ፈልግ

የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቅለት የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቅለት 

የመስከረም 9/2014 ዓ. ም ሰንበት መስቀል ዘፍሬ ቅዱስ ወንጌል እና የዕለቱ መልዕክቶች አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት፡- 2ኛ ቆሮ 9፡ 1-15 ፣ ያዕ 5፡1-9 ፣ ሐዋ 19፡21-40 ፣ ማር 4፡24-38

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

እንደ ቤተክርስትያናችን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር መሠረት የዛሬው ሰንበት  መስቀል ዘፍሬ በመባል ይታወቃል። በእነዚህ ጊዜያት ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በቃሉ አማካኝነት የተለያዪ ትምህርቶችና መልዕክቶች አስተላልፎልናል ።

በዚህም ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ንባቦች አማካኝነት ወደ እያንዳዳችን በመምጣት የሚያስፈልገንን ይሰጠናል የጎደለውን ሁሉ ይሞላልናል በእርሱም ቃል እንድንኖር ያበረታታናል።

በዚሁም መሠረት እንግዲህ በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ኛ የቆሮንጦስ መልዕክቱ የቆሮንጦስ ሰዎችን ሲያበረታታና  ሌሎችን ለመርዳት ስለሚደረግ አገልግሎት ሲያስተምራቸው እናያለን። በእርግጥ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ በ2ኛ የቆሮንጦስ መልዕክቱ የቆሮንጦስ ሰዎች የሚያስታውሳቸው በ8፡9 ላይ ያለዉን የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ምሳሌነት በመመርኮዝ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ መገመት ከምንችለዉና ማወቅ ከምንችለው በላይ በነገሮች ሁሉ ሃብታም ነው በዓለም ያለው ነገር በሙሉ የእርሱ ነው የዓለም ሃብት በሙሉ የእርሱ ነው የእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ የእርሱ ነው። ነገር ግን እንዲህ ሃብታም ሆኖ ሳለ ስለ እኛ ሲል ድሃ ሆነ። በእርሱ የድኅነት ሃብት እኛን ሃብታም አደረገን እኛን ባለ ጸጋ አደረገን።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይላል ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ታዲያ አምላክ ሆኖ ባለጸጋ ሆኖ ሳለ እንዲህ በድኅነታችን ካገዘን እኛስ ታዲያ እርስ በርሳችን እንዴት አንተጋገዝም? እንዴት አንዳችን ለአንዳችን አንተሳሰብም ይለናል። እነዚህ የቆሮንጦስ ሰዎች በእርግጥ ይህንን እገዛ መጀመራቸውን ያውቃል ነገር ግን ይህ የጀመሩትን የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰብ እስከ መጨረሻ እንዲቀጥሉበት ያበረታታቸዋል በዚህም እርምጃቸው እንዲያግዟቸው ቲቶንና ሌሎች ሁለት ወድሞችን ልኮላቸዋል። ከዚህ ጋር በታያያዘ እንደ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ አመለካከት አንድ ልናነሳው የሚገባን ነገር አለ ይኸውም በልግስናችን ሁሉ መልካም ፈቃድና ሙሉ ደስተኛነት በውስጣችን ሊኖር ይገባል ይላል። እንደ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሃሳብ ሌሎችን መርዳት ልክ ዘርን እንደመዝራት ይቆጠራል ይለናል። በልግስና ለምንሰጠው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር የልግስናችንን ዋጋ እንደሚከፍለን ይናገራል።

በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ በተለያዩ ቦታዎች በልግስና የሚሰጥ ስጦታ ስለሚያመጣልን በረከት ይናገራል። አብዛኛውን ጊዜ በዘልማዳዊ አነጋገር ሰው የሚያጭደው የዘራዉን ነው እንላለን እውነት ነው ሰው የሚያጭደው የዘራውን ነው። ይህም አነጋገር ለዓለማዊ አካሄድ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ አካሄኣችንም ያው ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል 10፡42 ላይ ስለዚህ ነገር በግልጽ ይናገራል እንዲህም ይላል ማንም ሰው ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውኃ በደቀ ማዝሙርት ሥም የሚሰጥ እውነት እውነት እላችኋለው ዋጋውን አያጣም። እንግዲህ ወደ እራሳችን እንመለስ ምን ያህል ጊዜ በሕይወታችን ይህንን ነገር ፈጽመናል? ምናልባት እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ ለተቸገሩት ወድሞቻችንና እህቶቻችን እረድተን ይሆናል ነገር ግን ይህንን የፈጸምነው በሙሉ ደስታና በወንድሞቻችን ችግርና ድህነት ከልባችን ለማሳተፍ ብለን ነው ወይስ ለታይታ ሰጡ ለመባል ብቻ ነው? እንግዲህ እዚህ ላይ ነው መጠንቀቅ ያለብን በእግዚአብሔር ፊት በረከት የሚያመጣልን በዚህ መንፈስ ያደረግነው እንደሆነ ብቻ ነው። እስቲ ሁላችንም ወደ ኋላ መለስ ብለን እናጢነው በሕይወት ዘመናችን ምንም ገንዘብ የሌላቸውን ድሆች በቤታችን ጋብዘናቸው ከእኛ ጋር እንዲውሉ ሁኔታዎችን አመቻችተን እናውቃለንን? አንድ ስኒ ቡና ጠጡ ብለን አብረናቸው ቁጭ ብለን እናውቃለንን? ወይስ ያው እንደተለመደው ብቻ ከኪሳችን ሳንቲም አውጥተን እንወረውራለን? እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ የሚጠይቀን ይህን ነው።

ገበሬ ዘሩን ሲዘራ የሚዘራው ፍሬ እንደጠፋ አያስብም እንደውም ይህ የተዘራው ፍሬ የበለጠ ብዙ ፍሬ እንደሚሰጠው መልካም መከር እንደሚሆን ያስባል ስለዚህ መልካም ፍሬ ለማግኘት መልካም ዘርን ይዘራል። የእኛም  ወደ እግዚአብሔርም መቅረብም ሆነ ለተቸገረ ሰው ስንረዳ እረዳን ለማልት ሳይሆን ወይንም ሰጠን ለማለት ሳይሆን ከልባችን ላደረግነው ነገር እግዚአብሔር ራሱ በመልካም እንደሚመልስልን በማሰብ ልናደርገው ይገባል። በሐዋርያት ሥራ በምዕራፍ 20 ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ሰው የተባረከ ነው ይላል ስለዚህ ይህ መስጠት ሁልጊዜ በመልካም ፈቃድ ላይ የተመረኮዘ የሚለውን ነገር በውስጡ መያዝ ይኖርበታል። በመዝሙረ ዳዊት 112፡9 ላይ ለድሆች የምናደርገው ማንኛውም ዓይነት ሥጦታ ከእግዚአብሔር ትልቅ በረከት እንደሚያመጣልንና ይህም ጽድቅ  ለዘለዓለምም እንደሚኖር ይናገራል ስለዚህ ልክ እንደ ገበሬው እኛም በልግስና ለምናበረክተው ነገር በእግዚኣብሔር ፊት ትልቅ ጸጋ እናቆያለን።

በልግስናችን ወቅት የምንችለውን ብቻ ማድርግ ይጠበቅብናል እንጂ ማድረግ ከምንችለው በላይ እግዚአብሔርም ቢሆን አይጠይቀንም። ነገር ግን ማድረግ የምንችለውን ትንሽም ቢሆን ካደረግን ዋናው ነገር የእኛ በዛ በረከት ውስጥ ማሳተፍ እንጂ ሁሉን የሚያበዛና በረከት በበረከት የሚያደርገው እግዚአብሔር እራሱ ነው። ለዚህም በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ላይ ያለውን የዛን ሕፃን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያበረከተውን አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ማንሳቱ በቂ ነው። ያ ብላቴና ያለውን ሰጠ እግዚአብሔርም ደግሞ በበረከቱ ይህን ትንሽ ሥጦታ ለአምስት ሺህ ሕዝብ እንዲበቃ አደረገው ስለዚህ እኛም ስንለግስ የምንችለውን ማድረግ ይጠበቅብናል በልግስናችን ትንሽነትና ትልቅነት ላይ ብዙም አንጨናነቅ የምንችለውን ብቻ እናድርግ። ያች መበለት ያላትን አንድ ሳንቲም ከልቧ በመስጠቷ ብዙ ሺህ ገንዘብ ለታይታ ካበረከቱት ጽድቅ ሆኖ ተቆጥሮላታል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በተጨማሪ ይህንን ያሳስበናል ለሌሎች ስለምናደርገው ሥጦታ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል ምክንያቱም ይህ መልካም ሃሳብና መልካም ድርጊት የሚመንጨው ከእግዚአብሔር ጸጋ ነውና ነው። የእግዚአብሔር ጸጋ የሌለው ሰው በውስጡ ለግስ ለግስ የሚል መንፈስ አይኖረውም እንደውም በአንጻሩ ከአለው ብዙ ነገር ቀንሶ ሲሰጥ ለእርሱ የሚያልቅበት ይመስለዋል ሃብቱ የሚቀንስበት ይመስለዋል ስለዚህ በውስጣችን የመስጠት የመለገስ መንፈስ ካለ ስለ እዚህ ሥጦታው እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባናል። እኛ የክርስቶስ ተከታዮች ነን ስንል እንደው ለሥም ብቻ መሆን የለበትም በትክክለኛ መንፈስ የእርሱ ተከታዮች መሆናችንን በተግባር ልናስመሰክር ይገባል። ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ በተግባር የማይመነዘር እምነት ከንቱ ነው የሚለን ለዚህ ነው። ክርስቶስን ምንም ያህል እንወደዋለን ብንል ነገር ግን ተግባራችን ያንን የሚያስመሰክር ካልሆነ አለን የምንለው እምነት አለን የምንለው ፍቅር  በትክክለኛ መስመር ላይ እንዳልሆነ ልንገነዘብና ልናስተካከል ይገባናል።

በዛሬው በሁለተኛ መልዕክት ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ መልዕክቱን ሃብታም ለሆኑ ሰዎች ያስተላለፋል። እዚህ ጋር ሃብታሞች ስንል ሃብታቸው በትክክለኛ መንገድ ያልተከማቸ ሰዎችን በተለይም ደግሞ የድሆችን ጉልበትና የላባቸውን ዋጋ በመከልከል በተከማቸ ሃብት የበለጸጉትን ይመለከታል። ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ እንደሚለው ሃብታችሁ ተበላሽቷል ልብሳችሁም በብል ተበልቷል ይላል ይህም ማለት በድሆች እንባ በድሆች ጉልበት አላግባብ እናንተ በልጽጋችኋል ስለዚህ የእነሱ እንባና ጉልበት በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ አሳጥቷችኋል ይህም ደግሞ ወደፊት ከባድ መከራ ያመጣባችኋል ይላል በተለይም ደግሞ በመጨረሻው ዕለት በእግዚአብሔር ፊት ይመሰክርባችኋል ይላል።

አንድ ሰው ሃብትን በተሳሳተ መገድ ሲያከማች ገና ከጅምሩ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት ተበላሽቷል ማለት ነው ምክንያቱም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው በእርሱ አምሳያ የተፈጠሩትን ሁሉ ያከብራል የሚገባቸውንም አይከለክልም ምክንያቱም በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን መንፈስ ይፈራል ያከብራልም። እግዚአብሔርን የሚያክብር ሰው ሰውን ሁሉ ያከብራል እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ሰውን ሁሉ ይፈራል በተመሳሳይ መልኩ የሰውን የልፋቱን ዋጋ የሚከለክል ሰው ወደ እግዚአብሔር በምን ድፍረት ሊቀርብ ይችላል? ምክንያቱም ያታለለው ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርንም ጭምር ነው።

በ1ኛ የቆሮንጦስ 13 ላይ በዓይኑ የሚመለከተውን ወንድሙን የሚጠላ እንዴት አድርጎ በዓይኑ ያላየውን እግዚአብሔርን እወዳለሁ ሊል ይችላል? ይላል ስለዚህ በዓይኑ የሚመለከተውን ወንድሙን የሚበድል ሰው እንዴት በዓይኑ ያላየውን እግዚአብሔርን እወዳለው አከብራለሁ ሊል ይችላል? እግዚአብሔርንና ሰውን መውደድ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ማንም ሰው እግዚአብሔርን ወዶ ሰውን ሊጠላ አይችለም ወይም ደግሞ ሰውን ጠልቶ እግዚኣብሔርን ሊወድ አይችልም። እግዚአብሔርን መውደዳችንን ለማረጋገጥ በዙሪያችን ካሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ድሆች ጋር ያለንን ግንኙነት መመልከቱ በቂ ነው።

ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ በመቀጠል በመከራ ውስጥ መታገስ መልካም እንደሆነ ይናገራል። ይህ ማለት መከራን ለማሸነፍ ጥረት መደረግ የለበትም የሚል ነገር አያሰማም ነገር ግን በሚቻለን ሁሉ እግዚአብሔር በሚስጠን ጸጋ ሁሉ በመጠቀም እግዚአብሔር በሰጠን አእምሮ በመጠቀም ችግራችንን ሁሉ ለመቅረፍ የሚገባንን ማድረግ ይጠበቅብናል። ሥራም መሥራት ካለብን በሚገባ መሥራት ያስፈልጋል ምክንያቱም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሥራን ሲፈጥር እንደ ትልቅ ጸጋ እንጂ እንድ አንድ እዳ አልሰጠውም። እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ሲፍጥር በኤደን ገነት ያኖራቸው እግዚአብሔር የፈጠረውን ሁሉ እንዲንከባከቡ ነው እንዲሠሩ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባቱን በአናጢነት ሙያ ያግዝ ነበር ሐዋርያቶች ሁሉ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚጠቅሰው ሁሉም ሥራ ይሠሩ ነበር። ስለዚህ በመከራ ውስጥ መታገስ ማለት በቃ የደረሰብኝን መከራ ለማሻሻል ለማስተካከል ጥረት ማድረግ አይጠብቅብኝም ምክንያቱም ይህ እጣ ክፍሌ ነው ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ተገቢ አይደለም። እግዚአብሔር ማስተዋልን የሰጠን ለዚህ ነው ከእንስሳት ሁሉ ለይቶ አእምሮን የሰጠን ለዚህ ነው። ነገሮች ሁሉ እንዴት መሆን እንዳለባቸው እንዴት መጓዝ እንዳለባቸው እንድናውቅና ወደ ትክክለኛ መስመር እንድናመጣቸውና በትክክለኛ መንገድ መመላለስ እንድንችል ነው ይህንን ለማድረግ ግን ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ እንደሚለው ትዕግስት ማድረግ ይገባል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ 5፡22 ላይ እንደሚገልፀው ትዕግስት ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች አንዱ ነው ስለዚህ በየትኛውም ፈተና ጊዜ ትዕግስት ማድረግ ይገባል።  ትዕግስት ያለው ሰው ወደ ሚፈልግበት ቦታ መድረስ ይችላል ትዕግስት ያለው ሰው ያሰበውን ዕቅድና ዓላማ ሁሉ ለማሳካት ይችላል ትዕግስት ያለው ሰው ወደፈተና ቶሎ አይገባም ቢገባም በእግዚአብሔር እርዳታ በእርጋታ እንዴት መውጣት እንዳለበት ያውቃል። ስለዚህ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ ትዕግስት በማድረግ ወዳስብንበትና ወደ ተጠራንበት የቅድስና ሕይወት መድረስ እንችላለን። ይህ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ የሆነ ትዕግስት ወደ ውስጣችን ዘልቆ እንዲገባ ዘወትር የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ መለመን ያስፈልገናል።

በዛሬም በማርቆስ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምንሰፍርበት መሥፈሪያ እንድሚሰፈርልን ይነግረናል ይህም ማለት በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት እጅግ ጠንካራና ሙሉ ከሆነ በምነም ነገር አንናወጥም ምክንያቱም ላለው ይጨመርለታል እንደተባለው ባለን እምነት ላይ ስለሚጨመርልን እምነታችን የበለጠ ሙሉ ይሆናል ይህ ደግሞ በክርስትና እምነታችን ላይ የበለጠ ጥንካሬና ተስፋ ሰንቀን አንድንጓዝ ያግዘናል። እምነታችን ደካማ ከሆነ ግን የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው ከሌለው ያው ያለችው እንኳን ትወሰድበታለች ይላልና ያቺም ትንሿ እምነታችን ከእኛ ተወስዳ ለሌላ ትሰጣለች ስለዚህ የእኛ ሕይወት በምድራዊም ሆነ በሰማይ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ እምነታችን እንዲቀንስ ሳይሆን ዘውትር በእግዚአብሔር ጸጋ እንዲበዛ ጥረት ማድረግ ይጠብቅብናል ይህን ካደረግን ለምኑ ይሰጣችኋል ፈልጉ ታገኛላችሁ በሚለው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ሁሉን ነገር በእጃችን ማስገባት እንችላለን።

እግዚአብሔር ለሰዎች የተለያዩ ሥጦታዎችን የሚሰጠው እንድንጠቅምባችው ነው ካልተጠቅምንባቸው ከእኛ ተወስደው ለሚጠቀሙባቸው ሰዎች እንደሚሰጡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ላይ ይናገራል። ሌላው በዚሁ በማቴዎስ ወንጌል ላይ ስለ ዘር ምሳሌ ይናገራል። ከዚህ ቀደም ባሉት መልዕክቶች ላይ አንድ ገበሬ በምን ተስፋ ዘሩን እንድሚዘራ ተመልክተናል በትልቅ ተስፋ ዘሩን ይዘራል። ገበሬው የሚዘራውን ዘር ያበቀልኩት እኔ ነኝ ሊል አይችልም የሱ ሥራ ዘሩን በተስፋ መዝራት ብቻ ነው የቀረውን ሁሉ የሚያከናዉነው እግዚአብሔር ራሱ ነው።እኛም በክርስትና ሕይወታችን እንዲህ ነን በተልቅ ተስፋ ወደ እግዚአብሔር ከተጠጋን እርሱ ሁሉን ነገር ያከናውንልናል። በውስጣችን ያለችውን ትንሿን የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክለውን እምነታችንን ይዘን ወደ እርሱ ከሔድን ከጅምሩ ትንሽ ብትሆንም ኃላ ግን ታድጋለች ከዛፎች ሁሉ ትበልጣለች በቅርንጫፎችዋም ላይ ብዙ ወፎችን ታስጠልላለች። የእኛም እምነት እንዲሁ ነው በእግዚአብሔር ላይ እምነቱን ያስቀመጠ ሰው በመጀመሪያ ደረጃ ለራሱ በመንፈስም በሥጋም በኣስተሳሰብም በሁሉም ዘርፍ ያድጋል በስተመጨረሻም ለሌሎች ሰዎች ሁሉ መከታና መጠለያ ይሆናል በእርሱም አማካኝነት ብዙ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲመለሱ ምክንያት ይሆናል።

እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው በልቡ ውስጥ ይህንን የእምነት ፍሬ ገና ሰው ሆኖ ሲፈጠር ኣስቀምጧል ይህ የእምነት ፍሬ እንዲያድግ መንከባከቡ ግን የእያንዳዳችን ግዴታ ነው። ይህ ፍሬ አንዱ 30 አንዱ60 አንዱ 100 ያፈራል ባፈራንበትም መጠን ሽልማታችንን ወይም ደግሞ ቅጣታችንን እንቀበልበታለን ምን አልባት እግዚአብሔር በውስጣችን ያስቀመጠው ፍሬ ከጠፋና ወይ ከሞተ ኃላፊነታችንን ባለመወጣት የተከሰተ ነገር እንጂ እግዚአብሔር ያስቀረብን ነገር ስላለ አይደለም የሕይወት እጣ ክፍላችን ስለሆነም አይደለም ስለዚህ ሁላችንም በተቻለን መጠን በመጨረሻ ጊዜ ወደ እርሱ ስንሄድ እንዳናፍር አንገታችንን እንዳንቀረቅር ከወዲሁ ለክርስትና ሕይወታችን ዋጋ እንስጠ። ለዚህም ደግሞ የዘውትር ጠባቂያችንና አማላጃችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልካም ዘር በተስፋ የምንዘራበትን ጸጋ ከአንድያ ልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን። በጉዞኣችን በሥጋና በመንፈስ ለመታደስ እንድንችል ሁሉ ጊዜ ከጎናችን ትቁምልን በእግዚአብሔር ፊት በድካማችን ለፈጠርነው ስህተት ሁሉ ጠበቃ ሁና ትቁምልን።

የሰማነውን ቃል በተግባር ለማዋል እንድንችል ዘወትር በጸጋዋ ታግዘን!

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

18 September 2021, 09:58