የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ለሚያንማር እና ለቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሰላም እንጸልይ”

በዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የተግባር መድረክ አስተባባሪነት በየዓመቱ የሚካሄድ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት፣ በጣሊያን እና በአርጄንቲና የሚገኙ መድረኮቹን፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ሴቶች ማኅበርን እና የአርጄንቲና ብሔራዊ የሰላም እና ፍትሕ ምክር ቤትን በማስተባብ፣ በሚያንማር እና በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሰላም እንዲወርድ የአንድ ደቂቃ የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንዲፈጸም መደረጉ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ግንቦት 29/2013 ዓ. ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር በመሆን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ባቀረቡር የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ወቅት ሁላችንም በየቀኑ የሰላም መሣሪያዎች እንድንሆን ጠይቀው፣ በሁለቱ አገሮች ማለትም በሚያንማር እና በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሰላም እንዲወርድ ጸሎት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የተግባር መድረክ ባወጣው መርሃ ግብር መሠረት ማክሰኛ ሰኔ 1/2013 ዓ. ም እንደ ኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ የሰላም ጸሎት፣ በተለይም ባሁኑ ወቅት ግጭቶች እና አለመረጋጋት በሚታይባቸው ሁለቱ አገሮች ማለትም በሚያንማር እና በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሰላም እንዲወርድ በመመኘት የአንድ ደቂቃ ጸሎት መደረጉ ታውቋል። በዚህ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ሰላም ወዳድ እና በጎ ፈቃድ ያላቸው በሙሉ መሳተፋቸው ታውቋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ግንቦት 29/2013 ዓ. ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን እንዳሳሰቡት፣ ሁሉም ሰው እምነቱ በሚፈቅደው መንገድ ለሰላም እንዲጸልይ፣ በተለይም ባሁኑ ወቅት ሰላም በሚጎድልባቸው ሁለቱ አገሮች እነርሱም በሚያንማር እና በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሰላም ይወርድ ዘንድ ጸሎት እንድናቀርብ አደራ ማለታቸው ይታወሳል።

የሰላም መሣሪያዎች እንድንሆን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያለፈው እሑድ ባስተላለፉት መልዕክታቸው “ሁላችንም በየዕለቱ የሰላም መሣሪያዎች እንድንሆን ይገባል” ማለታቸውን ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የተግባር መድረክ ዋና ጸሐፊ ማርያ ግራሲያ ቲባልዲ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውሰዋል። የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ለመጀመሪያ ጊዜ እ. አ. አ በ2014 ዓ. ም መካሄዱን ያስታወሱት ማርያ ግራሲያ ቲባልዲ፣ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ሰኔ 1 ቀን የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ሲፈጸም መቆየቱን ገልጸዋል። ዘንድሮ የተፈጸመው የሰላም ጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ሁለቱን አገሮች ማለትም ሚያንማር እና ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ያስታወሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚያንማር

በሚያንማር በተካሄደው የመንግሥት ግልበጣ ምክንያት ከአራት ወራት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ሰላም ጠፍቶ መቆየቱ ታውቋል። በአገሪቱ በተቀሰቀሰው አመጽ ምክንያት እስካሁን ወደ 800 የሚጠጉ ዜጎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ታውቋል። ለበርካታ ሳምንታት በሚያንማር ትላልቅ ከተሞች መጠነ ሰፊ ሰላማዊ ሰልፎች ሲደረጉ መቆየቱም ይታወሳል። ከሰላማዊ ሰልፈኞች ውስጥ ወጣቶችን ጨምሮ 4,000 የሚጠጉ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ባለፈው የአውሮፓዊያኑ ወር በሮም ከተማ ለሚኖሩ የእስያ አህጉር ተወላጆች ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት፣ ከጥላቻ እና ልዩነት ይልቅ ፍቅርን እና ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በመልካም ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች በመታገዝ ለኢየሱስ ክርስቶስ እውነት ታማኞች መሆን እንደሚገባ ማሳሰባቸው ታውቋል።

ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም

ከሁለት ሳምንታት በፊት በእስራኤል ሠራዊት እና በፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሐማስ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ላይ የሞት አደጋን ማስከተሉ ይታወሳል። በዚህ ጦርነት በቁጥር በርካታ ሕጻናት መሞታቸው እና ከአንድ ሚሊዮን ሕጻናት በላይ ለችግር እና ስቃይ መዳረጋቸው ይታወሳል። በሁለቱ ወገኖች በሚደረግ ጦርነት ከፍተኛ ሐዘን የተሰማቸው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሁለቱም ውቀገኖች ባስተላለፉት መልዕክት ጦርነት በእስራኤል ውስጥ በሚገኙት የተለያዩ ከተሞች ውስጥ በሚኖሩት ነዋሪዎች መካከል ጥላቻን በመዝራት ወንድማማችነትን ክፉኛ እየጎዳው ነው ማለታቸው ይታወሳል። ስለሆነም ሁለቱ ወገኖች ወደ ውይይት ገበታ እንዲቀርቡ እና በመካከላቸውሰላምን ለማውረድ እንዲጥሩ መጠየቃቸው ይታወሳል።                  

08 June 2021, 16:37