ፈልግ

የኢራቅ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ፣ የኢራቅ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ፣  

ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ ለኢራቅ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል መልዕክት አስተላለፉ

በምሥራቅ ቤተክርስቲያን የከለዳውያን ሥርዓተ-አምልኮን የምትከተል የኢራቅ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በማስመልከት ለኢራቅ ክርስቲያኖች መልዕክት አስተላልፈዋል። ብጹዕነታቸው ለክርስቲያን ማኅበረሰቡ ባስተላለፉት መልዕክት የኢራቅ ክርስቲያን ተስፋ እንዲያደርግ አሳስበው፣ በአገራቸው በሚከበረው ብሔራዊ የሰላም ቀን ኢራቅን በጸሎታቸው እንዲያስታውሱ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል በኢራቅ ውስጥ የከለዳውያን ሥርዓተ-አምልኮን ለሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ባስተላለፉት የብርሃነ ልደቱ መልዕክት፣ በኢራቅ ውስጥ በቅርቡ ከተካሄደው የሕግ አውጭዎች ምክር ቤት ምርጫ ወዲህ የፖለቲካ ውጥረት እና አመጾች እያደጉ መምጣታቸውን ገልጸው፣ ክርስቲያኖች የብርሃነ ልደቱ መሠረት የሆነው ተስፋ እንዲገለጽ ተስፋን ሳይቆርጡ ለሰላም እና መረጋጋት እንዲጸልዩ አሳስበዋል። ብጹዕነታቸው አክለውም የአካባቢ ብክለት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ከሕግ አውጭዎች ምክር ቤት ምርጫ ወዲህ የተፈጠሩ የተለያዩ ተግዳሮትች በሚታይባት ኢራቅ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት መልዕክት የተስፋ፣ የሰላም፣ የወንድማማችነት፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የእግዚአብሔር ቡራኬን የሚያስታውስ መሆኑን በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

ሌሎችን ማገልገል

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የእግዚአብሔር ፍቅር በዘመናት ሁሉ ለመላው የዓለማችን ሕዝቦች እና ባሕሎች እንዲገለጽ አድርጓል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ፣ በዚህም እግዚአብሔር ለልጆቹ ቅርብ መሆኑን እና ዘወትር እንደሚያስብላቸው መግለጹን አስረድተው፣ ክርስቲያኖች በተመሳሳይ ፍቅር በመታገዝ ሌሎችን በተለይም ድሆችን እና ለችግር የተጋለጡትን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።        

እውነተኛ ሀገራዊ ራዕይ ሊኖር ይገባል

ብፁዕ ካርዲናል ሩፋኤል በመቀጠልም፣ አንድ መንግሥት የሕዝቡን ፍላጎት በእውነተኛ አገራዊ ራዕይ የሚያገለግል ከሆነ ተስፋ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመው፣ ዴሞክራሲ፣ የገባውን የዜጎችን ደህንነት እና ክብር የመጠበቅ ቃል እውን እንዲያደርግ፣ በአገሪቱ የሚታዩ የተለያዩ ቀውሶችን በውይይቶች መቋቋም እንደሚቻል አስረድተዋል። ተስፋው ከታች ጀምሮ በሚገኘው የኢራቅ ሕዝብ ተሳትፎ እንጂ በሌላ ውጫዊ አካል እውን ሊሆን እንደማይችል ገልጸው፣ የኢራቅ ማኅበረሰብ ብሔርተኝነትን አስወግደው ሁሉም ዜጋ እኩል መብት እና ነፃነት የሚጎናፀፍበት፣ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ አንድነታዊ ሀገር ለመገንባት ጥረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ለአገር መረጋጋት መጸለይ ያስፈልጋል

“ለውድ አገራችን እና ለመላው ዓለም ሰላም እና መረጋጋት እንጸልይ” ያሉት በምሥራቅ ቤተክርስቲያን የከለዳውያን ሥርዓተ-አምልኮን የምትከተል የኢራቅ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላም በምድር ይሁን!” የሚለውን ዝማሬ በተግባር ለመግለጽ የመቻቻል፣ የምሕረት፣ የሰላም እና የወንድማማችነት እሴቶችን ልናንጸባርቅ ይገባል በማለት፣ የዘንድሮ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ፓትሪያርክ ሩፋኤል ሳኮ፣ የክርስትና እምነት ተከታዮች እና መልካም ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ በአገሪቱ ውስጥ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መረጋጋት ለማስፈን እንዲጸልዩ አደራ በማለት ለብሔራዊ የጾም እና የጸሎት ቀን ጠርተዋል።

በኢራቅ ውስጥ መስከረም 30/2014 ዓ. ም. የተካሄደው የሕግ አውጭዎች ምክር ቤት ምርጫ የፖለቲካዊ ሁከት እና ብጥብጥ ማስከተሉ የሚታወስ ሲሆን፣ ውጤቱ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ በተለይም በኢራን የሺዒ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች ዘንድ ቅሬታን ማስከተሉ ይታወሳል። በኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ በኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዲሚ መኖሪያ ቤት ላይ የተሰነዘረው የድሮን ጥቃት ስጋቱን መጨመሩ ታውቋል። በተጨማሪም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው ውጥረት ሀገሪቱን ወደ ትርምስ እና ሁከት እንዳያስገባት መንግሥት ጠንካራ አቋም እንዲወስድ ደጋግመው ያቀረቡት ጥያቄ በከለዳውያን ብጹዓን ጳጳሳት ላይ ስጋት መፍጠሩ ይነገራል።

22 December 2021, 13:38