ፈልግ

በሕንድ የቅድስት ሐና ልጆች ማኅበር አባላት “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን ሰነድ ሲመለከቱ በሕንድ የቅድስት ሐና ልጆች ማኅበር አባላት “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን ሰነድ ሲመለከቱ  

ገዳማዊያት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከዓለማችን እንዲወገ የጋራ ጸሎት አቀረቡ

ገዳማዊያት በግንቦት ወር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባቀረቡት ዓለም አቀፍ የመቁጠሪያ ጸሎት፣ የሰውን ልጅ እያሰቃየ የሚገኝ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከምድራችን እንዲጠፋ እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ እና ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው በሙሉ መጽናናትን እንዲያገኙ በማለት ለዓለም አቀፍ የገዳማዊያት አለቆች በተዘጋጀው የመቁጸሪያ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በግንቦት ወር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሚቀርበው የመቁጠሪያ ጸሎት፣ ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከምድራችን እንዲወገድ በአምስቱም አህጉራት የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሩ በማለት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የጸሎት ጥሪ ሁላችንን ይመለከትናል ያሉት የቅድስት ጆቫና የቸርነት እህቶች ማኅበር አባል እና የዓለም አቀፍ ገዳማዊያት የበላይ አለቆች ማኅበር ረዳት የሆኑት እህት ተሬዝ ራድ፣ ጸሎት የዓለማችንን ችግር የሚያስወግድ ኃይል እንዳለው በጽኑ እናምናለን ብለዋል። የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን በአውታረ መረብ የሚካፈሉ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የማኅበራቸው አባላት መኖራቸውን ገልጸው፣ በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፋኛ ባጠቃቸው አገሮች ማለትም በሕንድ እና በሜክስኮ ብቻ ሳይሆን ጣሊያንን ጨምሮ በቱኒዚያ፣ በአውስትራሊያ እና በአምስቱም አህጉራት የሚገኙ የማኅበራቸው አባላት በየዕለቱ በሚያቀርቡት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት መካፈላቸውን ገልጸዋል።

በወረርሽኙ ምክንያት ድህነት ተባብሷል

“ታሊታ ኩም” የተባለ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያት የበላይ አለቆች ማኅበር፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቃወም የተመሠረተ እና ባሁኑ ጊዜ በ70 አገሮች ውስጥ በመንቀሳቀስ፣ ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግር ለደረሰባቸው እና ጾታዊ ጥቃት ለሚፈጸምባቸው ሴቶች ዕርዳታን የሚያደርግ መሆኑ ይታወቃል። የዓለም አቀፍ ገዳማዊያት አለቆች ማኅበር ረዳት የሆኑት እህት ተሬዝ ራድ በገለጻቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማደግ ላይ ባሉ ድሃ አገሮች ላይ ያስከተለው ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያው ቀውስ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተው፣ የጋራ ጸሎታቸው በተለይ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ሕዝቦች የእግዚአብሔርን እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርዳታ ለመለመን ነው ብለዋል።

ቅድስት ድንግል ማርያምን የኢየሱስ እናት

ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የምናቀርበው ጸሎት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የፈሰሰውን የብዙዎች እንባ የሚያብስ እና በዓለማችን ውስጥ የሚፈጸመውን፣ በተለይም በአቅመ ደካሞች እና በድሆች ላይ የሚደርስ በደል እና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲቆም ለማድረግ መሆኑን እህት ተሬዝ ራድ ገልጸዋል። ስቃይ እና ችግር ሲደርስባቸው ቀድመው ዕርዳታን የሚለምኑት ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ መሆኑን እህት ተሬዝ ራድ አስረድተው፣ ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ በሚያቀርቡት የመቁጸሪያ ጸሎት ለማኅበረሰባቸው እና ለቤተክርስቲያናቸው ሰላምን እንለምናለን ብለዋል። ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አዎንታዊ ምላሽ በመማር እኛም በዕለታዊ ሕይወታችን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንታዊ ምላሽ መስጠትን እንማራለን ብለው፣ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በምናደርገው ጉዞ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘወትር የምትደግፋቸው መሆኑን የዓለም አቀፍ ገዳማዊያት የበላይ አለቆች ማኅበር ረዳት የሆኑት እህት ተሬዝ ራድ አስረድተዋል።       

01 June 2021, 16:21