መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበትን የሚያመለክት መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበትን የሚያመለክት 

በጴራቅሊጦስ በዓል ዋዜማ ሥነ ሥርዓት ላይ የመላው ዓለም ክርስቲያኖች መሳተፋቸው ተገለጸ

የቫቲካን ዜና አገልግሎት በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ድረ ገጾቹ በኩል ባዘጋጀው መስመር በኩል የአራት ከተሞች አብያተ ክርስቲያናት በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር መሠረት በተከበረው የጴራቅሊጦስ በዓል ዋዜማ ሥነ ሥርዓት ላይ መካፈላቸው ሲታወቅ፣ የዝግጅቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፒኖ ስካፉሮ በዚህ ዝግጅት ላይ የተሳተፉት የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ተከታዮች ምስክርነታቸውን መግለጻቸውን ተናግረዋል። አቶ ፒኖ ስካፉሮ አክለውም በተለያዩ ማኅበርዊ ችግሮች፣ በበሽታ፣ በጦርነት እና በኤኮኖሚያዊ ቀውስ ክፉኛ ለተጎዳው የሰው ልጅ መጸለይ ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ በአንግሊካን ቤተክርስቲያን የካንተር በሪው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ አስተንትኖ ያቀረቡ ሲሆን በመጨረሻም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቪዲዮ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን -

ቫቲካን በአውታረ መረብ አማካይነት በቀረበው ዝግጅት ላይ ከአሜሪካ፣ ከሮም፣ ከቦኔስ አይሬስ እና እና ከኢየሩሳሌም ከተሞች የተወጣጡ ምዕመናን መሳተፋቸው ታውቋል። በአውታረ መረብ በኩል በተዘጋጀው የጴራቅሊጦስ በዓል ዋዜማ ዝግጅት ላይ የአራቱ ከተሞች ምዕመናን እና የመላው ዓለም ክርስቲያኖች በቀጥታ መካፈላቸው ታውቋል። የአብያተ ክርስቲያናቱ ተከታዮች በጋራ ባቀረቡት ጸሎታቸው አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በምድራችን እንዲወርድ ጠይቀዋል። ሥነ ሥርዓቱ የተዘጋጀው በቅድስት መንበር ውስጥ በሚገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተሃድሶ እንቅስቃሴ አስተባባሪነት መሆኑ ታውቋል። በዝግጅቱ ላይ በአንግሊካን ቤተክርስቲያን የካንተር በሪው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ አስተንትኖአቸውን ያቀረቡ ሲሆን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስም የቪዲዮ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጉዳት ለደረሰበት የሰው ልጅ የተደረገ ጸሎት

ዘንድሮ በተዘጋጀው የጴራቅሊጦስ በዓል ዋዜማ የመላው ዓለም ክርስቲያኖች የሕይወት ምስክነትን እንዲያሰሙ ዕድል መስጠት እንደሚያስፈልግ የዝግጅቱ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፒንቶ ስካፉሮ ገልጸው፣ ይህ ብቻ ሳይሆን በበሽታ፣ በጦርነት እና በኤኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት በሰው ልጅ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን እያንዳንዱ ክርስቲያን በልቡ እንደሚያውቅ ገልጸዋል። በማከልም በሰው ሕይወት ላይ የደረሰው መከራ እና ጭንቀት ብዙ በመሆኑ የዕርዳታ ጥያቄ ጸሎታችንን ወደ መንፈስ ቅዱስ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን ወደ ዓለም ለመላክ ቃል መግባቱን እናምናለን ያሉት ክቡር አቶ ፒንቶ ስካፉሮ፣ ቃል ኪዳኑም እውነት እና የእግዚአብሔር ኃይል ወደ ምድራችን እንደሚወርድ እናምናለን ብለዋል።

ስለ መንፈስ ቅዱስ የመሰከሩ አራቱ ከተሞች

በዓለማችን ውስጥ የሚገኙ አራት ከተሞች የተመረጡበትን ምክንያት ያስረዱት አቶ ፒንቶ፣ በሰው ሕይወት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ታላቅ ሥራዎቹን እንደሚሰራ ገልጸው፣ እ. አ. አ በ1900 ዓ. ም በአሜሪካ ውስጥ የሚገኝ ቶፔካ ከተማ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በመቀበል በዚያች ከተማ ውስጥ በጰንጠቆስጤ ስም የሚመሩ የመጀመሪያዎቹ ቤተክርስቲያኖች መመስረታቸውን አስታውሰዋል። የሮም ከተማ የተመረጠበትን ምክንያት ሲገልጹ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የተካሄደበት ከተማ እና የአብያተ ክርስቲያናት ሕብረት እንዲመሠረት ምክንያት መሆኑን አስታውሰው፣ የአርጀንቲና ዋና ከተማ ቦይኔስ አይረስ የተመረጠበት ምክንያት ወንድማማችነት እና በካቶሊካዊ ተሃድሶ እንቅስቃሴዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር የሆነበትን አስረድተው፣ ኢየሩስሌም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ33ኛው ዓመት ምሕረት መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ የወረደበት ሥፍራ መሆኑን የዝግጅቱ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፒንቶ ስካፉሮ አስረድተዋል።

24 May 2021, 15:03