የጋራ ውይይትን መሠረት ያደረገ የፍጥረት መታሰቢያ ወቅት ይፋ ሆነ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ነሐሴ 26/2013 ዓ. ም. ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ዕለት፣ ክርስቲያኖች የጋራ መኖሪያ ምድርን ከውድመት ለማዳን የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርግ አሳስበዋል። የ2021 (እ. አ. አ) የፍጥረት መታሰቢያ ሰሞን ነሐሴ 26/2013 ዓ. ም መጀመሩንም አስታውቀው፣ ከቁንስጣንጢንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወ ቅዱስ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ እና ከካንተርበሪው የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ ጋር የጋራ መልዕክት ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከነሐሴ 26/2013 - መስከረም 24/2014 ዓ. ም. የሚቆየው የፍጥረት መታሰቢያ ወቅት፣ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳተፍ በየዓመቱ የሚካሄድ ዝግጅት ሲሆን ይህን መልካም ዓላማ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን የሌሎች እምነቶች ተከታዮች እና በጎ ፈቃድ ያላቸው በሙሉ የሚሳተፉበት አጋጣሚ እንደሆነ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ገልጸዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እንቅስቃሴ የአውሮፓ ፕሮግራሞች ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት ቼቺሊያ ዳልኦሊዮ፣ ዘንድሮ የሚከበረው የፍጥረት መታሰቢያ ወቅት የሚያስተላልፈውን መልዕክት ሲያብራሩ፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚያስፈልገውን ጥበቃ እና እንክብካቤ በስምምነት ካከናወኑ በኋላ ሌሎችም የሚኖሩበት ምቹ ሥፍራ ስለ ማዘጋጀት የሚያሳስብ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል የራሱን ድርሻ ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህ አጋጣሚ በየዓመቱ የሁሉንም አብያተ ክርስቲያናት ምዕመና በማሰባሰብ የመታደስ እና የተስፋ ጊዜን እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በጸሎት ሥነ-ሥርዓት ነሐሴ 26/2013 ዓ. ም. የተጀመረው ዓለም አቀፍ የፍጥረት እንክብካቤ ቀን፣ ዓመታዊ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ክብረ በዓል ዕለት መስከረም 24/2014 ዓ. ም. የሚገባደድ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ዕለት በመላው ዓለም የሚገኙ ምዕመናን ከዓለም ፈጣሪ እና ከፍጥረታቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያድሱበት ዕለት መሆኑ ወ/ሮ ቼቺሊያ አስታውቀዋል። ለዘንድሮ በዓል የተመረጠው መሪ ቃልም “የሁላችን መኖሪያ ምድራችን የሆነውን የእግዚአብሔርን ቤት እናድስ” የሚል መሆኑን ወ/ሮ ቼቺሊያ አክለው አስረድተዋል። በጋራ መኖሪያ ምድራችን ለሁሉ ሰው የሚሆን ሥፍራን ለማዘጋጀት ያለውን ቁርጠኝነት ለመግለጽ፣ ዘንድሮ የሚከበረውን የፍጥረት መታሰቢያ ወቅትን በሚገባ ለማክበር ታስቦ የቀረበ የዓመቱ ምልክት “የአብርሃም ድንኳን” መሆኑ የገለጹት ወ/ሮ ቼቺሊያ፣ ይህን ለመግለጽ በሚል ዓላማ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች በርካታ ድንኳኖች መተከላቸውን አስታውሰዋል። ዓላማው ከዚህም በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚገኙ ምዕመናን ለሁሉም ሰው የሚሆን ቤት እንዲገነቡ ፣የጋራ መኖሪያ የሆነውን ምድራችንን፣ የእግዚአብሔርን ቤት በማደስ ሌሎችን በእንግድነት ተቀብለው የሚያስተናግዱበትን ጥሪ መቀበላቸውን እንደሚያመለክትም ወ/ሮ ቼቺሊያ አስረድተዋል።

“የጋራ መኖሪያ ቤታችን” ለሚለው መሪ ሃሳብ ትኩረታቸውን የሰጡት ወ/ሮ ቼቺሊያ፣ ሥነ-ምህዳርን ከጉዳት ለመከላከል መወሰድ ያለበት እርምጃ እጅግ አስቸኳይ መሆኑን ገልጸው፣ የመላው ዓለም ክርስቲያን ማኅበረሰብ ቆም ብሎ በማሰብ፣ የሁላችን መኖሪያ የሆነውን ምድራችን ለመገንባት የሚያስችል ጸጋን ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመቀበል በጸሎት መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም የእግዚአብሔርን ቤት ለማደስ መነሳሳት የሚቻለው፣ እንደሌሎች ፍጥረታ ሁሉ ምድርም የእርሱ ፍጥረት መሆኗን ስንረዳ ነው ብለዋል። ይህ የጋራ መኖሪያ ምድራችን፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ የእግዚአብሔር ቤት የተሠራው በፍጥረታት መካከል ባለው መልካም ግንኙነት እንደሆነ ወ/ሮ ቼቺሊያ አስረድተዋል።  አክለውም ፈጣሪ ለሰው ልጅ መኖሪያ ቤቱን እንዲንከባከብ ልዩ ጥበብ እንደሰጠው እናውቃለን ያሉት ወ/ሮ ቼቺሊያ፣ ስለሆነም ፍትሃዊነት ያለው ሥነ-ምህዳራዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችን ለማሳደግ በአንድነት ተጠርተናል ብለዋል።          

የፍጥረት መታሰቢያ ወቅት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን የሚያሳትፍ መሆኑን የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እንቅስቃሴ ምሥራች አባል እና ዳይሬክተር ወ/ሮ ክርስቲና ሊኖ ገልጸዋል። ላለፉት ሰባት ዓመታት ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር መሥራታቸውን አስታውሰው፣ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፣ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አንድነት የወካዮች፣ ከአንግሊካን ቤተክርስቲያን፣ ከሉተራን ኅብረት እና ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በኅብረት መሥራታቸውን አስረድተዋል። በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው የአንድነት እና የመተጋገዝ ምኞት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም በተጨባጭ የታየ መሆኑን አስረድተዋል። እ. አ. አ በ2021 ዓ. ም. ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በኅብረት ለመፈጸም ያቀዷቸው ተግባራት መኖራቸውንም ገልጸዋል።        

03 September 2021, 14:47