52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ 

አቡነ ማሪኒ፣ “የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት በቅዱስ ቁርባን እናረጋግጣለን!”

በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ነሐሴ 30/2013 ዓ. ም. ተጀምሮ በመካሄድ ላይ በሚገኝ ለ52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ተካፋዮች የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ያሳረጉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፔሮ ማሪኒ፣ “ምንጮቼ ሁሉ በአንተ ውስጥ ናቸው” በሚለው በጉባኤው መሪ ቃል ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከት፣ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ማረጋገጥ የሚቻለው በቅዱስ ቁርባን መሆኑን አስረድተው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ፣ ቅዱስ ወንጌልን ልብን በሚነካው እና በሚለውጥ የሕይወት ምስክርነት ለመመስከር ያስችላል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቡዳፔስት የሚካሄደው 52ኛ የቅዱስ ቁርባን ዓለም አቀፍ ጉባኤ፣ ትናንት ጳጉሜ 1/2013 ዓ. ም. የአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ባኛስኮ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት መከፈቱ ይታወሳል። አምና ሊካሄድ የነበረው የዘንድሮ ጉባኤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መተላለፉ ይታወሳል። በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ሁለተኛ ቀኑን በያዘው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ለተገኙት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ካህናት እና ምዕመናን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን የመሩት፣ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ጳጳሳዊ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፔሮ ማሪኒ፣ ጉባኤው ካህናት በዕለት ተዕለት ሕይወት ጉዞ ላይ ቅዱስ ቁርባንን መኖር እንዳለባቸው የሚያስተምር መሆኑን በስብከታቸው ገልጸው፣ በየዕለቱ የሚቀርበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የምሕረት ጸጋን የምንቀበልበት፣ የእግዚአብሔርን ቃል የምንሰማበት፣ ከሁሉም በላይ ምስጋናን የምናቀርብበት እና ቅዱስ ቁርባንን ተቀበለን አንድነታችንን የምንገልጽበት ነው ብለዋል።

የፍቅር ሕግ

በዕለቱ በተነበቡት ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፔሮ ማሪኒ፣ በሁለት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ በማትኮር የመጀመሪያው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበት የፈጸመው የሽባ ሰው እጅ የፈውስ አገልግሎት እና ፈሪሳውያን ከሚያረጋግጡት በተቃራኒ፣ በሰንበት የሚቀርብ የፈውስ አገልግሎት ሰውን ለማዳን የተደረገ አገልግሎት እንጂ በሰው ላይ ሸክምን ለመጫን በእግዚአብሔር የተቋቋመ ሕግ አለመሆኑን አስረድተዋል። የነጻነት ሕግ የፈለቀበት፣ ለሰው ልጆች ሕይወትን ለመስጠት የእግዚአብሔር የማዳን ኃይል የሆነው ፍቅር የተገለጠበት ነው በማለት አስረድተዋል።

ኢየሱስ ፣ መለኮታዊ ሐኪም ነው

በወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው እጀ ሽባ ሰው፣ በሕመም የሚሰቃይ እና ከዚህ ሕመም መፈውስ ያለበት መላውን የሰውን ልጅ የሚያመለክት መሆኑን ገልጸው፣ መለኮታዊ አዳኝ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ልጅ ውስጥ ተሰውሮ የሚገኘውን ሥጋዊ ሆነ መንፈሳዊ ሕመሞችን መፈወስ የሚችል ኢየሱስ መሆኑን ያስረዳል ብለዋል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው ታማሚ ሰው በሕመም እና በሌሎች ምክንያቶች ከሥራ ገበታቸው የተገለሉትን ሰዎች እንድናስታውስ አድርጎናል ብለዋል።

ቅዱስ ቁርባን ለእኛ ኃጢአተኞች መፈወሻችን ነው

በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው ሰው ያስታወሱት የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ጳጳሳዊ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፔሮ ማሪኒ፣ ያ ሰው ፈወስን ለማግኘት እንደሚጠባበቅ ሁሉ እያንዳንዱ ምዕመን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ በሙላት በመሳተፍ፣ ከቅዱስ ቁርባን የሚገኘውን ፈውስ እንዲያገኝ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

07 September 2021, 17:06