ፈልግ

በፖላንድ የተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በፖላንድ የተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል 

የአውሮፓ ወጣት ካቶሊካውያን፣ ወንድማማችነትን የበለጠ እንዲያሳድጉ ጥሪ ቀረበላቸው

የአውሮፓ ወጣት ካቶሊካውያን በመካከላቸው ያለውን ትብብር እና ወንድማማችነት የበለጠ እንዲያሳድጉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን ጥሪውን ያቀረቡት የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች መሆናቸው ታውቋል። ብጹዕነታቸው አክለውም ወጣቶቹ የወደ ፊት ብቻ ሳይሆን የዛሬ አውሮፓ ተስፋዎች መሆናቸውንም አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአውሮፓ ካቶሊካውያን ወጣቶች አህጉሩ የተመሰረተበትን የአብሮነት ፣ የወንድማማችነት እና የመከባበር እሴቶችን ጠብቆ የበለጠ እንዲተባበሩ በማለት የአውሮፓ ኅብረት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት በሪፖርቱ አሳስቧል። ምክር ቤቱ ይህን ለማስተባበር የሚያግዙ ተጨባች የፖሊሲ ሀሳቦች እና ጥቆማዎች በሰኔ ወር 2013 ዓ. ም ከተካሄደው የአውሮፓ ወጣቶች ጉባኤ የተግባር እቅድ ውስጥ ማግኘቱን ሪፖርቱ አስታውቋል። በሰኔ ወር 2013 ዓ. ም የተካሄደው የአውሮፓ ወጣቶች ጉባኤ፣ ከመቶ በላይ የወጣት ማኅበራት ተወካዮችን፣ በብዛትም ከአውሮፓ ሕብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች የተወከሉ ወጣቶችን እና ከአሥር በላይ የሚሆኑ የወጣት ካቶሊካዊ ማኅበራት ተወካዮችን ማሳተፉ ታውቋል።

በአውሮፓ የወደፊት ዕጣ ላይ ሦስት ዌብናሮች ተካሂደዋል

ያለፈው 2013 ዓ. ም ሰኔ ወር ውስጥ በተካሄዱት ሦስት የአውታረ መረብ ላይ ስብሰባዎች፣ የ COVID-19 ወረርሽኝ ካስከተለው ቀውስ በኋላ በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ለውጥን ለማምጣት እንዲቻል አውሮፓዊያንን ፣ በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙ ተቋማትን እና ድርጅቶችን ያሳተፈ የውይይት ሂደት መካሄዱ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ለአውሮፓ ኅብረት አገሮች ያስተላለፉትን መልዕክት መሠረት ያደረገው  የአውሮፓ ካቶሊካውያን ወጣቶች ስብሰባ፣ በሦስት ጭብጦች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ እነርሱም ፍትሃዊነትን የተላበሰ ማህበራዊ መልሶ ግንባታ፣ የሥነ -ምህዳር እና የዲጂታል ሽግግሮች፣ ዴሞክራሲ እና የአውሮፓ እሴቶች የሚሉ መሆናቸው ይታወሳል። ወጣቶቹ ያካሄዷቸው ውይይቶች በሥነ -ምህዳር ፣ በዲጂታሉ ዓለም እና በወጣቶች የተሳትፎ ዘርፎች ውስጥ ልምድ ባላቸው ባለሞያዎች በኩል የቀረቡ በርካታ ግብዓቶችን እና ድጋፎችን ማግኘታቸው ታውቋል።

ለተጎጂ ቡድኖች ወጣቶች የሚደረግ ድጋፍ

የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት፣ ጳጉሜ 4/2013 ዓ. ም ያቀረበው የባለ 13 ገጽ የመጨረሻ ሪፖርት፣ በመላው አውሮፓ ውስጥ የሚገኙ ወጣት ካቶሊካውያን ፍላጎቶችን እና ስጋቶች፣ የሕብረቱ የወደፊት ዕጣቸውን የሚመለከቱ ቀዳሚ የመፍትሄ ሃሳቦችን ይፋ ማድረጉ ታውቋል። ፍትሃዊ ማህበረሰብን መልሶ መገንባትን በተመለከተ ከተሳታፊዎቹ የቀረቡ ሃሳቦች፣ በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙ ትውልዶች እና አገሮች መካከል ልዩነት ሳይደረግ የበለጠ ተቀራርበው፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸት፣ የሞያ ብቃታቸውን ማሳደግ ፣ የዕድሜ ልክ ስልጠና ዕድሎችን ማመቻቸት በሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ትኩረትን በመስጠት፣ በአንድነት እና በወንድማማችነት አስፈላጊነት ላይ አፅንዖትን መስጠቱ ታውቋል። የጉባኤዎቹ ምክር ቤት ሪፖርት አክሎም፣ ጉዳት ከደረሰባቸው ማኅበረሰቦች ለሚመጡ ወጣቶች ልዩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ በዘላቂ የእድገት ዕቅዶች ውስጥ መሳተፍ እንዲችሉ በቂ ሥልጠናን መስጠት የሚያስፈልግ መሆኑን አስታውቋል። የቤተሰብ ሕይወትን በማሳደግ፣ የመረዳዳትን ባሕል ማሳደግ እንደሚገባ እና ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ዘላቂነት እንክብካቤን ማድረግ

ሥነ-ምሕዳርን እና ዲጂታል ሽግግርን የተመለከተው ሪፖርቱ፣ በዕለታዊ ሕይወት መካከል ለሥነ-ምህዳር እና ለዘላቂ የዲጂታል ማኅበረሰብ ግንባታ ትኩረትን በመስጠት የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ከፍተኛ ሚናን እንዲጫወቱ፣ የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ በእንግሊዝ፣ ግላጎው ከተማ በሚካሄድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

ክርስቲያናዊ እሴቶችን ማሳደግ

የአውሮፓ ዴሞክራሲ እና እሴቶች የሚለውን ርዕሠ ጉዳይ የተመለከተው ሪፖርቱ፣ በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ወጣቶችን ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጾ፣ በተለይም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ወጣቶች ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሷል። ለአውሮፓ ማኅበረሰብ በቂ መረጃን በማዳረስ፣ የአውሮፓ አዲሱ ትውልድ አንድነት፣ ወንድማማችነት እና እርስ በእርስ መከባበር ያለበትን ክርስቲያናዊ የዴሞክራሲን እና የአንድነት እሴቶችን በሚገባ እንዲያውቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አሳስቧል።

“የዛሬዪቱ አውሮፓ ወጣቶች ናችሁ!”         

የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች፣ በስምምነቱ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ ወጣቶች የዘመናችንን አንገብጋቢ ጉዳዮችን በመቋቋም መፍታትን ማግኘት እንደሚችሉ ያላቸው እምነት ገልጸዋል፣ ወጣቶች የወደ ፊት ብቻ ሳይሆን የዛሬ አውሮፓ ተስፋዎች መሆናቸውን አስርድተው “ወጣቶች ባካበቱቷቸው ልምዶች፣ ዕውቀቶች እና ተስፋዎች በመታገዝ የተሻለ አውሮፓን ለአውሮፓዊያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለማችን ወንድሞች እና እህቶች መገንባት ይችላሉ” ብለዋል።

21 September 2021, 16:40