ፈልግ

በሳልቫዶር የሚታይ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር በሳልቫዶር የሚታይ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር 

አቡነ ፋሬል፣ በደብሊን ከተማ የአደንዛዥ ዕጽ በመደበኛነት በጥቅም ላይ መዋሉን አወገዙ

በአይርላንድ የደብሊን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዴርሞንት ፋሬል፣ የጎርጎርሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ለማክበር በሚዘጋጁበት የመጀመሪያ እሑድ ስብከታቸው፣ በአይርላንድ ዋና ከተማ ደብሊን ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ አደንዛዥ ዕፅ መስፋፋቱን ገልጸው፣ በመደበኛነት ጥቅም ላይ መዋሉንም በጥብቅ አውግዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መካከል ሌላ ተጨማሪ የአምጽ ወረርሽኝ በዋና ከተማ ደብሊን መስፋፋቱን ገልጸው፣ ሁኔታው የኅብረተሰቡን ምላሽ ይጠይቃል ብለዋል። በዋና ከተማው የአደንዛዥ ዕጽ የተስፋፋበት ምክንያት ውስብስብ እና ጥልቅ ነው ያሉት ብጹዕ አቡነ ፋሬል፣ ለችግሩ መፍትሄ ሊገኝ የሚችለው በጋራ በመሥራት ብቻ መሆኑን አስረድተው፣ በኅብረተሰቡ፣ በመንግሥት እና የሐይማኖት አባቶች በሚያሳዩት በጎ ፈቃደኝነት ብቻ እንደሆነ ገልጸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር በዋና ከተማዋ ደብሊን እና በመላው የአገሪቱ ክፍሎች መስፋፋት የኅብረተሰቡ ችግር በመሆኑ የኅብረተሰቡን ምላሽ ይጠይቃል ብለዋል።

የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ሕጋዊ ማድረግ

በአገሪቱ ውስጥ የአደንዛዥ ዕጽ አጠቃቀም መደበኛ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት የደብሊን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፋሬል፣ "ለአንዳንድ ሰዎች አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ እንደ መጠጥ የተለመደ ሆኗል" ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ "ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህትማማቾች፣ በማይነጣጠል አንድነት እርስ በርሳችን የተያያዝን ነን" ማለታቸውን አቡነ ፋሬል አስታውሰው፣ በማይነጣጠል አንድነት ውስጥ ያለውን ርኅራሄ፣ ገርነት እና ለሌሎች ሰዎች ያለንን ሃላፊነት ማጣት የለብንም ብለዋል። ስለሆነም መፍትሄው የሕገወጥ አደንዛዥ ዕጽ ዝውውር መግታት ብቻ ሳይሆን አዘዋዋሪዎችን እና የተዋናይ ወንጀለኞች መረብ መበጠስ፣ የበለጠ ውጤታማ ክትትል ማድረግ፣ የፍትህ ማሻሻያ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ በኤኮኖሚ በተጎዱ አካባቢዎች መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ብቻ ሳይሆን የባህሪ ለውጥ ለማምጣት መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ሕይወት ይሻላል

የችግሩ ትክክለኛ መልስ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ማስቆም የሚችል የተሻለ ዕቅድ ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን በአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪነት ከሚታወቁ እና ከተጠቃሚ ሰዎች ቤተሰቦች ጋር በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ሰዎችን ከጎጂ ልማዳቸው ለማላቀቅ መርዳት እና ጉዳቱንም ማስረዳት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት የዳብሊን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዴርሞንት ፋሬል፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን መልዕክት በማስታወስ፣ ምርጫን ለመልካም ሕይወት፣ ለእርስ በእርስ መዋደድ፣ ሌሎች ለመቅረብ፣ ለመልካም ትምህርት፣ ለስፖርት፣ እና ለተጨማሪ የሥራ ዕድሎች ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ እነዚህን ተግባራዊ ማድረጉ እንደሚጠቅም ከልብ ከተገነዘቡ፣ ለአደንዛዥ ዕፅ፣ ለአልኮል እና ለሌሎች ሱሶች ቦታ የለም ብለዋል።

እግዚአብሔር በመካከላችን አለ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን መገኘቱን ለማወቅ ስንዘጋጅ፣ እርሱ በቃሉ እና በቅዱስ ቁርባኑ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአካባቢያችን ባሉ ሰዎች ውስጥም መኖሩን መገንዘብ ይኖርብናል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ "ስጋት ውስጥ በሚገኙት፣ ከማኅበረሰቡ መካከል በተገለሉት እና የብቸኝነት ሕይወት በሚኖሩ፣ በአደንዛዥ ዕፅና በዓመፅ በተሰቃዩት ሰዎች በኩል ይመጣል” ብለዋል። ስለዚህ፣ በጎጂ ሱሶች የተጠቁትን ለማገልገል ሕይወታቸውን የሰጡት በሙሉ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ለእኛ ቅርብ መሆኑን፣ እግዚአብሔርም ሕዝቡን እንደማይተዋቸው እና ክርስቲያን መሆን ማለት የደከሙ ሰዎችን ለመርዳት በተለየ መንገድ መጠራት መሆኑን መመስከር ያስፈልጋል በማለት፣ በአይርላንድ የደብሊን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዴርሞንት ፋሬል አሳስበዋል።

30 November 2021, 16:32