያደርገው ጥረት በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፣ የታሊባንን አስተዳደር ሸሽተው ወደ አውስትራሊያ ለሚመጡ የአፍጋኒስታን ስደተኞች በጎ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአውስትራሊያ መንግሥት በዚህ ሳምንት ውስጥ ባወጣው መግለጫ፣ በሰብአዊ እርዳታ እና የቤተሰብ ቪዛ መርሃ ግብር አማካይነት በአራት ዓመታት ውስጥ አፍጋኒስታንን ለቀው የተሰደዱ 15,000 ሰዎችን ተቀብሎ ማስተናገዱን አስታውቋል። ነገር ግን በአውስትራሊያ ውስጥ በኢየሱሳዊያን ማኅበር የሚመራ ካቶሊክ አልያንስ የተሰኘ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መርጃ ድርጅት፣ የአውስትራሊያ መንግሥት ስደተኞችን ለመርዳት እስካሁን ያደረገው ጥረት በቂ እንዳልሆነ ገልጾ፣ ቢያንስ ለ20,000 ተጨማሪ ስደተኞች ቦታ እንዲያዘጋጅ ጠይቋል።

ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት

“የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት የጠቀሰው የ15,000 ስደተኞች ቁጥር በየዓመቱ ከሚቀበላቸው 13,750 ስደተኞች ጋር እንዲካተት እና ደህንነት ፍለጋ ከአፍጋኒስታን ለሚሰደዱ ሰዎች መንግሥት ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ በማለት በአገሪቱ ውስጥ ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ዕርዳታን የሚያቀርብ የኢየሱሳዊያን ማኅበራዊ አገልግሎት ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሳሊ ፓርኔል ተናግረዋል። ሥራ አስፈጻሚዋ አክለውም፣ "የአውስትራሊያ መንግስሥት በአፍጋኒስታን ያለውን ወቅታዊ ቀውስ ሸሽተው ለሚሰደዱ ሰዎች አስቸኳይ ሰብአዊ ዕርዳታን ከማድረግ በተጨማሪ በአውስትራሊያ ውስጥ ላሉ ሰዎች ደህንነት ቅድሚያን በመስጠት፣ ቤተሰቦቻቸውን በመደገፍ እውነተኛ አመራርን የማሳየት ዕድል አለው" ብለዋል።

ተግባራዊ ርህራሄን ከፍ ይበል!

በኢየሱሳዊያን ማኅበር የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አገልግሎት ለመንግሥት ያቀረበው ጥያቄ በአውስትራሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኩል ድጋፍ ማግኘቱ ታውቋል። "በአፍጋኒስታን ውስጥ ያለው የሰብአዊ ቀውስ መጠን በአውስትራሊያ ያለው የሰብአዊ ዕርዳታ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ተጨማሪ ቦታዎችን በአስቸኳይ እንዲያዘጋጅ ይጠይቃል" በማለት በጳጳሳቱ ጉባኤ የማኅበራዊ ፍትህ፣ ተልዕኮ እና አገልግሎት ኮሚሽን ሊቀመንበር የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቪንሰንት ሎንግ ተናግረዋል። አቡነ ቪንሰንት አክለውም፣ አሁን ባሉ ዕቅዶች ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጥባቸውን ነገሮች ማስተካከል ብቻ ሳይሆን” ተግባራዊ ርኅራኄአችንን ማሳደግ አለብን በማለት አሳስበዋል።

9 ሚሊዮን አፍጋኒስታውያን ለስደት ተዳርገዋል

አፍጋኒስታኖች በዓለም ላይ ካሉት ትልቅ የስደተኞች ቁጥር መካከል አንዱ መሆናቸው ሲነገር፣ ምንም እንኳን ዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን ካስወጣች በኋላ እ. አ. አ በነሐሴ ወር 2021 ዓ. ም. ታሊባኖች አገሪቱን ሲቆጣጠሩ ጦርነቱ ጋብ ያለ ቢመስልም ፍርሃት፣ ሁከት እና የመሠረታዊ ቁሳ ቁሶች እጦት አፍጋኒስታኖች ከድንበር አልፈው በተለይም በአጎራባች ኢራን እና ፓኪስታን ጥገኝነት እንዲጠይቁ ማስገደዳቸው ታውቋል። ከ2.2 ሚሊዮን በላይ የተመዘገቡ የአፍጋኒስታን ስደተኞች፣ ሌሎች 4 ሚሊዮን በተለያየ ደረጃ ወደ ውጭ አገራት የተሰደዱ እና 3.5 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ መኖራቸው ታውቋል።

ረሃብ

በአጠቃላይ ወደ 9 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍጋኒስታኖች ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ የተገደዱ ሲሆን፣ ሀገሪቱ አሁን በረሃብ አፋፍ ላይ መሆኗ አፍጋኒስታንን በዓለም ላይ ትልቁ ሰብአዊ ቀውስ የሚታይባት አገር አድርጓታል። ባለፉት አሥርተ ዓመታት የተከሰተው አስከፊ ድርቅ እና ታሊባን ኢኮኖሚውን ከተቆጣጠረ በኋላ ከሃያ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አፍጋናውያን በረሃብ እንደሚሰቃዩ ታውቋል። በአፍጋኒስታን ውስጥ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ መኖሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው ዘገባ አስታውቋል።

29 January 2022, 15:24