የወጣቶች የሕይወት ክፍሎት የወጣቶች የሕይወት ክፍሎት  

የሕይወት ክህሎት

በሕይወት ደስተኛ እና ስኬታማ መሆን ዝም ብሎ በአንድ ቀን ወይም በአንድ ሌሊት የሚመጣ ወይም የሚፈጠር ሳይሆን በመንፈሳዊ፣ በማሕበራዊ፣በስነልቦናዊ እና በአዕምሮአዊ ሕይወታችን ሚዛናዊነት የምናጎለብተው፣ የሚያድግ፣ እየበሰልን ስንመጣም የሕይወትን ትርጉም ትክክለኛ ምላሽ እየሰጠን ባደግን ቁጥር የበለጠ የሚበለጥግ የእድገት ጉዞ ነው፡፡አሁን በምንኖርበት አለም ብዙ እሩጫ፣እረፍት ማጣት፣አንዱን አንስተን ስላልገባን ሌላውን የምንጥልበት፣ቅጥ ያጣ ውድድርና ከንቱ መባከን በሆነበት በዚህ ዘመናዊ ዘመን በልበሙሉነት ረጋ ብሎ ማሰብ፣በሚሆነው እንጂ የማይሆነው ላይ ጊዜ ሳያጠፉ የሚበጀውን በመያዝ እራስን በማወቅ ትክክለኛና ደስተኛ ሕይወት መምራት የማስተዋል ውጤት ነው፡፡

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ

ከልጅነታችን ጀምሮ በእድገታችን የብዙ ሰዎች ውጤት ነን፤ በመሆኑም ከቤተሰባችን ጀምሮ እንዲህ አድርጉ ወይም እንዲህ ሁኑ እየተባልን አድገናል፡፡እነዚህም የተባልናቸው ነገሮች እራስህን ግዛ/ዢ፣አስተውል፣ትግስት ይኑርህ/ሽ፣ሃላፊነትህን ተወጣ/ጪ፣ ልበ ሙሉ ሁን/ኚ እስቲ፣እራስህን/ሽ እወቅ/ቂ፣ማንነትህን/ሽን አትርሳ/ሺ፣ጠይቀህ/ሽ ተረዳ/ጂ አትንከርፈፍ/ፊ፣ተማር/ሪ፣እያሉ ዘመናዊ እውቀት እንዳሁን ሳይስፋፋ የወደፊቱ ገብቱአቸው ሲመክሩን እና ሲገስጹን የነበሩ አሁንም ያሉ ወላጆቻችን እና ቤተሰቦቻችን አሁን ያለንበት ዘመን ውጥረት በደንብ የገባቸው በመሆኑ ልቡ የበራለት እና የገባው ሰምቶ ሲሰተካከልና ቀጥ ቀና ብሎ ሲያድግ ያልገባው ደግሞ በተቃራኒው ይሆናል፡፡

ታላላቆቻችን በማንኛውም ሰው ሕይወት ውስጥ በዋናነት ሁለት ትላልቅ ምርጫዎች እንዳሉ ያወቁና እነሱም በሕወታችን የሚገጥሙንን አስቸጋሪ አጋጣሚዎችን ተቀብሎ ዝም ብሎ መኖርና በሌላ በኩል ደግሞ የሚቀረፉትን ቀርፎ ለችግሮች መፍትሄ አበጅቶ ሻል ባለ መልኩ ማደግ መሆኑን የተረዱ ናቸው፡፡

በመሆኑም ቤተሰቦቻችን፣ጎረቤቶቻችን፣ታላላቆቻችን ከላይ እንደዘረዘርኩት፤ ሲመክሩን፣ ሲያስተምሩን እና በሕይወት ክህሎት ሲያስታጥቁን የነበረው፤ ሕይወታችንን በማስተዋልና በመረዳት እንድንኖር እና ለችግሮቻችን መፍትሄ በማግኘት ጤነኛ ሕይወት ለመኖር ትክክለኛ የሕይወት ውሳኔ እንድንወስን ይረዳን ዘንድ በመሆኑ ነው፡፡እኛ ወጣቶች ከቤተሰባችን፣ከማህበረሰባችን፣ከጉአደኞቻችን በአጠቃላይ ከአካባቢያችን መልካምን ነገር ተምረን የነገን ሕይወታችን ዛሬ ትክክለኛ ሕይወት  በመኖር አድገን ማህበረሰባችንን በማገዝ የወደፊቱን ትውልድ የተሻለ ነገር የምናወርስ ብርቱዎች እንድንሆን ነው፡፡

እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን ሕይወት በሙላት መኖር የእኛ ሃላፊነት ነው፡፡ወጣቶች በመሆናችን ይህን ጉልበታም እና ብዙ ፍሬ የምናፈራበት ግዜ በማስተዋልና በመረጋጋት ካልታጀበ የሚያሳድገን አይሆንም በመሆኑም የተሻለውን በመምረጥ፣መልካምነትን ጠበቅ አድርጎ በመያዝ ወደፊት የምናድግበትና የምንበረታበት የሕይወት ክህሎት ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡ከራሳችን ጋር፣ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ከማህበረሰባችን ጋር በምን አይነት መልኩ መኖር እንዳለብን ይረዳን ዘንድ እግዚአብሔር የሰጠንን አዕምሮ በመጠቀም የሚሻለውንና የሚበጀውን ለይተን በማጤን ከእውቀት ማነስ ፀድተን የሕይወት መንገዳችንን በብርሃን መራመድ አለብን፡፡እኛ ወጣቶች እንደቀደመውም እንዲሁም የሚመጣውም ትውልድ እጣ ፈንታው እንደሆነው ሁሉ ሁላችንም የቤተሰባችን እንዲሁም የማህበረሰባችን ውጤቶች ነን፡፡ስለዚህ ከዚህ ማህበረሰባችን ጋር አብሮ ለማደግ እና ለመኖር ይረዳን ዘንድ ከተኖረውና ከኖርነው ሕይወት በመማር ከራሳችንና ከማህበረሰባችን ጋር መኖር የምንችልበትን ክህሎት ማሳደግ የዘመናዊነት ምልክት በመሆኑ መትጋት ግድ ነው፡፡

ታድያ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመረዳት ይረዳን ዘንድ የሕይወት ክህሎት ምን እንደሆነና ከምን ከምን የተዋቀረ መሆኑን ማየት የበለጠ የሚረዳን በመሆኑ እንደሚከተለው ቀለል ባለ መልኩ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ምንም እንኩአን ይህ ትምህርት እንደስልጠና ብንወስደው ብዙ የተግባር ስራ የሚፈልግ ቢሆንም ነገር ለጊዜውም ቢሆን ይጠቅማል በሚል የታሰበ በመሆኑ እንማርበት ዘንድ ታስቦ ነው፡፡በሌላ በኩል ድግሞ እነዚህ የሕይወት ክህሎት የምንላቸው ነገሮች በተለያየ መልኩ የተገለጹ ነገር ግን ስለ አንድ ነገር የሚናገሩ ናቸው፡፡እሱም ሕይወትን ጤናማ በሆነ መልኩ እንድንመራ ነው፡፡፡፡የተለያዩ ተቁአማት ወይም ምሁራን በገባቸው መጠን ይከፋፍሉታል በመሆኑም ለኛ ድግሞ ለጊዜውም ቢሆን ቀለል ባለ መልኩ ለማየት ተሞክሩአል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የሕይወት ክህሎት ማለት ሰዎች ከአካባቢያቸው ጋር በመላመድና መልካም ባህሪን በመላበስ የሕይወት ፈተናዎችን ማለፍ የሚችሉበት ብቃት የሚሰጥ እና ከማህበረሰው ጋር ተባብሮና ተስማምቶ ለመኖር የሚረዳ ነው በማለት ያስቀምጣል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዩኒሴፍ ደግሞ የህይወት ክህሎት ማለት “የሶስት መስኮች ሚዛናዊነት ጥቅም እና መልካም እሴትነት ለማስተማር የታሰበ የባህሪ ለውጥ ወይም የጤነኛ ባህሪ  ማበልጠጊያ ዘዴ” ነው በማለት ይናገራል፡፡እነዚህ ሶስት ነገሮች በእውቀት ፣ በአመለካከት እና በክህሎት ሚዛናዊነት የምንሰራበት የሚያበለጥገን ከማህበረሰብ ጋር ተስማምቶ የመኖር የሕይወት እውቀት የምናገኝበት ነው በማለት ይገልጣል፡፡ይህም ማለት ከቤተሰብ፣ከማህበረሰብ ያገኘነውን መልካም ነገሮች በሙሉ መልሰን ጨምረን ለመስጠት በልበ ሙሉነት እና በመልካም ምግባር የምንታነጽበት ነው፡፡

የህይወት ክህሎቶች በዋነኝነት ወጣቶች አስቸጋሪና ፈታኝ የህይወት ሁኔታዎችና እውነታዎች ሲያጋጥሟቸው በብቃት ችግሮቻቸውን በመቅረፍ ለራሳቸው፣ለቤተሰባቸው፣ለማህበረሰው ሁሉ የሚበጅ ጤነኛ ውሳኔ እንዲወስኑና ትክክለኛ የሕይወት ምርጫ እንዲመርጡ የሚረዳ  የአእምሮ ደህንነትን እና ብቁነትን ለማሳደግ የሚረዳ ነው።

ከላይ ለትርጉም ይረዳን ዘንድ በነጠላ ነበር ሲንመለከት የነበረው ነገር ግን የሕይወት ክሎቶች እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ፡ዩኒሴፍ፣ ዩኔስኮ እና የዓለም ጤና ድርጅት አስር ዋና የሕይወት ክህሎት፣ስልቶችን እና ቴክኒኮችን ይዘረዝራሉ-የችግሮችን የመፍታት ክህሎት፣ ጠለቅ ብሎ የማሰብ ክህሎት፣ ውጤታማ የመግባባት ችሎታ ፣በራስ መተማመን፣ለራስ ግምት መስጠት፣የውሳኔ አሰጣጥ ክህሎት፣ የፈጠራ አስተሳሰብ ፣ ከራስና ከሌሎች ጋር የመግባባት ችሎታን ፣ እራስን የማወቅ ችሎታ ፣ የሌላውን ችግር እንደራስ አድርጎ በመረዳት የመርዳት ክህሎትን፣ጭንቀትን ድብርትን መቋቋም ናቸው፡፡

ስለ እራስ ያለ እውቀት ወይም ግንዛቤ ፣ በራስ መተማመን እና ለራስ ግምት መስጠት በሚባሉ ክህሎቶች የአንድን ሰው ጥንካሬዎችን እና ድክመቶችን ለመረዳት አስፈላጊ መሣሪያዎች ናቸው።ስለዚህ ማንኛውም ሰው ወይም ግለሰብ እራሱን በማወቅ፣በራስ መተማመን እና ስለራሱ ያለው ግምት ሚዛን ላይ በማስቀመጥ በሕይወት ሊገኙ የሚችሉ እድሎችን ማስተዋል እና ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶችን ለመጋፈጥ መዘጋጀት ይችላል፡፡ በመሆኑም በግለሰብ፣በቤተሰብ እና በማህበረሰብ ወስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍ ወደ ተሻለ አድገት መጉአዝ ይችላል።

አንድ ሰው በነዚህ በሕይወት ክህሎቱ መበልጠግ አማካይነት አማራጮችን የማየት፣ የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን በማወቅ ምክንያታዊ በመሆን ትክክለኛ ውሳኔ የሚወስንበት አቅም ያገኛል፡፡ከሌሎችም ጋር መልካም፣ ጤነኛ እና ሰላማዊ ግንኙነትን መመስረት ይችላል፡፡የህይወት ክህሎቶች ውጤታማ በሆነ መልኩ ከራስ ጋርና ከሌሎች ጋር የመግባባት ችሎታ እንዲኖር ያስችላሉ ፣ ለምሳሌ በመስማት እና በማዳመጥ መካከል ያለውን ልዩነት ለመለየት እና መልእክቶች እና አስተሳሰቦች በትክክል መድረሳቸውን ለማወቅ ያስችላሉ በመሆኑም ለመናገር ብቻ ሳይሆን ለማድመጥም መትጋት እንዲሁም ስናዳምጥ ደግሞ መልስ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን በትክክል ለመተላለፍ የተፈለገውን ነገር በትኩረት አድምጦ፣ ተረድቶ እና ጠይቆ መግባባትን መፍጠር ነው፡፡

25 June 2021, 12:06