ፈልግ

በቆጵሮስ የማሮናይት ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን በቆጵሮስ የማሮናይት ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን 

የቆጵሮስ ቤተክርስቲያን የቅዱስነታቸውን ጉብኝት በደስታ እንደምትጥብቀው አስታወቀች

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከኅዳር 23 – 27/2014 ዓ. ም. ድረስ በቆጵሮስ እና በግሪክ የሚያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ የሁለቱም አገራት ምዕመናን በደስታ፣ በፍቅር እና በአንድነት ስሜት እንደሚጠባበቁ ክቡር አባ ኢብራሂም ኪታ ከቆጵሮስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በሰላም እና በፍቅር የተሞላ አዲስ ሕይወት ያግናጽፈናል በማለት በቆጵሮስ የማሮናይት ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካኅን ክቡር አባ ኢብራሂም የምዕመናኖቻቸውን ስሜት በመጥቀስ አስታያየታቸውን ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንስችስኮስ በቆጵሮስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲያጠናቅቁ ወደ ሮም ከመመለሳቸው በፊት በግሪክም እንደዚሁ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ-ግብር አመልክቶ፣ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው 35ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት መሆኑን መርሃ-ግብሩ አስታውቋል።

በቆጵሮስ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት የአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ በላይነት እየመራው እንደሚገኝ የገለጹት ክቡር አባ ኢብራሂም፣ እርሳቸውም በኒቆሲያ ዋና ስቴዲዬም የሚካሄደውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት አፈጻጸም እንደሚያስተባብሩ ተናግረዋል። በሌላ ወገንም የማኅበራዊ ሚዲያ አስተባባሪ ኮሚቴ በበኩሉ አመርቂ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ክብር አባ ኢብራሂም አክለውም በየደረጃው የተዋቀሩ የዝግጅት አስተባባሪ ኮሚቴዎች ላለፉት ሦስት ሳምንታት ያህል በደስታ፣ በፍቅር እና በአንድነት ስሜት የተሰጣቸውን የሥራ ድርሻ በሚገባ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል። “ሁላችንን ለማዳን የሞተው ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ነው!” ያሉት ክቡር አባ ኢብራሂም፣ በቆጵሮስ የሚገኙ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መተባበራቸውን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለቆጵሮስ ሕዝብ በላኩት ሐዋርያዊ መልዕክ፣ “በቆጵሮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት የማደርገው ካቶሊካዊ ምዕመናንን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምዕመናን፣ በአገሪቱ ከሚገኙ ስደተኞች እና ከመላው የአገሪቱ ሕዝብ ጋር ለመገናኘት ነው” ማለታቸውን ክቡር አባ ኢብራሂም አስታውሰዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለቆጵሮስ ሕዝብ የላኩት መልዕክት፣ እያንዳንዱ ክርስቲያንና የሰው ልጅ በፍቅር እና በሰላም የተሞላ አዲስ ሕይወት እንደሚያገኝ ተስፋ በማድረግ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለቱ የሜዲትራኒያን አገራት በሚያድረጉት የ5 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ኒቆሲያን፣ ቆጵሮስን፣ የግሪክ ዋና ከተማ አቴንስን እና በርካታ ስደተኞች የሚገኝባትን የግሪክ ደሴት ሌስቦስን እንደሚያካትት 35ኛው የዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ-ግብር አመልክቷል።

የሐዋርያትን ፈለግ መከተል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ሁለተኛው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ በነዲክቶስ 16ኛም እ. አ. አ በ2010 በቆጵሮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚገልጽ መንፈሳዊ አርማ የደሴቲቱን የመሬት አቀማመጥ የሚያሳይ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የደሴቲቱ ጠባቂ እና  የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አጋር የሆነው የቅዱስ በርናባስ ምስል በዋናነት የተመለከተ ሲሆን፣ በተጨማሪም የወይራ ቅርንጫፍ እና የስንዴ ዘለላ በአንድነት ታስረው ሰላምንና ኅብረትን ለማመልከት የተቀመጡበት መሆኑ ተመልክቷል።

የቅዱስነታቸው 35ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ጭብጥ ወይም መሪ ቃል፣ ሐዋርያው ጳዎሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ በምዕ. 5 ቁ.11 ላይ “ስለዚህ አሁን በምታደርጉት ዓይነት አንዱ ሌላውን በማነጽ እርስ በርሳችሁ ተረዳዱ” የሚል ሲሆን፣ ይህም “የመጽናናት ልጅ” የሚለውን የቅዱስ በርናባስ ስም ትርጉም እንደሚያስታውስ ታውቋል።

ከቆጵሮስ ሕዝብ መካከል ስምንት ከመቶ ማለትም 850, 000 ያህሉ ክርስቲያን ሲሆን፣ ከዚህም መካከል 38,000 የሚሆኑ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች መሆናቸው ታውቋል። የእስልምና እምነት ተከታዮች ብዛትም ሁለት ከመቶ እንደሚደርስ ሲነገር፣ አብዛኛው የቆጵሮስ ሕዝብ የግሪክ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መሆኑ ተገልጿል። ከእነዚህ ምዕመናን መካከል ብዙዎቹ በ12ኛው ክፍለ ዘመን ኢየሩሳሌምን በበላይነት በተቆጣጠሩ እና በአካባቢው በሠፈሩ የመስቀል ጦርነት ተሳታፊዎች መሠረት ያላቸው መሆኑ ታውቋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በቆጵሮስ ውስጥ ባደረገው ቆይታ የደሴቲቱ ሮማዊ ገዥ የነበረው ሰርግዮስ ጳውሎስን ወደ ክርስትና እምነት መመለሱ ይታወሳል።

የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ-ግብር

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 35ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚጀምረው ሐሙስ ህዳር 23/2014 ዓ. ም. ወደ ቆጵሮስ በሚያደርጉት ጉዞ ሲሆን፣ በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ በዘጠኝ ሰዓት ተኩል ላይ ላርናካ አየር ማረፊያ እንደሚደርሱ ይጠበቃል። ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለ ስልጣናት በኩል ይፋዊ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ በኒቆሲያ የማሮናይት የጸጋ እመቤታችን ማርያም ካቶሊካዊ ካቴድራል ውስጥ ተገኝተው ከካኅናት፣ ከገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ከዲያቆናት፣ ከትምህርተ ክርስቶስ መምህራን እና ከልዩ ልዩ የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት አባላት ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል። በአሥራ አንድ ሰዓት ከሩብ ላይ  የቆጵሮስ ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ኒቆስ አናስታሲዮስ በዋና ከተማው በሚገኝ ቤተ መንግሥት የክብር አቀባበል ካደረጉላቸው በኋላ ለአገሪቱ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለሲቪሉ ማህበረሰብ ተወካዮች እና ዲፕሎማቶች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ዓርብ ጠዋት በኒቆሲያ በሚገኘው የቆጵሮስ ኦርቶዶክሳዊ ሊቀ ጳጳስ የነበሩ የብፁዕ አቡነ ክሪሶስቶሞስ 2ኛ መካነ መቃብር ከጎበኙ በኋላ በኒቆሲያ በሚገኝ የኦርቶዶክስ ካቴድራል ውስጥ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል። ረፋዱ ላይ በአገሪቱ ስታዲዬም የሚዘጋጀውን የመስዋዕት ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት እንደሚመሩም ይጠበቃል። ከሰዓት በኋላም በኒቆሲያ በሚገኝ በቅዱስ መስቀል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከስደተኞች ጋር ሆነው የአብያተ ክርስቲያናት የጋራ ጸሎት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ቅዳሜ ኅዳር 25/2014 ዓ. ም. የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ ክፍል ወደሆነው ወደ ግሪክ ከተማ አቴንስ እንደሚያመሩ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አስታውቋል።

01 December 2021, 14:08