የማርያም ደስታ የመነጨው ከእግዚኣብሔር ነው የማርያም ደስታ የመነጨው ከእግዚኣብሔር ነው 

የማርያም ደስታ የመነጨው ከእግዚኣብሔር ነው

የነሐሴ 16/2013  ዓ.ም የፍልሰታ ማርያም በዓል የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.     ዮሐንስ ራዕይ 11፡19, 12፡1-6

2.     መዝሙር 44

3.     1 ቆሮ. 15፡20-26

4.     ሉቃስ 1፡39-56

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ማርያም ኤልሳቤጥን ጥየቃ ሄደች

ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሎአልና። ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”

የማርያም መዝሙር

ማርያምም እንዲህ አለች፤ “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤

እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቶአልና። ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤ ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።

በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቶአል፤ በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኖአቸዋል፤ ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤ ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጎአቸዋል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአቸዋል፤ ሀብታሞችን ግን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል፤ ምሕረቱን በማስታወስ፣ ባሪያውን እስራኤልን ረድቶአል፤ ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣ ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።” ማርያምም ሦስት ወር ያህል ኤልሳቤጥ ዘንድ ከቈየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች።

የእለቱ አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳቺሁ!

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን የፍልሰታ በዓል በምናክብርበት በዛሬው ቀን የተነበበልን የቅዱስ ወንጌል ቃል (ሉቃስ 1፡36-56) ውስጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች” (ሉቃስ 1፡46-47) በማለት ትጸልያለች። በእዚህ ጸሎት ውስጥ “ከፍ ከፍ ታደርገዋለች እና ሐሴት” ታደርጋለች የሚሉትን ግሶች እንመልከት። ሐሴት የምናደርገው በሕይወታችን ውስጥ በጣም ውብ የሆነ ነገር ሲከሰት እንዲሁ በውስጣችን ያለውን ደስታ በቀላሉ በመግለጽ ሳይሆን ነገር ግን ነፍሳችንን እና መላው ሰውነታችን ተሳታፊ በሚሆኑበት ሁኔታ በተቀናጀ መልኩ ሐሴት በማድረግ ለመግለጽ እንፈልጋለን። የማርያም ሐሴት የመነጨው ከእግዚኣብሔር ነው። ማን ያውቃል እኛም በሕይወታችን ውስጥ በጌታ ተደስተን ደስታችንን በሐሴት ገልጸን ሊሆን ይችላል፣ በአንድ ነገር ውጤታማ በምንሆንበት ወቅት ተደስተን ሊሆን ይችላል፣ መልካም የሆነ ዜና ሲያጋጥመን ደስታችንን ገልጸን ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ዛሬ ማርያም በጌታ እንዴት ሐሴት ማደረግ እንደ ሚቻል ታስተምረናለች፣ ምክንያቱም እርሱ “ታላላቅ ነገሮችን አድርጎልናልና”።

በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥሙን ታላላቅ የሚባሉ ክስተቶች ደግሞ ታላቅ ነገር ያደረግልንን አካል ከፍ ከፍ እንድናደርግ ያነሳሳናል። በእውነቱ ከፍ ከፍ ማደረግ ማለት ለታላቅነቱን፣ አንድ ታላቅ የሆነን ነገር በእውነቱ ከፍ ማደረግን የሚያመልክት ሲሆን ለታላቅነቱ እና ለውበቱ እውቅና በመስጠት እርሱን ከፍ ከፍ ማደረግ ማለት ነው። ማርያም የጌታን ታላቅነት ከፍ ከፍ ታደርጋለች ፣ በእውነት ታላቅ ነው ብላ አመስግነዋለች። በህይወት ውስጥ ታላላቅ ነገሮችን መሻት አስፈላጊ ነው ፣ አለበለዚያ ብዙ ትናንሽ ነገሮች እንወሰዳለን። ሕይወታችን ደስተኛ እንዲሆን ከፈለግን፣ በሕይወታችን ውስጥ ለእግዚአብሔር ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ማርያም ታሳየናለች፣ እርሱ ብቻ ታላቅ እንደ ሆነ ታስምረናለች። እነዚህን ታላላቅ የሚባሉ ነገሮችን ወደ ጎን በመተው ብዙ ጥቅም የማይሰጡ ነገሮችን ለምሳሌም ጭፍን ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ብጥብጥ ፣ ምቀኝነት ፣ ከልክ በላይ በሆነ መልኩ ለቁሳቁሶች ያለንን ፍላጎት . . .  ወዘተ የምንክተልባቸው ብዙ ወቅቶች አሉ። በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ስህተት እንፈጽማለን። ዛሬ ማርያም ጌታ በእርሷ ውስጥ ያከናወናቸውን “ታላላቅ ነገሮች” እንድንመለከት ዛሬ ትጋብዘናለች።

ዛሬ የምናከብራቸው “ታላላቅ ነገሮች” ናቸው። ማርያም ወደ ሰማይ ፈልሳለች፣ ትንሽ እና ትሑት የሆነች ማርያም ከሁሉም በፊት ከፍተኛ ክብርን ተቀበለች። እንደ እኛ ፍጡር የሆነች እርሷ በነፍስ እና በሥጋ ዘላለማዊ ትሆናለች። እናቶች ልጆቻቸው ከሄዱበት ቦታ ወደ ቤት እስኪመለሱ ድረስ እንደ ሚጠብቁ ሁሉ እርሷም እኛን በእዚያ በሰማይ ቤት ሆና ትጠብቀናለች። በእርግጥ የእግዚኣብሔር ሕዝቦች ሁሉ እርሷን “የሰማይ ደጃፍ” እያሉ ነው የሚያወድሱዋት። እኛም ወደ ሰማይ ቤት የምንጓዝ ምጻተኞች ነን። ዛሬ ማርያምን ቀና ብለን ወደ ሰማይ እንመለከታለን፣ በእዚያም የእኛ መዳረሻ የሆነውን ግባችንን እናያለን። አንድ እንደኛ ፍጡር የሆነች ከሙታን ወደ ተነሳው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር እንደ ተወሰደች እናያለን፣ ያቺ እንደኛ ፍጡር የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዳኛችን እናት በመሆን ከጎኑ ትቀመጣለች። በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ አዲሱ አዳም የሆነው ክርስቶስ አዲሲቷ ሔዋን ከሆነችው ማርያም ጋር በጋራ በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ እናያቸዋለን፣ እኛም በእዚህ ምድር ምጻተኞች ሆነን በምንኖርበት ጊዜ ለእኛ ታላቅ የሆነ መጽናናትን እና ተስፋን ይሰጠናል።

የማርያምን የፍልሰታ አመታዊ በዓል በምናክብርበት በአሁኑ ወቅት ለሁሉም የሰው ልጆች በተለይም በጥርጣሬ እና በሐዘን ለተሰቃዩ እና ዓይኖቻቸውን ወደ ታች ወደ ምድር አቀርቅረው ለሚገኙ ሰዎች ጥሪ ያቀርባል። ቀና ብለን ክፍት የሆነውን ሰማይ እንመልከት፣ ፍርሃት ሊያድርብን በፍጹም አይገባም፣ በጣም ሩቅ የሆነ ሥፍራም አይደለም፣ ምክንያቱም በሰማይ ደጃፍ ላይ የምትጠብቀን አንድ እናት አለችና። የሰማይ ንግሥት የሆነቺው እርሷ የእኛም እናት ናት። እርሷ ትወደናለች፣ ፈገግታዋንም ታሳየናለች፣ ትንከባከበናለችም። እያንዳንዷ እናት ለልጆቿ የተሻለውን ነገር እንደ ምትፈልግ እና እንደ ምታስብ ሁሉ “በእግዚአብሔር ፊት ውድ ነህና ፣ እናንተ የተፈጠራችሁት ትንንሽ የሆኑ የአለም ነገሮችን ለመፈጸም አይደለም፣ ነገር ግን እናንተ የተፈጠራችሁት ለሰማይ ታላቅ ደስታ ነው” በማለት ተናገረናለች። አዎን! ምክንያቱም እግዚአብሔር አስደሳች ነው እንጂ አሰልቺ አይደለም። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እጃችንን ይዛ እንድትመራን እንፍቀድላት። በእያንዳንዱ ቀን መቁጠሪያችንን በእጃችን ይዘን የመቁጠሪያ ጸሎት በምናደርግበት ወቅቶች ሁሉ ሕይወታችን ወደ ላይ አንድ እርምጃ እንዲራመድ እናደርጋለን ማለት ነው።

በእውነተኛ ውበት እንማረክ፣ ትናንሽ ወደ ሆኑ ነገሮች አንግባ፣ ነገር ግን የሰማይ ታላቅነትን እንምረጥ። ቅድስት ድንግል እና የሰማይ ደጃፍ የሆነቺው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደስታ እና በመተማመን እውነተኛ የሆነውን የሰማይ ቤታችንን ብቻ በእየለቱ መመልከት እንችል ዘንድ እንድትረዳን አማላጅነቷን መማጸን የገባል።

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የማርያም ደስታ የመነጨው ከእግዚኣብሔር ነው” አሉ

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በነሐሴ 09/2011 ዓ.ም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ሰማይ ያረገችበት የፍልሰታ በዓል ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህንን ታላቅ በዓል በምናከብርበት ወቅት ምልከታችንን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በምትገኝበት በሰማያዊው ቤታችን ላይ በማድረግ በዚያ ልጇ በምገኝበት ሰማያዊ ክብር ላይ አስተንትኖ እንድናደርግ የዛሬው ቀን ስርዓተ አምልኮ ይጋብዘናል

ምንጭ፡ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ምዕመናን ዘንድ በነሐሴ 09/2011 ዓ.ም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ እና በነብስ ወደ ሰማይ ያረገችበት የፍልሰታ በዓል በቫቲካን በተከበረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

21 August 2021, 21:30