በጋና ውስጥ የጤና አገልግሎትን ለማዳረስ ከሚደረጉ የሚዲያ ጥረቶች አንዱ በጋና ውስጥ የጤና አገልግሎትን ለማዳረስ ከሚደረጉ የሚዲያ ጥረቶች አንዱ  

አፍሪካ የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት እና የዕድገት ተስፋ ያላት አህጉር መሆኗ ተነገረ

የአፍሪካ አህጉር ገና ጥቅም ላይ ያልዋሉ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋዎች የሚገኝበት የእድገት ተስፋውም የጎላ መሆኑን አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አመልክቷል። ጥናቱ ይፋ የሆነው በሮም በሚገኝ ግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ታውቋል። በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኝ አልቤርቶ ሁርታዶ ማዕከል በኩል የቀረበው ሳይንሳዊ ጥናቱ “ሁላችንም ወንድማማቾች” ነን የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ጥናቱ በተጨማሪም የአህጉሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ባሕላዊ፣ ሐይማኖታዊ እሴቶችን በማጤን የአፍሪካን አህጉር ድሎች እና የተፈጥሮ ሃብትን ያገናዘበ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ገና ያልታወቁ ብዙ የተፈጠሮ ጸጋ ያላት እና ሕዝቦቿም ሰፊ የማደግ ዕድል የሚታይባት አፍሪካ በሚል የመነሻ ሃሳብ በርካታ ምሁራን በመሳተፍ አስተዋጽኦዋቸውን ማበርከርታቸው ታውቋል። ይሁን እንጂ በሌላ ወገን ጥናቱ የአፍሪካን አህጉር እየጎዱ ያሉትን የተለያዩ ችግሮችንም  ግልጽ ማድረጉ ታውቋል። ከችግሮቹ መካከል ጥቂቶቹ ያሏቸውን፣ በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ውስጥ የሚንጸባረቁ የባሕል ለውጦችን እና አዳዲስ ርዕዮተ ዓለሞችን ጥናቱ ግልጽ አድርጓል። የአፍሪካ አህጉር እንደ ሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅምን ከሚያስቀድሙ የራስ ወዳድነት አስተሳሰቦች በመውጣት በኤኮኖሚ እና ስነ-ተፈጥሮ ላይ ለደረሱት ቀውሶች ትክክለኛ መፍትሄን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ጥናቱ አሳስቧል።

ለአፍሪካ አህጉር የተለየ አመለካከት ተሰጥቶታል

የጥናቱ ውጤት ባለቤት እና የሲንዴረሲ ትምህርት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል ሳንጋሊ፣ አፍሪካ የተረሳች አህጉር ብትባልም እና ሥር የሰደዱ የራሷ ችግሮች ያሉባት አህጉር ብትሆንም የከፍተኛ ተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት እና በርካታ አመሪቂ ውጤቶችን በማምጣት ላይ የምትገኝ አህጉር መሆኗን ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል በማከልም አፍሪካ ገና ወጣት፣ ከፍተኛ የወሊድ መጠን እና አማካይ ሕዝቧ በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ እና የተፈጥሮ አንጡራ ሀብቶች ያሏት አህጉር መሆኗን አስረድተዋል።          

የ “ኡቡንቱ ንድፈ ሃሳብ” ምንድነው?

በአፍሪካዊ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ “ኡቡንቱ” በመባል የሚጠራ ንድፈ ሃሳብ መኖሩን ያስታወቁት ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል፣ በዚህ ዕይታ ውስጥ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ይፋ ካደረጉት እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ከሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ጋር የሚቀራረብ ግብረ ገባዊ ንድፈ ሃሳብ መሆኑን አስረድተዋል። “ኡቡንቱ” የሚለው ቃል በመሠረታዊ ሃሳቡ አንዱ ለሌላው መልካምን ለማድረግ መኖሩን፣ አንድነትን፣ ማንኛውንም ችግር በጋራ ሃላፊነት መውጣትን እና አፍሪካዊ ማንነትን የሚገልጽ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን ገልጸው፣ ምዕራባዊያን ግሎባላይዜሽን የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ጀምረው ለረጅም ዘመናት የቆየውን የአፍሪካን ባሕል ፈተና ውስጥ መክተታቸውን አስረድተዋል።

ጥናታዊ ጽሑፋቸው የተለያዩ የአፍሪካ አካባቢዎችን የተመለከተ መሆኑን የተናገሩት ብጹዕ አቡነ ሳሙኤል ሳንጋሊ፣ በአፍሪካ አገራት ውስጥ የተለያዩ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ተፈጥሮአዊ እና የጤና ይዘት መኖሩን ገልጸዋል። የ “ኡቡንቱ” ንድፈ ሃሳብ አዲስ የአሠራር ዘዴዎችን ማስተዋወቁን የገለጹት አቡነ ሳሙኤል፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ እና ከእውቁ የነጻነት ታጋይ ማንዴላ ዘመን በኋላ ከሰሃራ በታች ባሉት አገራቱ መካከል ሕጋዊነትን አግኝቶ የተዘረጋው ማኅበራዊ ትስስር መኖሩን አስረድተዋል። የ “ኡቡንቱ” ንድፈ ሃሳብ በሐይማኖታዊ ገጽታውም በሰሜን አፍሪካ አገሮች ለምሳሌ በሰኔጋል ውስጥ በጎሳዎች እና በሐይማኖቶች መካከል የጋራ ሃላፊነት አስተሳሰብን ማሳደጉን፣ በካሜሩን እና ዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ውስጥ የሚታየውን አለመረጋጋት በማጤን መፍትሄን ማግኘት የሚቻለው የ“ኡቡንቱ” ንድፈ ሃሳብን በመጠቀም መሆኑን አስረድተዋል። የእነዚህ አገራት ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች የ“ኡቡንቱ” ንድፈ ሃሳብን በመከተል፣ የባሕል፣ የማኅበራዊ ሕይወት እና የሐይማኖት ልዩነት ባሉባቸው አካባቢዎች የሕዝቦች በሰላም የመኖር መንገዶችን በማመቻቸት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

20 May 2021, 15:03