ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ ከሐይማኖት መሪዎች ጋር በተገናኙበት ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ ከሐይማኖት መሪዎች ጋር በተገናኙበት ወቅት  (AFP or licensors)

ሊቀ ጳጳስ ቤርናርድ፣ የክርስቲያኖች የኅብረት ጉዞ ወደ አንድነት የሚመራ መሆኑን ገለጹ

ዘንድሮ ከጥር 10-17/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረውን የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ምክንያት በማድረግ ሃሳባቸውን ያካፈሉት የካቶሊክ እና የአንግሊካን አብያተ ክርስቲያናት ግኑኝነት ተባባሪ ሊቀመንበር ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ቤርናርድ ሎንግሊ፣ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ወደ ሙሉ አንድነት እንዲደርሱ የሚያግዙ በርካታ ሥራዎች መከናዎናቸውን ተናግረው ወደ ግብ ለመድረስ አሁንም ረጅም መንገድ የሚቀራቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በክርስቲያኖች መካከል የጠበቀ ግንኙነት እና መግባባት በመፍጠር አንድነት የሚያሳድጉ መሠረታዊ መንገዶች ወዳጅነት፣ አስተንትኖ፣ ጸሎት እና የጋራ ምስክርነት መሆናቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ ገልጸዋል። በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና በአንግሊካን ኅብረት መካከል የጋራ ዓለም አቀፍ ምክር ቤት የተመሠረተው እ. አ. አ በ1969 ዓ. ም. ሲሆን ዓላማውም በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድነትን የሚያሳድጉ መንገዶችን በጋራ ለመፈለግ መሆኑ ይታወሳል።

ዘንድሮ ከጥር 10-17/2014 ዓ. ም. ድረስ በሚከበረው ዓመታዊ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ላይ በማስተንተን የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ ሃሳባቸውን አካፍለዋል። እስከ ጥር 17/2014 ዓ. ም. ድረስ በሚካሄደው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ውስጥ፣ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ በርካታ ምዕመናን በጥምቀት ያገኙትን ክርስቲያናዊ አንድነት ለማሳደግ ጸሎት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ለዘንድሮ የቀረበውን የጸሎት ሃሳብ በጋራ የመረጡት የመካከለኛው ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት እና በጳጳስዊ ምክር ቤት የክርስቲያኖችን አንደነት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መሆናቸው ታውቋል። ዋና ጽሕፈት ቤቱ ቤይሩት ከተማ የሚገኝ የመካከለኛው ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ለዘንድሮ ዓመት የመረጠው የአስተንትኖ መሪ ቃል ከማቴ. 2:2 የተወሰደ እና ሰብአ ሰገል፣ “ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ለእርሱ ልንሰግድለት መጣን” የሚል መሆኑ ታውቋል። መሪ ቃሉ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ያላሉበት ሁኔታ በመግለጽ ግንዛቤን ለማስጨበጥ የሚረዳ መሆኑ ታውቋል።

የኅብረት ጉዞ

ዘንድሮ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቆይታን ያደረጉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ ሎንግሊ፣ በእንግሊዝ ውስጥ በሚገኝ ሀገረ ስብከታቸው፣ “የበርሚንግሃም አብያተ ክርስቲያናት አንድነት” በሚል የጋራ ተነሳሽነት ከኦርቶዶክስ፣ ከቢዛንታይን እና ከምሥራቃውያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ግንኙነት በመፍጠር መንቀሳቀሳቸውን ገልጸዋል። ይህ የጋራ እንቅስቃሴያቸው ስለ አብያተ ክርስቲያናቱ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደረዳቸው ገልጸው፣ በምሥራቅ ቤተክርስቲያ፣ በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም እና በአጎራባች አገሮች ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ቀጣይነት ሕይወት፣ ታሪክ፣ አስተዋጽዖ እና ጠቀሜታን በሚገባ ለማወቅ ያስቻላቸው መሆኑን አስረድተዋል። የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን በሕይወት ያቆዩት ታሪኮች በክርስቲያን ቤተሰቦች ሕይወት ውስጥ በግልጽ እንደሚታይ አስረድተው ነገር ግን በቀጣናው የሚገኙ በርካታ አገራትን እያጋጠመ ያለው ትልቁ ፈተና ስደት መሆኑን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ ጠቁመዋል።

ሲኖዶሳዊነት እና የክርስቲያኖች አንድነት

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ እና በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ ጥቅምት 18/2014 ዓ. ም. በመላው ዓለም ለሚገኙ የክርስቲያኖች አንድነት እንቅስቃሴ አስተባባሪ ብጹዕን ጳጳሳት ባቀረቡት ሃሳብ፣ ሲኖዶሳዊነት እና የክርስቲያኖች አንድነት አብረው የሚከናወኑ ሂደቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ የክርስቲያኖችን አንድነት እንደ ስጦታ መለዋወጥ ስለሚረዳ፣ ካቶሊኮች ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር መለዋወጥ ከሚችሏቸው ስጦታዎች መካከል አንዱ በሲኖዶሳዊነት ያላቸውን ልምድና ግንዛቤ ነው ብለዋል። “ሲኖዶሳዊ ጎዳና” በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና ቤተ ክህነታዊ ማኅበረሰቦች ውስጥ ሰፊ ፍላጎት መቀስቀሱን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ ሎንግሊ፣ “የሲኖዶሳዊ ጉዞ ፍሬ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ምን ሊሆን እንደሚችል፣ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ልምድ ለመመልከት እና ከሲኖዶሳዊ ጉዞ ለመማር ግልጽነት ያለው ትልቅ ፍላጎት መኖሩን የሚያመለክት መሆኑን አስረድተዋል።

የተጓዙበት መንገድ እና የወደፊት ጉዞ

ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ አስቀድሞ የተጀመረ የክርስቲያኖች አንድነት ጉዞ አካል ሆና መቆየቷን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ፣ “የዚህን ረጅም ጉዞ የመጀመሪያ ቀናት ሁላችንም የምናስታውሰው ነው ብለው፣ ይህ ከፊታችን በግልጽ የሚታየው ጉዞ የተሟላ ግብ ያለው የአንድነት ጉዞ መሆኑን አስረድተዋል። በክርስቲያኖች የአንድነት መንገድ ላይ አብያተ ክርስቲያናት ምን ያህል ርቀት እንደሄዱ የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ፣ ክርስቲያናዊ አንድነት በመጀመሪያ ደረጃ በውስጣችን ያለው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው” ብለዋል። አክለውም፣ በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ ረጅም መንገድ ተጉዘናል ብለው፣ ላለፉት ስልሳ ዓመታት የተጓዙበትን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የክርስቲያኖች አንድነት ጉዞን በማሰላሰል፣ የክርስቲያኖች አንድነት ጉዞ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕይወትና የዘወትር ተስፋ አካል መሆኑን አስረድተዋል። አሁንም በጋራ የምንጓዝባቸው ረጅም የክርስቲያኖች የአንድነት መንገዶች እንዳሉ ሊቀ ጳጳሱ ገልጸው፣ በኅብረት በተጓዝን ቁጥር ስለራስ እና ስለሌላው የበለጠ ማወቅ እንደሚቻል እና ስለሚገጥሙን አንዳንድ ተግዳሮቶች የበለጠ ክፍት መሆን እንደሚቻል አስረድተዋል።

የጸሎት እና የምስጋና ሳምንት

ዓመታዊው የጸሎት ሳምንት “በእርግጥ አስፈላጊ ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ፣ “በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት መርሃ ግብር እና ንቃተ ህሊና ውስጥ ጠልቆ የገባ” መሆኑን ገልጸው፣ ተነሳሽነቶችን ለመቀስቀስ፣ ለመጸለይ እና በጋራ ለመሰብሰብ እድሎችን የሚሰጥ በመሆኑ ለአጋጣሚው ያላቸውን አድናቆት፣ በእንግሊዝ የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናርድ ሎንግሊ ገልጸዋል።

24 January 2022, 14:49