በኢየሩሳሌም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር የሚገኝበት ባዚሊካ በኢየሩሳሌም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር የሚገኝበት ባዚሊካ 

የሕማማት ሳምንት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በተነሳባት ኢየሩሳሌም

ባሁኑ ጊዜ በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙት ክቡር አባ ቪንቼንሶ ፔሮኒ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር በሚገኝባት ኢየሩሳሌም በሦስቱ የሕማማት ቀናት፥ ዕለተ ሐሙስ፣ ዓርብ እና ቅዳሜ የሚፈጸሙ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶችን በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ ከሚከናወኑ ዓብይ ሥነ-ሥርዓቶች መካከል ሐሙስ ዕለት የሚፈጸመውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር ጉብኝት፣ በስቅለተ ዓርብ ስለሚፈጸመው የዑደት ሥነ-ሥርዓት፣ ፍኖተ መስቀል እና በበዓለ ፋሲካ ዕለት ስለሚቀርበው የዜማ ሥነ-ሥርዓት በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአብያት ክርስቲያናት ዘንድ የሚቀርበው እያንዳንዱ የአምልኮ ሥርዓት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ የሚገለጽበት ሲሆን፣ በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የሚፈጸመው ሥነ-ሥርዓት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት፣ በተቀበረበት እና ከሞት በተነሳበት አገር የሚፈጸም በመሆኑ ልዩ ክብር የሚሰጠው መሆኑን ክቡር አባ ቪንቼንሶ ፔሮኒ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት አስረድተዋል። በጣሊያን ውስጥ የብሬሻ ሀገረ ስብከት ካህን የሆኑት ክቡር አባ ቪንቼንሶ ፔሮኒ የጳጳሳዊ ክብረ በዓላት አስተባባሪ ሆነው ለስምንት ዓመታት ያህል ካገለገሉ በኋላ በሀገረ ስብከታቸው መሪ ጳጳስ መልካም ፈቃድ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወደ ኢየሩሳሌም ከተዛወሩ ጥቅት ወራትን አስቆጥረዋል። በቂ የሥርዓተ አምልኮ ዕውቀት ያላቸው ክቡር አባ ቪንቼንሶ፣ ጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉት ምዕመናን ዘንድ ሰኞ መጋቢት 20/2013 ዓ. ም. የተጀመረው የሕማማት ሳምንት፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር በሚገኝበት የኢየሩሳሌም ካቴድራል ውስጥ ምን ይዘት እንዳለው አብራርተዋል።

የዘንድሮ የሕማማት ሳምንት የተጀመረው የቅድስት አገር ኢየሩሳሌም አስተዳደር እና የላቲን ሥርዓት የምትከተል ካቶሊክዊት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አባቶች ከምዕመና ጋር እሑድ ጠዋት በቅዱስ መካነ መቃብር ባሲሊካ ውስጥ ባከበሩት የሆሳዕና ክብረ በዓል መሆኑን ክቡር አባ ቪንቼንሶ ገልጸው፣ በዚሁ ዕለት የዘንባባ ቅጠል ቡራኬ እና ሦስት የሕማማት ቀናትን፣ ሐሙስ፣ ዓርብ እና ቅዳሜን የያስታውሱ የቤተ መቅደስ ዙሪያ ሦስት ዙር የዑደት ሥነ-ሥርዓት መካሄዱን አስረድተዋል። ከዑደት ሥነ-ሥርዓቱ ቀጥሎ በኢየሩሳሌም ፓትሪያርክ በሆኑት በብጹዕ አቡነ ፒዬርባቲስታ ፒሳባላ የተመራ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት መካሄዱንም ገልጸዋል። በዚሁ ዕለት ከሰዓት በኋላ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክስቶስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ለማስታወስ ብጹዕ ፓትሪያርክ ከቤተ-ፋጌ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም ከተማ ድረስ መንፈሳዊ ዑደት ማካሄዳቸውን ክቡር አባ ቪንቼንሶ ፔሮኒ ገልጸው፣ በዚሁ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ምዕመናን ያልተካፈሉት መሆኑን አስረድተዋል።

በአራተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ንግደት ያደረጉት አባቶች እንደሚመሰክሩት፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር በሚገኝበት ሥፍራ የሚከናወነው የሕማማት ሳምንት ሥርዓት ምስጢር በሌላ አካባቢ ከሚከናወነው ሥርዓት የሚለይበት ዋናው መንገድ፣ ኢየሩሳሌም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት፣ ደሙን በማፍሰስ የሞተበት እና ከሞት የተነሳበት ሥፍራ በመሆኑ በዚህ ሥፍራ በአካል ተገኝቶ ሕማማቱን ማስታወስ ልዩ ክብር የሚሰጠው መሆኑን አስረድተዋል።

ሐሙስ የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ሥነ-ሥርዓት መፈጸሙን የገለጹት ክቡር አባ ቪንቼንሶ ፔሮኒ፣ የገዳሙ ካህናት ከሰዓት በኋላ ጀምረው ሌሊቱን በሙሉ በቅዱስ ቁርባን ፊት ጸሎት ሲያቀርቡ እንደሚያነጉ ገልጸው፣ ይህ ሥነ-ሥርዓት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ከማስታወስ ይልቅ፣ ኢየሩሳሌም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር የሚገኝበት ቅዱስ ሥፍራ መሆኑን ለመግለጽ መሆኑን አስረድተዋል። በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የሚካሄደው የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ሥነ-ሥርዓት እምነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን አስረድተው፣ ቅዱስ ቁርባን የሚገኝበት ይህ እውነተኛ ሥፍራ የብርሃነ ትንሳኤውን ጸጋ በትክክል የሚገልጽ ነው ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በመሩት የበዓለ ሆሳዕና ዕለት ባቀረቡት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል በጥልቀት እና በተመስጦ እንድንመለከተው ማሳስባቸውን የተናገሩት ክቡር አባ ቪንቼንሶ ፔሮኒ፣ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኩሳት እና ምዕመናን ከሕማማት ሳምንት ሥነ-ሥርዓት እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪኮችን ይልቅ ከልብ ማድመጥ እንደሚበልጥ ገልጸው፣ በኢየሩሳሌም የሚፈጸመው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕማማት ሳምንት ሥነ-ሥርዓት በተለያዩ የዓለማችን ቋንቋዎች የሚነገረው በዚህ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። በኢየሩሳሌም ዓርብ ዕለት በሚካሄደው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት ምዕመናን ወደ ቅዱስ መስቀሉ በመመልከት የኢየሱስ ክርስቶስን ስቃይ በሚያስተነትኑበት ወቅት፣ በሚስማር መወጋቱን የሚያስታውስ የመዶሻ ድምጽ ከባዚሊካው ጀርባ እንዲሰማ መደረጉን አባ ቪንቼንሶ አስታውሰው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ከቀራንዮ መንበረ ታቦት ወርዶ ቅባት እንዲደርግበት ዲያቆናት የሚቀበሉበት ሥነ-ሥርዓት መኖሩንም ገልጸዋል።

በሁሉም የአምልኮ ሥርዓት ወቅት እንደሚካሄደው ሁሉ፣ በብርሃነ ትንሣኤው ቀንም በቅዱስ መካነ መቃብር ፊት በሚፈጸመው የሕማማት ቀናት ሥነ-ሥርዓት የቅዱስ ወንጌል ንባባት የሚቀርቡ መሆኑን አባ ቪንቼንሶ አስታውሰዋል። እሑድ መጋቢት 19/2013 ዓ. ም. በተከበረው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ መታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት ወቅት በዓሉን ለማክበር በባዚሊካው በተሰበሰቡት ምዕመናን ፊት፣ እንደ ኢየሩሳሌም ልማድ መሠረት የመስዋዕተ ቅዳሴው መሪ ጳጳስ ቅዱስ ወንጌልን በማንበብ የትንሳኤውን መልካም ዜና የሚያበስር መሆኑን ገልጸዋል።

በብርሃነ ትንሳኤው ዕለት በሚቀርበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ በኢየሩሳሌው በሚገኘው ባዚሊካ ዙሪያ ዑደት በማድረግ የብርሃነ ትንሳኤውን ዜና የሚገልጹ፣ ከአራቱ ወንጌላት የተወሰዱ ንባባት በዜማ እንዲነበቡ መደረጉን ክቡር አባ ቪንቼንሶ አስታውሰዋል። በሮም የሚከበረውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ መታሰቢያ በዓል ከቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ እና አሁን በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ ከሚገኙት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በጸሎት ለማክበር ዕድል ማግኘታቸውን የገለጹት ክቡር አባ ቪንቼንሶ ፔሮኒ፣ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ እና ወደ ልዩ ልዩ አገሮች በመሄድ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የቤተክርስቲያኗን ኩላዊነት በመግለጽ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳቱን በሥርዓተ አምልኮ አፈጻጸም ሲያግዙ መቆየታቸውን ተናግረዋል።  

በመጨረሻም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ቤዛነቱን በገለጸበት ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ለትንሳኤው ክብረ-በዓል ምስጢር ቀጣይነት ማረጋገጫን በመስጠት፣ በአስጨናቂው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም በመላው ዓለም ካሉት ክርስቲያኖች ጋር ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ጸሎታቸውን በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ክቡር አባ ቪንቼንሶ ፔሮኒ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት አስረድተዋል።

02 April 2021, 00:32