ፈልግ

ዓለም አቀፍ የተልዕኮ እሑድ ዓለም አቀፍ የተልዕኮ እሑድ  

ዓለም አቀፍ የተልዕኮ ቀን ከባድ ሐዋርያዊ ምስክርነቶች የሚታወሱበት ቀን መሆኑ ተገለጸ

እሑድ ጥቅምት 14/2014 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የተልዕኮ ቀን ተክብሮ መዋሉ ተገልጿል። “ሚሲዮ” አይርላንድ በመባል በቅርቡ የተመሰረተ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ሊቀ መንበር የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኬይራን ኦሬይሊ በመልዕክታቸው ዕለቱ በዓለም ውስጥ ሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎት አበርክተው ያለፉትን እንድናስታውስ የሚያግዝ ነው ብልዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥቅምት 14/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፣ የወንጌል ምስክርነታቸውን ታላቅ መስዋዕትነትን በመክፈል የሚያቀርቡ ሚሲዮናዊያንን በክብር አስታውሰዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመላው ዓለም የምትገኝ ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፍ የተልዕኮ እሑድን ትናንት ጥቅምት 14/2014 ዓ. ም. ስታከብር፣ ዕለቱ በማይመች እና አስቸጋሪ ሁኔታ መካከል ሚሲዮናዊያን ያበረከቱትን በርካታ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን በማስታወስ አንድነትን በመግለጽ በጸሎት እንድናስታውሳቸው መልካም አጋጣሚ የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 2014 ዓ. ም. ለተከበረው ዓለም አቀፍ የተልዕኮ ቀን መልዕክታቸው የመረጡት ርዕሥ፦ በሐዋ. 4፡20 ላይ “እኛስ ያየነውን እና የሰማነውን ከመናገር አንቆጠብም” የሚል እንደነበር ታውቋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው “የእግዚአብሔርን የፍቅር ኃይል ካገኘን በኋላ ያየነውንና የሰማነውን ከመስበክና ለሌሎች ከማካፈል በቀር ምንም ማድረግ አንችልም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ እና ከስብዕናው ጋር ያለው ግንኙነት ፣ እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚወደን፣ ደስታችንን እና መከራችንን ፣ ተስፋችንን እና ጭንቀታችንን ከራሱ ጋር አንድ እንደሚያደርግ ያሳየናል” ብለዋል።

የተልዕኮ አርበኞች

በአይርላንድ የሚገኝ ጳጳሳዊ የተልዕኮ ማኅበራት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሊቀ መንበር፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኬይራን ኦሬይሊ ከቫቲካን የዜና አገልጎሎት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ የተልዕኮ ቀን ችግር እና መከራ በበዛበት በዚህ ወቅት ለሚሰጠው ምስክርነት እውቅናን እንድንሰጥ ታላቅ ጥሪ የሚያቀርብ መሆኑን ገልጸው፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚገኙ ብዙ ክርስቲያን ማህበረሰቦች የሚቀርቡ ምስክርነቶች ጠንካራ መሆናቸውን አስታውሰው፣ በዓለም አቀፍ የተልዕኮ ቀን ስለ እነዚህ ምስክርነቶች መናገር ከተልዕኮ ቀን ዋና ዓላማዎች መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኬይራን ኦሬይሊ በማከልም፣ ዕለቱ ሚሲዮናዊያኑ በችግር መካከል ያበረከቱትን ከፍተኛ አገልግሎቶችን እንድናስታውስ ጥሩ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ገልጸው፣ ዛሬም ቢሆን በችግር እና በፈተና ውስጥ የሚገኙትን በማሰብ በጸሎታችን ልናስታውሳቸው ይገባል ብለዋል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ

“የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎት መካከል ምንን አስተማረን?” ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ መልሳቸውን የሰጡት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኬይራን ኦሬይሊ፣ “በዓለም ዙሪያ የሚቀርቡ የሐዋርያዊ ተልዕኮ ይዘትን በብዙ መልክ በመለወጥ፣ የሰው ዘር በሙሉ አንዱ በሌላው እንዲመካ ከማድረጉ በላይ ሁላችንም በወንድማማችነት እና እህትማማችነት ላይ ያለንን ጥገኝነት ከፍ አድርጎታል” ብለዋል። እርስ በእርስ የመተጋገዝ ተልዕኮ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ኬይራን፣ በወረርሽኙ ተይዘው የሚሰቃዩትን መንከባከብ እና የመከላከያ ክትባቶች በትክክል መሰራጨታቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም ሁሉንም ሰው ለመርዳት የበለጠ ሚስዮናዊ መሆን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ወረርሽኙ በተለይም በድሃ አገራት ውስጥ ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመቋቋም የጋራ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።     

ሚሲዮናዊ ደቀ መዛሙርት

እኛ ሁላችንም ለተልዕኮ ተጠርተናል ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኬይራን ኦሬይሊ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ የአገልግሎት ዓመታት፣ እያንዳንዱ ሰው “ለተልዕኮ ደቀ መዝሙርነት” የተጠራ መሆኑን በጥብቅ ማሳሰባቸውን አስታውሰው፣ ባለፉት ዓመታት “ሚሲዮናዊነት” የሚለው አስተሳሰብ ከትውልድ አገር ወጥተው በውጭ አገራት የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ አገልግሎት እንደሚያመለክት ገልጸው፣ ይህን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ ከበርካታ ዓመታ በፊት አገራቸው አይርላንድ በርካታ ሚሲዮናዊያንን ወደ ውጭ አገራት መላኳን አስታውሰዋል። ያ የሐዋርያዊ አገልግሎት ጥሪ ዛሬ፣ በተለይም ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በኋላ የቤተክርስቲያን ማንነት የሚገለጽበት እና እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን አባል ሚስዮናዊ ደቀ መዝሙር እንዲሆን የተጠራበት ሐዋርያዊ ተልዕኮ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ኬይራን አያይዘውም፣ ዛሬም ቢሆን ወንጌል ወዳልተሰበከባቸው አካባቢዎች ሄደው ምስክርነታቸውን የሚያቀርቡ ሚሲዮናውያን መኖራቸውን ገልጸው፣ በእምነታቸው የጸኑ ማህበረሰቦች በሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርትነት በርትተው የተልዕኮ አገልግሎታቸውን እንዲያበረክቱ የሚያሳስብ ጠንካራ ጥሪ መኖሩን ገልጸዋል። 

ከክፍፍል ይልቅ አንድነት እንደሚበጅ

በሰሜን ናይጄሪያ፣ ካዱና ግዛት በሚሲዮናዊነት የሚኖሩ እህት ቬሪኒካ ኦያኒሲስ፣ የዘንድሮ ዓለም አቀፍ ተልዕኮ ቀንን በሕይወት ምስክርነት በተግባር መግለጻቸው ታውቋል። በአገሪቱ በሚገኝ የእምነት ተቋማት ምክር ቤት ውስጥ የሴቶች ምክር ቤትን የሚመሩት እህት ቬሮኒካ በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን እና ሙስሊም ሴቶችን በማስተባበር፣ ሁለቱም እምነቶች በሰላም የሚኖሩበትን፣ ሃይማኖታዊ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት የሚቀሰቀሱ ዓመጾችን አስወግደው የመቻቻል ባሕልን ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ብጹዕ አቡነ ኬይራን ገልጸዋል። እህት ቬሪኒካ የሁለቱ እምነቶች ተከታዮች ከሚከፋፍላቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጉ የጋራ እሴቶችን ማጠናከር እንደሚገባ ማሳሰባችውን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ኬይራ፣ የሰው ልጅ የሕይወት ጉዞ ይህን መምሰል ይገባል ብለዋል። ሁል ጊዜ የሚከፋፍሉን ነገሮች እንመርጥ ይሆናል፣ ነገር ግን ምንም ጥቅም አይሰጡንም ያሉት ብጹዕ አቡነ ኬይራን፣ እርስ በርሳችን በመረዳዳት አብረን መጓዝ ከቻልን፣ በፍቅሩ ብዛት ልጁን አሳልፎ ወደሚሰጠ እግዚአብሔር ዘንድ መቅረብ እንችላለን ብለዋል። 

አዲስ ስም ማግኘት

በአይርላንድ የሚገኝ ጳጳሳዊ የተልዕኮ ማኅበራት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለውጥ ማድረጉን የጽሕፈት ቤቱ ሊቀ መንበር ብጹዕ አቡነ ኬይራን፣ ባለፉት ዓመታት “የአየርላንድ ዓለም አቀፍ ተልዕኮዎች” ተብሎ ይጠራ የነበረው ጽ/ቤታቸው “ሚሲዮ አይርላንድ” በሚለው አዲስ ስም መተካቱን አስረድተው፣ “ይህ የሆነበት ምክንያትም በሌሎች አገሮች ውስጥ ከሚገኙ መሰል የተልዕኮ ጽ/ቤቶች ጋር የበለጠ ተቀራርቦ ለመሥራት እና ሁሉም አገራት ‘ሚሲዮ’ የሚል ተያያዥ ስም ስላላችው ነው ብለው፣ አዲሱ ስማቸው ከቤተክርስቲያን ጠቅላላ ተልዕኮ ጋር የበለጠ እንደሚገናኝ እና ይህም ጠቃሚ ሆኖ በማግኘታችን ነው” ብለዋል።  

25 October 2021, 17:17