ፈልግ

የሄይቲ ሕዝብ ብሶቱን በሰልፍ ሲገልጹ የሄይቲ ሕዝብ ብሶቱን በሰልፍ ሲገልጹ 

የሄይቲ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት የአገር ፍቅር ስሜት የበለጠ እንዲታይ ጠየቁ

የሄይቲ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ለአገሪቱ ካቶሊካዊ ምዕመናን ባስተላለፈው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል መልዕክት፣ ሕዝቡ የአገር ፍቅር ስሜቱን እንዲያሳይ ጠይቆ፣ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሰብአዊ ቀውሶች በገጠማት ባሁኑ ጊዜ ሀገራዊ ሃላፊነትን እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ጠይቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሄይቲ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ መዘፈቋ በቀጠለበት ባሁኑ ወቅት፣ የጸጥታ እጦት እየጨመረ በመምጣቱ፣ የሄይቲ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት የአገሪቱ የፖለቲካ መሪዎች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በድጋሚ አሳስበው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሄቲን ሳይዘነጉ አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርጉላት አደራ ብለዋል። ቀውሱን ለማሸነፍ የሀገር ፍቅር ስሜት በተግባር እንዲገለጽ የጠየቁት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ "በቅርብ ወራት ውስጥ የተከሰቱትን አሳዛኝ ክስተቶች በዝምታ መመልከት አንችልም" በማለት ጠንከር ያለ የገና መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል።

ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውሶች

በሄይቲ ውስጥ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው በቆዩባቸው ጊዜያት ኤኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ማኅበራዊ አለመረጋጋት እና እያደገ በመጣው የጎዳና ተዳዳሪዎች መታፈን ሁሉንም የሄይቲ ዜጎች ፍርሃት መክተቱ ታውቋል። በተለይም ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ውስጥ ከተፈጸመው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ግድያ እና በነሐሴ ወር በደሴቲቱ ደቡባዊ ክፍል ከ2,000 በላይ ሰዎች ሞት እና ለ12,000 ሰዎች መቁሰል ምክንያት የሆነው የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ ወዲህ ችግሮች እያደጉ መምጣታቸው ታውቋል። ባለፉት ቅርብ ቀናት ውስጥም በሰሜናዊቷ ካፕ-ሄይቲ ከተማ ውስጥ በነዳጅ ማከማቻ ላይ የደረሰው ፍንዳታ ወደ 75 በሚጠጉ ሰዎች ላይ ጉዳት ማስከተሉ ይታወሳል።

"እንዲህ ያለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ውስጥ ሃላፊነት ያለባቸውን ሰዎች ህሊና በመውቀስ እርዳታን እንዲያደርጉ፣ የወጣውንም ቁስል በመፈወስ እና የሰብዓዊ መብቶች መከበርን ለማበረታታት እንዲተባበሩ ሊያደርጋቸው አይገባም ወይ?" በማለት የሄይቲ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው ጠይቀው፣ “የፖለቲካ መሪዎቻችንም በዚህ ምስቅልቅል እና አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሊጨነቁ አይገባም ወይ?” በማለት ጠይቀዋል።

የሀገር ፍቅር ስሜት ሊኖር ይገባል

የሄይቲ ሕዝብ ሕሊና፣ “በሰዎች ላይ ብዙ ግፍና መከራ የሚፈጽሙት ክፉ ኃይሎችን ለመዋጋት የሞራል እና የአገር ፍቅር ስሜት ይጠይቃል” በማለት ብጹዓን ጳጳሳቱ ገልጸው፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ኃላፊነት ያለባቸው ሁሉ፣ አገሪቱን ለረጅም ጊዜ ሲያቆስላት ለቆየው ቀውስ ዘላቂ መፍትሄ በማፈላለግ በሃላፊነት ስሜት ተነሳስተው መግባባትን እና ሰላምን በማፈላለግ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

ሄይቲን የወንድማማችነት አገር ማድረግ

የሄይቲ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በአፈና እና በአስገድዶ መደፈር ጥቃት ለተጎዱ ቤተሰቦቻቸው ያላቸውን አጋርነት ገልጸው፣ እነዚህን ድርጊቶች በጽኑ አውግዘው፣ በአገሪቱ ሕግ እና ስርዓት እንዲሰፍን በድጋሚ ጥሪ አቅርበው፣ የታጠቁ ቡድኖችም ትጥቃቸውን እንዲፈቱ አሳስበዋል። የበለጠ ፍትሃዊ፣ ሰብአዊ እና ወንድማማችነት የሰፈነባት አገርን መልሶ ለመገንባት ሁሉም ሰው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አሳስበዋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ትብብር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እስካሁን ለሄይቲ ሕዝብ ያደረጉትን ድጋፍ ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳቱ ለአጋርነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበው በተለይም በጥቅምት 21/2014 ዓ. ም. በመሩት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ የዓለም መሪዎች ሀገሪቱን እንዲረዱ እና የሄይቲን ህዝብ እንዲያስታውሱ መጠየቃቸውን ብጹዓን ጳጳሳቱ አስታውሰዋል።

በተጨማሪም አገራቸውን ጥለው የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚገደዱ ብዙ የሄይቲ ዜጎች፣ በውጭ አገራት የሚደርስባቸው ጥቃትና መድልዎ ሰለባ መሆናቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸው፣ “ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በመሆን የሰውን ልጅ ክብር የሚያረጋግጡ መሠረታዊ ሕጎች በሁሉም ዘንድ ተግባራዊ እንዲሆኑ እንጠይቃለን” ብለዋል።

የጸሎት ጥሪ

የሄይቲ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የብርሃነ ልደቱ መልዕክት፣ የሄይቲ ሕዝብ “ከአገሪቱ ጥቅም ይልቅ ጥቃቅን ጥቅሞቻቸውን” ማስቀደም እንዲያቆም እና ጸሎቱን እንዲያጠናክር ጥሪውን አቅርቦ፣ መንፈስ ቅዱስ ጥበብን እና ማስተዋልን እንዲሰጥ፣ አገሪቱን ለሁለንተናዊ መታደስ ፍለጋ እንዲመራ መጸለይ ያስፈልጋል በማለት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ታኅሳስ 6/2014 ዓ. ም. ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት፣ በካፕ-ሄይቲ ከተማ በሚገኝ አንድ የነዳጅ ማከማቻ ላይ የደረሰውን ፍንዳታ በማስታወስ የጸሎት ጥሪ ማቅረባቸውን የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤው በመልዕክቱ አስታውሷል።

21 December 2021, 16:44