ፈልግ

ሕጻናት በሊባኖስ ቤቴ ሄባክ ካቶሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሕጻናት በሊባኖስ ቤቴ ሄባክ ካቶሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ 

ክርስቲያናዊ ድርጅቶች ለሊባኖስ ካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ዕርዳታ ማድረጋቸው ተገለጸ

የተለያዩ ክርስቲያናዊ በጎ አድራጊ ድርጅቶች በሊባኖስ ውስጥ ለሚገኙ ካቶሊክ ትምህርት ቤቶች የገንዘብ ዕርዳታ ማድረጋቸውኝ በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍል ጎብኝት ያደረገው የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። ሊባኖስን ያጋጠማት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ የበርካታ ቤተሰብ ሕይወት አደጋ ላይ በመጣል ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ማድረጉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እ. አ. አ በ2020 በቤይሩት ወደብ የተከሰተው ፍንዳታ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ የሊባኖስን ሕዝብ ለድህነት ሕይወት ማጋለጡ ታውቋል። ከአራት ሚሊዮን የአገሪቱ ሕዝብ መካከል ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው በቂ የምግብ ዋስትና እንደሌለው ይነገራል። የሊባኖስ የገንዘብ ምንዛሪ ከ90 በመቶ በላይ ዝቅ ማለቱ እና የዋጋ ግሽበቱ በድህነት ሕይወት የሚገኙ ቤተሰቦች ከዕለት ምግባቸው፣ ከጤና እንክብካቤ እና ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ መካከል አንዱን ለመምረጥ ማስገደዳቸው ተነገሯል።  

ይህ ቢሆንም በአገሪቱ ከሚገኙ ካቶሊክ ትምህርት ቤቶች መካከል አብዛኛዎቹ ለትምህርት አገልግሎት ቅድሚያን በመስጠት ሂደቱ እንዳይቋረጥ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ የቅዱሳት ምስጢራት ደናግል ማኅበር፣ በሰላሳ መንደሮች የሚኖሩ 1,500 ተማሪዎች የሚማሩበትን ትምህርት ቤት በማስተዳደር ላይ መሆኑ ታውቋል። ከተማሪዎቹ መካከል አብዛኛዎቹ ከክርስቲያን ቤተሰብ የመጡ ሲሆን ከእስልምና እምነት ተከታይ ቤተሰብ የመጡ ተማሪዎችም በትምህርት ቤቱ ተመዝግበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸው ታውቋል። ዕድሜአቸው ከአራት እስከ አሥራ ስምንት ዓመት የሚሆናቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሰማንያ የሚደርሱ ተማሪዎች ማደሪያ ቤት ተሰጥቶአቸው የሚኖሩ ልጃ ገረዶች መሆናቸው ታውቋል።

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለተመዘገቡት 700 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው መንግሥት በዓመት 40 ዶላር ለመክፈል ቃል ቢገባም እ. አ. አ ከ2019 ጀምሮ ትምህርት ቤቱ ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ሳያገኝ መቆየቱ ታውቋል። አቅም የሚፈቅድላቸው ቤተሰቦችም በበኩላቸው ለትምህርት ቤቱ በዓመት እስከ 55 ዶላር ማዋጣት ቢጠበቅባቸውም ይህን ለማድረግ ለአብዛኞቹ ወላጆች አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱ ተገልጿል።

ለልጆች የትምህርት አገልግሎትን ማረጋገጥ

የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር፣ እህት ማጊ አዳባሺ፣ ልጆች ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ በማለት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ሲነገር፣ ትምህርት ቤቱ ለ80 መምህራን እና አሥራ አምስት የአስተዳደውር ክፍል ሠራተኞች ወርሃዊ ደሞዛቸውን ሳያቋርጥ ለመክፈል መገደዱ ታውቋል። መምህራን የዋጋ ግሽበት ያስከተለውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸው ሲታወቅ የትራንስፖርት ወጪዎቻቸውን ለመቀነስ ሲሉ በትምህርት ቤት አውቶቡስ እንደሚጓዙ፣ አለበለዚያ ብዙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል እንደማይችሉ ተነግሯል።

የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር፣ እህት ማጊ የቤተሰብን የገንዘብ ችግር ሊቀንስ ይችል ይሆናል በማለት በወሰዱት እርምጃ ተማሪዎች ዩኒፎርም እንዲለብሱ የሚያስገድድ መመሪያ ደንብ መሻራቸው ታውቋል። የምንዛሪው ዋጋ መቀነስ ረድቶናል ያሉት የትምህርት ቤቱ ረዳት ዳይሬክተር እህት ቻርሎት፣ በውጭ አገር ምንዛሪ የሚደረጉ ትንንሽ ልገሳዎች በርካታ የትምህርት ቤታቸውን ውጥኖች ተግባራዊ ለማድረግ ያስቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ጊዜ በሳምንት ሁለት ጊዜ ብቻ፣ ማክሰኞ እና ዕሮብ ክፍት መሆኑን እህት ቻርሎት ገልጸው፣ በተቀሩት ቀናት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአውታረ መረብ አማካይነት የሚከታተሉ መሆኑን አስረድተዋል።

በዓለም አቀፍ ዕርዳታ ላይ መተማመን

ይሁን እንጂ እነዚህ ዕርዳታዎች በቂ አለመሆናቸውን የገለጹት የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር እህት ማጊ፣ ከቤተክርስቲያን ጋር ግንኙነት ካላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከእነዚህም መካከል በችግር ለወደቁት ቤተክርስቲያናት ዕርዳታን ለሚለግስ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን፣ መካከለኛውን ምሥራቅ አገራት ለሚረዳ ድርጅት እና ከሌሎች የተለያዩ ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ዓመታዊ የሥራ እቅዳቸውን አዘጋጅተው ማቅረባቸውን እህት ማጊ ገልጸዋል።

በአገሪቱ ላይ የደረሰው ቀውስ የትምህርት ቤቱን ፍላጎቶች በረጅም ጊዜ ሂደት በጥንቃቄ እንዲያቅዱ እና የገንዘብ ድጋፍም በየዓመቱ እንዲረጋገጥላቸው መጠየቁን እህት ማጊ ገልጸው፣ በሊባኖስ እንዳሉት ሌሎች በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ የቤቴ ሄባክ ካቶሊክ ትምህርት ቤትም ሙሉ በሙሉ በውጭ ዕርዳታ የሚደገፍ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ካልሆነ ትምህርት ቤታቸው አገልግሎቱን ለማቋረጥ የሚገደድ መሆኑን አስረድተዋል።

ተስፋ መቁረጥ የለብንም

እነዚህ ጥረቶች በሙሉ በተስፋ የተደገፉ በመሆናቸው እና መነኮሳቱም ተስፋን ላለመቁረጥ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ መሆናቸው ታውቋል። በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የሚኖሩ በቁጥር 80 የሚደርሱ ልጃገረዶች  የዕለት ቀለባቸውን ከትምህርት ቤቱ እያገኙ ከበጎ ፈቃደኞችም ዕርዳታን በማግኘት ላይ መሆናቸው ታውቋል። በችግር ወቅት ለአዲሱ ትውልድ የሚስጥ የትምህርት አገልግሎት እንዳይቋረጥ በማለት መምህራን፣ መነኮሳት፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች የጋራ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ሲነገር፣ አልፎ አልፎ ድካም ቢሰማቸውም የቆሙለትን ዓላማ ለማሳካት በርትተው በመሥራት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

13 December 2021, 16:45