ፈልግ

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የወጣቶች የሰላም ጉዞ በይፋ ተጀመረ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የወጣቶች የሰላም ጉዞ በይፋ ተጀመረ 

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የወጣቶች የሰላም ጉዞ በይፋ ተጀመረ

የአዲስ አበባ ካቶሊካዊ ሰበካ ሐዋርያዊ ጽ/ቤት ከሰበካው የምእመናን ሐዋርያዊ ተግባር ምክር ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሰላም ጉዞ በይፋ ተጀመረ። የጉዞ ማስጀመሪያ መርሃግብሩ በአዲስ አበባ መድኃኔዓለም ቁምስና በጸሎት የተጀመረ ሲሆን የመርሃግብሩ ተሳታፊዎች ከመድኃኔዓለም ቁምስና እስከ ብሔራዊ ትያትር ድረስ በጸሎት እና በዝማሬ የታጀበ የእግር ጉዞ አድርገዋል። በብሔራዊ ትያትር በተከናወነው የጉዞ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይም የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት የአስተምህሮ፣ የዝማሬ እንዲሁም የተለያዩ አዝናኝ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ የአዲስ አበባ ካቶሊካዊ ሰበካ ሐዋርያዊ ጽ/ቤት ኃላፊ የመክፈቻ እና የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል። በመልዕክታቸውም የሰላም ግንባታ የጋራ ጉዳይ በመሆኑ ሁላችንም በጋራ ለሰላም እንሥራ፣ በጋራ እንጸልይ በጋራ ወደ ሰላም እንጓዝ ብለዋል። በዕለቱ የተገኙ የክብር እንግዶችን በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በመርሃግብሩ አዘጋጆች ሁሉ ስም አመስግነዋል። የሰላም ሐዋርያ የሆነውን ቅዱስ ፍራንቸስኮስን በመዘከር ከኢትዮጵያ የካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ገዳም አባት የሆኑት ክቡር አባ ኃይለገብርኤል መለቁ መርሃግብሩን በጸሎት አስጀምረዋል።

ክብርት ወ/ሮ ወርቅ ነሽ ብሩ ከሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው። ሰላም በጎደለበት ቦታ አምልኮን እንኳን መፈጸም አይቻልም እና ይህንን ሰላም ላይ ትኩረት ያደረገ መርሃግብር በማዘጋጀታችሁ እና እኛንም እንድንሳተፍ ስለጋበዛችሁን ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ሰላምን መስበክ የሁላችን ድርሻ ነው። ሁላችንም የሰላም ሰባኪዎች ነን። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ወቅቱ የሚጠይቀውን የሰላም ሥራ ለመሥራት ወጣቶችን አነሳስታ እና አዘጋጅታ በማሠራቷ በሁሉም ዘንድ የሚያስመሰግናት ተግባር ነው። የሃይማኖት ተቋማት ወትሮም ዋነኛ ተግባራቸው ሰላም በሰዎች መካከል እንዲሰፍን ማድረግ በመሆኑ ቤተክርስቲያኒቷ ኃላፊነትዋን ለመወጣት የምታከናውነው ተግባር አካል ነው። ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የተለያዩ አስተምህሮዎች ሊኖሯቸው ቢችልም በሰላም ጉዳይ ግን በጋራ የምታደርጓቸው ተግባራት የመተሳሰብ ባህላችንን ቀጣይ ለማድረግ የሚያግዝ እና ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር በመሆኑ የሰላም ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግላችሁ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

ክቡር ዶ/ር ወዳጄ ነህ መሐረነ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስን ጠቅሰው ባስተላለፉት መልዕክት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለሰው ልጅ ሕይወት ከፍተኛ ክብር የምትሰጥ እና የሰውን ሕይወት እግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ማንም በምንም ምክንያት ሊወስድ አይችልም የሚል እጅግ የጸና እምነት ያላት ቤተክርስቲያን ናት። በመሆኑም የንጹሐን ደም እንዳይፈስ፣ ሰዎች እንዳይፈናቀሉ ድምጿን ከፍ አድርጋ ማሰማት እና ሰላም እንዲሰፍን መሥራት ባሕሪዋ ነው። በመሆኑም ወጣቶች በሀገራችን የሰላም ጉዞ ማቀዳችሁ ታሪክ የሚያስታውሰውን ተግባር ለመፈጸም የተነሳችሁ በመሆኑ በርቱ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን እላችኋለሁ። የሰላም ጥሪ ለማስተላለፍ በመላው ኢትዮጵያ በምታደርጓቸው ጉዞዎች የምታደርጉት ውጊያ ከአጋንንት ጋር ስለሆነ የማሸነፊያ መሳሪያዎቻችሁን መጽሐፍ ቅዱስን እና መቁጠሪያችሁን መያዛችሁን እንዳትረሱ። በጸሎት እና በተጋድሎ ድል አድርጋችሁ በሰላም እና በጤና እንድትመለሱ እመኝላችኋለሁ ብለዋል።

ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡራን እንግዶችን በተለይም የሰላም ተጓዦችን ካመሰገኑ በኋላ የሰላም ጉዞ የህሊናም ጉዞ ጭምር ነው። ሁላችንም በየተቀመጥንበት እንጓዘዋለን። ካሉ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት በቅርቡ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚል ባስተላለፉት ሰነድ ላይ አስተምህሮ አቅርበዋል። በአስተምህሯቸው ርእሰ ሊቃነጳጳሳት መልዕክታቸውን የሚጀምሩት “ዛሬ ዓለማችንን ጥቁር ጨለማ ከብቧታል” በማለት ነው። ኢትዮጵያችንንም እነዚሁ ጥቁር ደመናዎች ከብበዋታል። ሆኖም ሀገራችን የሚጸልዩላት፣ የሰላም መሳሪያ በመሆን የሚሠሩላት ዜጎች ስላሏት ለከበባት የደመና ጨለማ አትሸነፍም ብዬ አምናለሁ። ብለዋል።

ክቡርነታቸው የርዕሰ ሊቃነጳጳሳትን መልዕክት ሲያብራሩ የሰው ልጅ ያለመጠን በራስ ወዳድነት የማግበስበስ ባህሪ ውስጥ ወድቋል። አዳዲስ ከፋፋይ ግንቦችም በየቦታው ተገንብተዋል። በአካል ብቻ ሳይሆን በስነልቦናም ተለያይተናል። የመለያየት ግንባታን አብዝተንም የገነባናቸው ግንቦች እስረኞች ሆነናል። በዚህም ምክንያት ለጥላቻ ተጋልጠናል። ኢትዮጵያውያን በከተማ ስንኖር በቤቶቻችን አሠራሮች እጅግ የተጠጋጋን ብንመስልም ጉርብትናችን ግን በሃይማኖት እና በብሄር ግንቦች ፈርሷል። ተጠጋግተን እየኖርን እጅጉን የተለያየን ሆነናል።

ቅዱስነታቸው በሰነዳቸው የጠቀሱት የደጉ ሳምራዊ ታሪክ ውስጥ አይተው እንዳላየ ያለፉ እና ተጎድቶ የወደቀውን ሰው የረዳው ሁለት ዓይነት ሰዎች ይገኛሉ እኛም ሁለት ምርጫ ነው ያለን የወገኖቻችንን ሰቆቃ አይቶ እንዳላየ ማለፍ ወይንም ጎንበስ ብለን ቁስላቸውን ማከም። እኛ ካቶሊካውያን ግን ከተጎዱ እና ከተበደሉ ወገኖች ጎን እንድንቆም የወንድማማችነት ጥሪያችን ግድ ይለናል።

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሰላም ተጓዦች የሰላም ጥሪ እና መልዕክቶችን በመያዝ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ካቶሊካዊ ሰበካዎች ከዛሬ ሚያዝያ 3 ቀን 2013 ዓ.ም.  ጀምሮ የሰላም ጉዞ ያደርጋሉ። በብሔራዊ ትያትር በተከናወነው የጉዞ ማስጀመሪያ መርሃግብር  ላይ ቡራኬ እና ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

12 April 2021, 18:51