ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት 

በስሎቫኪያ የምትገኝ ቤተክርስቲያን ለኩባ ችግረኞች ዕርዳታን ማሰባሰብ ጀምራለች

የስሎቫኪያ ካቶሊካዊ ምዕመናን በኩባ ለሚገኙ ችግረኛ ወንድሞች እና እህቶች ዕርዳታ ማሰባሰብ ጀምረዋል። ዕርዳታን የማሰባሰቡ መርሃ ግብሩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ወደ ስሎቫኪያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ውጤት መሆኑ ሲነገር፣ ምዕመናኑ ዕርዳታውን የሚሰበስበው እሑድ መስከረም 16/2014 ዓ. ም. መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የስሎቫኪያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እንዳስታወቀው፣ ከስሎቫኪያ ምዕመናን የሚሰብሰብ ዕርዳታ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ጨምሮ በከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ የሚገኘውን የኩባ ሕዝብ ለመደገፍ የታሰበ መሆኑን አስረድቷል። የስሎቫኪያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ያስጀመሩት የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ሃሳብ የመነጨው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከመስከረም 2 - 5/2014 ዓ. ም. ድረስ በስሎቫኪያ ካደረጉት 34ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት መሆኑ ታውቋል። የስሎቫኪያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በጉባኤው ድረ ግጽ ላይ ባሰፈሩት የእርዳታ ጥሪ፣ ምዕመናኑ ቸርነታቸውን በመግለጽ ዕርዳታቸውን እንዲለግሱ አሳስበው፣ ዕርዳታቸውን ወደየቁምስናቸው የሚያቀርቡትም እሑድ መስከረም 16/2014 ዓ. ም. መሆኑ አስታውቀዋል። ጳጳሳቱ በዕርዳታ ጥሪያቸው የተቸገሩ ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን እንዲረዱ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውሰው፣ “ዕርዳታ ባስፈልገን ጊዜ ሌሎች እንደረዱን ሁሉ እኛም ልንረዳቸው ይገባል” ብለዋል።

የኩባ ተግዳሮቶች

የኩባ ኤኮኖሚ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ማሽቆልቆል የታየበት መሆኑ ሲነገር፣ የሕዝቡ የኑሮ አለመመጣጠን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተባብሷል ተብሏል። ባለፈው ሐምሌ ወር በአሥር ዓመታት ውስጥ ትልቅ የተባለ ፀረ መንግሥት ስልፍ ተካሂዶ ማለፉ ሲታወስ፣ በዚህ ሰልፍ አማካይነት የኩባ ሕዝብ የደረሰበትን መሠረታዊ የፍጆታ ቁሶች እጥረት፣ የጤና እንክብካቤ መጓደል እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ  ቀውስ መግለጹ ይታወሳል።

ሰልፉ ከመካሄዱ አስቀድሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው የጉዞ መታቀብ ምክንያት የአገሪቱን ዋና የገቢ ምንጭ የተባለለት የቱሪዝም እንዱስትሪ ሙሉ በሙሉ መዘጋቱ ይታወሳል። ከዚህም በተጨማሪ አገሪቱን ያጋጠማት የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት እያደገ ከመጣው የዋጋ ግሽበት ጋር ተዳምሮ የኩባን ሕዝብ ብሶት መጨመሩ ታውቋል።

በኩባ ውስጥ አዲስ የዴልታ ቫይሬስ መከሰቱ ለተጨማሪ የኮሮና ቫይሬስ ጉዳት የዳረጋት ሲሆን፣ ይህም በአገሪቱ ቀድሞውኑ በተዳከመ የጤና ስርዓት ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠሩ ታውቋል። በኩባ ውስጥ ወደ 790,000 የሚደርሱ ዜጎች በኮሮና ቫይሬስ ወረርሽኝ የተጠቁ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከ6000 በላይ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። በኩባ ውስጥ የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ እስካሁን ከ15 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች መታደላቸው ታውቋል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ኩባ የራሷን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት ማዳረስ መጀመሯ በዓለማችን የመጀመሪያ አገር አድርጓታል ተብሏል።        

20 September 2021, 17:17