ፈልግ

የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል  

የእምነት መሪዎች በአየር ንብረት ላይ ፍትሃዊነት ያለው እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰቡ

ከአምስቱም አኅጉራት የተወጣጡ የእምነት መሪዎች በአየር ንብረት ላይ ፍትሃዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅ “ቅዱስ ሕዝብ እና ቅዱስ ልብ” በሚል አርዕስት የተዘጋጀ አንድ አቤቱታ እና ከዚህም ጋር ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላስከተለው ቀውስ የጋራ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያሳስብ መልዕክት በጋራ ፈርመዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዓለም መንግሥታት መሪዎች በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት 26ኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ሊያካሂዱ ጥቂት ቀናት በቀሩበት ባሁኑ ጊዜ ከአምስቱም አኅጉራት የተወጣጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእምነት መሪዎች፣ በአየር ንብረት ላይ ፍትሃዊነት ያለው እርምጃ እንዲወሰድ በማለት ያቀረቡትን ማሳሰቢያ በፊርማቸው አረጋግጠዋል። “ቅዱስ ሕዝብ እና ቅዱስ ልብ” የሚል አርዕስት የተሰጠው አቤቱታ በተጨማሪም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላስከተለው ቀውስ የጋራ ምላሽ እንዲሰጥም አሳስቧል። አቤቱታው እንዲዘጋጅ ድጋፍ ያደረገው “የአየር ንብረት እና የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ አረንጓዴ እምነት” የተሰኘ የእምነት ተቋማት ኅብረት ሲሆን ፊርማቸውን ያኖሩት የካቶሊክ እና ሌሎች የክርስትና እምነት መሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

የአየር ንብረት ለውጡ ለሚያስከትለው አደጋ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦች ሁኔታ ያሳሰባቸው የእምነት መሪዎች ፊርማቸውን በማኖር ባቀረቡት አቤቱታ፣ የአየር ንብረት ለውጥንም ሆነ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስን ለመዋጋት ጊዜውን የሚመጥን በርህራሄ፣ በፍቅር እና በፍትህ የተመራ የጋራ ምላሽ ሊኖር ይገባል ብለዋል። መልካም ሕይወት የአንድነት መገለጫ እንደሆነ የገለጹት የእምነት መሪዎች፣ የሕይወት አንድነት ከተፈጥሮ ሁሉ ጋር ግንኙነት እንዳለ ያረጋግጣል” ሲሉ ገልጸዋል።

ጊዜው ያለፈበት የኢኮኖሚ ሥርዓት የመቀየር አስፈላጊነት

እንደ እምነት መሪዎች ገለጻ፣ በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚካሄድ 26ኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤን የሚካፈሉ የመንግሥታት መሪዎች የተፈጥሮ ነዳጆችን በመጠቀም በደን ፣ በውሃ ፣ በውቅያኖሶች እና በአፈር ላይ ውድመትን የሚያስከትል፣ ጊዜ ያለፈበት የኢኮኖሚ ሥርዓትን እንዲያስቀሩ ጠይቀዋል። በምትኩ “የታዳሽ ሃይል ልማትን ማፋጠን እንዳለባቸው፣ ንጹሕ ውሃ እና ንጹሕ አየር፣ ተመጣጣኝ የሆነ ንጹህ የኃይል አቅርቦት፣ የመሬትን ደህንነት ያከበረ የምግብ ምርት እና ቤተሰብን መመገብ የሚችል ደመወዝ የሚገኝበት የሥራ ዕድልን” ማረጋገጥ እንዳለባቸው ጠይቀዋል። የእምነት መሪዎቹ በተጨማሪም “ሀብታም አገሮች ዓለም አቀፍ ፍትሃዊ ሽግግርን በመደገፍ የበካይ አየር ልቀትን ለመቀነስ ኃላፊነትን እንዲወስዱ” እንዲሁም “በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈናቀሉትን ተቀብለው ለማስተናገድ መዘጋጀት እንዳለባቸው ጠይቀው፣ ርህራሄ፣ ፍቅር እና ፍትህ ከሁላችንም ዘንድ ሊቀርብ ይገባል በማለት አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።

አሥር ምክረ ሃሳቦች

የእምነት መሪዎቹ በምድራችን ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋን ሊቀለብሱ ይችላሉ ያሏቸውን አሥር ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር አስቀምጠዋል። እነርሱም ታዳሽ ሃይል፣ ፍትሃዊ የፋይናንስ ሥርዓት፣ የሥራ ዕድል፣ የነባር ዜጎች ራስን በራስ የመወሰን መብት፣  ስደተኞችን ማስተናገድ፣ አካባቢን መልሶ መገንባት፣ ብዝሃ ሕይወትን መንከባከብ፣ የቅሪተ አካል ነዳጆችን እና በዝባዥ የግብርና ሥርዓትን ማጥፋት፣ የበለጸጉ አገሮች የአየር ንብረት ማካካሻ እና ጠንካራ የእምነት ማህበረሰብ አመራር የሚሉትን አስቀምጠዋል።

የገንዘብ ሥርዓት የጋራ ጥቅም ማገልገል አለበት

የእምነት መሪዎቹ ለፋይናንስ ተቋማት ባቀረቡት አቤቱታቸው፣ የፋይናንስ ተቋማት በብዝበዛ ላይ የተመሠረተ የአሰራር ሥርዓትን እንዲያስወግዱ፣ ምክንያቱም ገንዘብ "የጋራ ጥቅምን የሚያስከብ እንጂ ደካማን የሚበዘብዝ፣ ተፈጥሮን የሚጎዳ እና በሰዎች ገቢ መጠን ላይ ልዩነት የሚጨምር መሆን የለበትም" ብለዋል። ስለሆነም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ለአዳዲስ የቅሪተ አካል ነዳጅ ማምረቻ እና አካባቢን ለሚያበላሹ የግብርና መሠረተ ልማቶች የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቆሙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

“ጤናማ ፕላኔት እና ጤናማ ሰዎች” አቤቱታ

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦች “ጤናማ ፕላኔት እና ጤናማ ሰዎች” የሚለውን አቤቱታ በመፈረም፣ የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም ለሚሰበሰቡት የዓለም መንግሥታት መሪዎች አቅርበዋል። ፊርማ የማሰባሰቡን እንቅስቃሴ ያስተባበረው እና በገንዘብ ያገዘው በቀድሞው ስሙ “ግሎባል ካቶሊካዊ የአየር ንብረት ንቅናቄ” በመባል የሚታወቅ በአዲስ ስሙ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ንቅናቄ መሆኑ ታውቋል። አቤቱታው ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ የብዝሀ ሕይወት ቀውስን ለመቅረፍ እና የአየር ብክለትን ለመቀነስ ፖሊሲ አውጪዎችን የበለጠ በሚያስገድዱ ስምምነቶች ላይ እንዲደርሱ እና ከሥር ያሉ ማህበረሰቦች ንቁ ተሳትፎን በመደገፍ፣ የበለጠ ግንዛቤን የማስጨበጥ አስፈላጊነት የሚያጎላ መሆኑ ታውቋል። 

27 October 2021, 17:07