የሚያዝያ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ዘገብር ኄር ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የሚያዝያ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ዘገብር ኄር ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ  

የሚያዝያ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ዘገብር ኄር ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ  ንባባት

1.     2ጢሞ 2:1-15

2.     1ጴጥ 5:1-11

3.     ሐዋ 1:6-8 

4.     ማቴ 25:14-30

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የሰነፉ አገልጋይ ምሳሌ

“የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጒዞውን ቀጠለ። አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውዬ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።

“የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። አምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።

“እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው።

“ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሮአል? ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር። “ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ የተትረፈረፈም ይኖረዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ይህን የማይረባ አገልጋይ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።

የእለቱ አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አምልኮ አቆጣጠር ዘገብርኄር የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን። በዚህ ሰንበት እግዚአብሔር ስላደረገልን ነገርና ስለሰጠን ስጦታ የምናስብበት እንዲሁም እርሱን የምናመሰግንበት ነው። እግዚአብሔር ሰው አድርጎ ስለፈጠረን ብቻ ሳይሆን ከውልደት አንስቶ እስከ ዳግም ውልደት ከእኛ ጋር በመሆን በሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ከጎናችን መሆኑንና በተለይም በዚህ  ጾም ወቅት ከቃሉና ከቅዱስ ማዕዱ ራሳችንን በመመገብ የሕይወታችንን ጉዞ እንድንመለከት እንጋበዛለን።

በዛሬው የመጀመሪያ መልእክት ማለትም 2ጢሞ 2፣ 1-15 ባለው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በርታ በማለት የምክር ቃሉን ሲለግሰው እናያለን። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በርታ የሚለው በራስህ ኃይል በራስህ ጉልበት የነቃህ ወይም የበረታህ ሁን ለማለት ሳይሆን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው ጸጋ እና  ኃይል በርታ ማለቱ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያት ሥራ ም 1፣8 ላይ ለሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን እንደሚቀበሉ ብርታትን እንደሚቀበሉ ነግሮአቸዋል ስለዚህ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በርታ ሲለው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው ጸጋና ከመንፈስ ቅዱስ በሚገኘው ኃይል ተንቀሳቀስ ማለቱ ነው። ይህ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር ዛሬ ለእኔና ለእናንተም ያገለግላል የእኔ ማንነት ዕውቀቴም ይሁን ጥንካሬዬ ሁሉ የመጣው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሚመነጭ ነፃ የጸጋ ስጦታ መሆኑን በመገንዘብ ዘወትር ለሱ ምስጋናና ውዳሴ ልናቀርብለት ይገባል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር ለራሱ ብቻ አንዲይዘው ሳይሆን ይህንን ምክር ለሌሎችም እንዲያስተላልፍ አደራ ብሎታል። ይህም የሚያስገነዝበን እያንዳዳችን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምንቀበለው ጸጋ ለግላችን ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የዚህ ጸጋ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ውስጣችንን ክፍት ማድረግ ይጠበቅብናል ይህ የምንቀበለውን ጸጋ ለሌሎች የማካፈል ለሌሎች የማስተላለፍ ግዴታ ይኖረናል በዚህ አኳሃን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከአንዱ ወደ አንዱ በቀላሉ ይተላለፋል ማለት ነው።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በቁጥር 3 እና 4 ላይ እንደጠቀሰው ቁርጠኛ ወታደር በመሆን መከራን ሁሉ በትዕግሥት አንዲያሳልፍ አንደመከረው እኛም ሁላችን በተቀበልነው ምስጢረ ሜሮን አምካኝነት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወታደሮች ሆነናልና እንደ ታማኝ ወታደር ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ተገዢዎች በመሆን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ስንል በነገሮች ሁሉ ትዕግሥት በማድረግና የዓለምን ምኞት ሁሉ ወደኃላ በመተው መኖር ይገባናል። በዚህ መልኩ የምንኖርና የምንንቀሳቅስ ከሆነ ልክ ለዓላማውና ለስልጠናው ታማኝ እንደሆነ እንደ ትጉ እስፖርተኛ የድል አክሊል ተቋዳሾች እንደ ትጉ ገበሬም የመጀመሪያ የፍሬው ተካፋዮች እንሆናለን።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንድሚለው ምን አልባት እውነትን በመናገራችን እውነትና የእውነት መንገድ የሆነውን ክርስቶስ በመስበካችን ብዙ በደልና እንግልት ሊደርስብን ይችል ይሆናል ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንደሚነግረን የእርሱ መከራ፣ ስቃይና በደል ውስጥ ተካፋይ ሆነናልና እንዲሁ ደግሞ አብረን የእርሱ ነፃነት፣ ደስታና ትንሳኤ ተካፋዮች የዘለዓለም ሕይወትም ተቋዳሾች እንሆናለን። በሮሜ 6፡3-5 እንዲህ ይላል ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እነደተነሳ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን ይላል።

በመጀመሪያው መልእክት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በርታ በማለት የምክር ቃሉን እንደለገሰው ሁሉ በዚህ በሁለተኛ መልእክትም ደግሞ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ለቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ምክሩን ሲለግሳቸዋል እናያለን።  በዮሐንስ ወንጌል 21፡15-17 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኃላ ለሐዋርያው ጴጥሮስ 3 ጊዜ በጎቹን እንዲጠብቅ በጎቹን እነዲያሰማራ ግልገሎቹን እንዲጠብቅ ትእዛዝ ሰጥቶት በነበረው መሰረት  ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በተለይም የቤተክርስቲያን መሪዎችና ሽማግሌዎች ይህንን ኃላፊነት ጠንከር አድርገው አንዲይዙ ለየት ባለ መልኩ ደግሞ ለምዕመናን ግንባር ቀደም ምሳሌ በመሆን ዓይነተኛ ሚና እንዲጫወቱ ምክሩን ይለግሳል።

እረኛው በቃሉም በምግባሩም መልካም ከሆነ በጎቹ ሁልጊዜ ሊከተሉት ዝግጁዎች ናቸው ምክንያቱም በቃሉ የሚናገረውን በሕይወቱ እየኖረ ያሳያቸዋል እነርሱም በእርሱ ላይ የሚኖራቸው መተማመን ይጨምራል የእርሱንም አብነት ለመከተል ውስጣቸው ይነሳሳል።

በመቀጠልም ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ወጣቶቸ እንዲሁም ጎልማሶች ለሽማግሌዎች አንዲታዘዙ ሁልጊዜም በትሕትና እንዲጓዙ ምክሩን ይለግሳል ምክንያቱም ትሑት የሆነ ሰው አለኝ የሚለው ወይም የሚመካው በ1ኛቆሮ 15፡ 10 ላይ እንደምናገኘው በራሱ ጉልበትና አቅም ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋና ከእርሱ ከሚያገኘው ኃይል ነው። ትሕትና ዋናው የሰይጣንን ባሕሪ ትዕቢትን አሽቀንጥሮ ለመጣል የሚያገለግል ዓይነተኛ መሣሪያችን ነው። በትሕትና የተሞላ ሰው ምንጊዜም ቢሆን ራሱን ዝቅ ለማድረግ አይከብደውም ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሰው እግዚአብሔርን ከፍ ያደርጋል ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሰው ደግሞ እግዚአብሔርን ዝቅ ያደርጋል በዚህም ምክንያት በመጽሐፈ ምሳሌ 3፡34 ላይ እንደተጻፈው ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሰው ካለበት ከፍታ ላይ እግዚአብሔር ራሱ ዝቅ ያደርገዋል ይላል። ሰይጣን ከነበረበት ከከፍተኛ የመላእክት ማዕረግ የወረደው በትዕቢቱ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ማስተካከል በመፈለጉ ነው አዳምና ሔዋንም ዋናው ኃጢአታቸው በትዕቢት እንደ እግዚአብሔር መሆን መፈለጋቸው ነው።

ሌላው ትዕቢትን ማስወገጃ መሳሪያቸን በመጠን መኖር ነው በመጠን የሚኖር ሰው ራሱን በብዙ መልኩ ስለሚቆጣጠር ሰይጣን ወደ ውስጡ እንዲገባ ክፍተት አይፈጥርም በዚህ ሁኔታ ራሱን ከኃጢአት ምክንያት ሁሉ ያርቃል ማለት ነው። ሰይጣንን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል በምናደርገው ጾምና ጸሎት በምናደርገው ተጋድሎ ወደ ዘለዓለማዊ ክብሩ የጠራን አምላክ ራሱ ጸጋ ይሰጠናል ፍጹሞች ያደርገናል ያጸናናል ያበረታንማል።

በዛሬው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ላይ እንዳዳመጥነው እግዚአብሔር ለእያንዳዳችን እንደየአቅማችንና እንደየችሎታችን የተለያየ ስጦታ ይሰጠናል ነገር ግን በሰጠን ስጦታ ላይ በስተመጨረሻ ምን ያህል ሰርተን አንዳተረፍን ማወቅ ይፈልጋል። በተሰጠን ጥቂት ነገር ሰርተን ማትረፍ ከቻልን እግዚአብሔር አንተ ታማኝ እና ደግ አገልጋይ በጥቂት ነገር ላይ ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃልና በትልቅ ነገር ላይ እሾምሃለው ይለናል። ነገር ግን በዚች በትንሿ ነገር ላይ ታማኝ ሳንሆን ብዙ ነገር ቢሰጠንም ይህንን ብዙ ስጦታ በከንቱ እንደምናባክነው ግልጽ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር በሰጠን በማንኛውም ስጦታ ደስተኞች በመሆን ያንን የተሰጠንን ስጦታ ለማሳደግና ውጤታማ ለመሆን የተቻለንን ጥረት አናድርግ።

እግዚአብሔር በሰጠን በትንሿ ስጦታ ሳንጠቀምና ሳንሠራበት ቆይተን መልሰን እርሱን ብናማርር ልክ አንድ መክሊት እንደተቀበለው ወስዶም እንደቀበረው አገልጋይ ከውርደትና ወደውጭ ከመጣል አንተርፍም። ስለዚህ ይህ ሁሉ ከመምጣቱ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ ስጦታችን ምን መሆኑን በሚገባ እንለይ ከዛ በኋላ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን በእግዚአብሔር ጸጋ እየታገዝን እንሥራበት ካልሰራንበት ከእኛ ተወስዶ ለሌሎች ይሰጣል እኛም እንደማይረባ ቆሻሻ ወደውጭ እንጣላለን በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፏጨት ይሆናል።

ከእንዲህ ዓይነቱ ሃዘን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትታደገን ስጦታችንን በሚገባ ለማሳደግ እንድንችል ዘወትር በልጇ ፊት ታማልደን በውድቀታችንና በድካማችን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ጠበቃ ሆና ትቁምልን።

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

10 April 2021, 10:56