በኢትዮጵያ ውስጥ ሕጻናት በትምህርት ገበታ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕጻናት በትምህርት ገበታ ላይ 

በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሕጻናት ተብሎ አዲስ የዕርዳታ ዕቅድ መዘርጋቱ ተነገረ

በኢትዮጵያ ውስጥ ሕጻናት በቂ የሕክምና አገልግሎት የማግኘት እና በመልካም አስተዳደግ የወደ ፊት ሕይወታቸውን የመገንባት መብት ያላቸው መሆኑን በሮም ከተማ “ባምቢኖ ጄሱ” በመባል ከሚታወቅ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ለሕጻናት ሰብዓዊ ዕርዳታን በማቅረብ ላይ የሚገኝ የቅዱስ ቪንሴንት በጎ አድራጊ ድርጅት አስታውቋል። ድርጅቱ “ኢትዮጵያን እወዳታለሁ” በሚለው መርሃ ግብር አማካይነት በኢትዮጵያ የሚገኙ ሕጻናትን ለማገዝ የዕርዳታ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ የጀመረ መሆኑን አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን                  

ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቱ “በኢትዮጵያ ውስጥ ወላጆች በአቅም ማነስ ምክንያት ልጆቻቸውን በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የጤና ተቋማት ውስደው በቂ ሕክምናን እንዲያኙ አላደረጉም” በማለት ገልጿል። በመሆኑም በሮም ከተማ የሚገኝ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር የዕርዳታ አስተባባሪ ምክር ቤት ዓላማው ከማኅበሩ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ከድሃ ቤተሰብ የሚወለዱ ሕጻናት በቂ የሕክምና አገልግሎትን እንዲያገኙ ማድረግ እንደሆነ አስረድቷል።

ሰብአዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቱ በዕቅዱ መሠረት በጣሊያን እና በዓለም ውስጥ ችግር ላጋጠማቸው ዕርዳታን ለማቅረብ በሮማ ከተማ ውስጥ ከሚገኝ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል ጋር የሚተባበር መሆኑን አስታውቋል። “ኢትዮጵያን እወዳታለሁ” በሚል መርሃ ግብር በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ድሃ ሕጻናትን በቂ የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻል መሆኑ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር የዕርዳታ አስተባባሪ ምክር ቤት አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የሚገኝ ጠንካራ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር

በአቅም ማነስ ለሚቸገሩ ቤተሰቦች ዕርዳታን የማሰባሰብ እንቅስቃሴ የተጀመረው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር ገዳማዊያን እና የፍቅር ሥራ ልጆች ገዳማዊያት በኩል በቀረበው ጥያቄ መሠረት ሲሆን ማኅበሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ለድሃ ቤተሰብ ሐዋርያዊ እና ቁሳዊ ዕርዳትን ሲያቀርብ መቆየቱን በሮም ከተማ የሚገኝ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር የዕርዳታ አስተባባሪ ምክር ቤት አስታውቋል። የዕርዳታ አስተባባሪ ምክር ቤቱ በሮም ከሚገኝ ባምቢኖ ጄሱ ጋር በመተባበር በከባድ ሕመም የሚሰቃዩ ሕጻናትን ተቀብሎ የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚቻልበትን መንገድ እንደሚያመቻች ገልጾ፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በሮም የሚገኝ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር የዕርዳታ አስተባባሪ ምክር ቤት ፕሬዚደንት በሆኑት በክቡር አቶ ጁሊያኖ ክሬፓልዲ የሚመራ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ከዚህ በፊትም ሲተባበሩ የቆዩ የማኅበሩ ካህናት እና ደናግል ጋር እንደሚገናኝ ታውቋል።      

ሕፃናትን በማከም ተስፋን መስጠት

በሮም የቅዱስ ቪንሴንት ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት ተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ኪያራ ኦቶሌንጊ “ኢትዮጵያን እወዳታለሁ” በመባል የሚታወቅ አዲስ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአቅመ ደካማ ቤተሰብ ለሚወለዱ ሕጻናት ብሩህ ተስፋን ለመስጠት የተጀመረ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ሕጻናትን እና ወላጆቻቸውን በመርዳት የሚታወቁ የፍቅር ሥራ ልጆች የደናግል ማኅበር መኖሩን የገለጹት ወ/ሮ ኪያራ፣ የደናግል ማኅበሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመር የታቀደውን የዕርዳታ አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ የሚተባበሩ መሆኑን አስረድተዋል። በርሃብ እና በጤና አገልግሎት እጥረት ለሚሰቃዩ ሕጻናት ማኅበራቸው አስፈላጊውን ዕርዳታን በማቅረብ መልካም የወደፊት ተስፋ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያቀደ መሆኑን አስረድተዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተነሳው ግጭት ምክንያት ሕጻናት በከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ያስታወሱት ወ/ሮ ኪያራ፣ በከባድ ሕመም ሚሰቃዩ ሕጻናትን ወደ ሮም አምጥቶ ሕክምና እንዲከታተሉ ማድረግ በዚህ ጊዜ አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል። ሁኔታዎች ሲረጋጉ በጦርነት የተጎዱ ሕጻናትን ተቀብሎ ለማገዝ ማኅበራቸው ዕቅድ ያለው መሆኑን ገልጸው በተለይም ሕጻናቱ በተወለዱበት አካባቢ የሚረዱበትን መንገድ ለማመቻቸት ማኅበራቸው እንደሚያስብ ወ/ሮ ኪያራ አስረድተዋል።

በሮም የሚገኝ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት ወ/ሮ ኪያራ ገልጸው በከባድ ሕመም የሚሰቃዩ ሕጻናትን ተቀብሎ አስፈላጊውን የሕክምና ዕርዳታን በመስጠት ረገድ የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በሮም ከተማ የሚኖሩ የቅዱስ ቪንሴንት የዕርዳታ ማኅበር አባላት እና ማዕከላት ከኢትዮጵያ የሚመጡ ተረጂዎችን ተቀብለው ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። የቅዱስ ቪንሴንት ዕርዳታ አስተባባሪ ድርጅት ከመጭው መስከረም ወር ጀምሮ ዕርዳታ የማሰባሰብ እንቅስቃሴውን የሚጀምር መሆኑን ወ/ሮ ኪያራ አስታውቀው፣ ማኅበራቸው የገንዘብ ዕርዳታን ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን የዕርዳታ ሂደቱ ምን ያህል እንድተጓዘ፣ የሕክምና ዕርዳታ የሚደረግለት ሕጻን የሚገኝበትን የጤና ሁኔታ ተከታትሎ የማሳወቅ ሃላፊነት ያለው መሆኑንም አስረድተዋል።      

10 July 2021, 22:13