የመጋቢት 19/2013 ዓ.ም 2ኛ የዐብይ ጾም እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመጋቢት 19/2013 ዓ.ም 2ኛ የዐብይ ጾም እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የመጋቢት 19/2013 ዓ.ም 2ኛ የዐብይ ጾም እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.     ኦሪት ዘጸዐት 22፡1-2.9-13.15-18

2.     መዝሙር 115

3.     ሮሜ 8፡31-34

4.     ማርቆስ 9፡1-9

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የኢየሱስ መልክ አበራ

ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን አስከትሎ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ይዞአቸው ወጣ፤ ብቻቸውንም ነበሩ፤ በፊታቸውም ተለወጠ፤ ልብሱም በምድር ላይ ማንም አጣቢ አጥቦ ሊያነጣው በማይችልበት ሁናቴ እጅግ ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።

ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፣ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “ይህ የምወደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። ወዲያውም ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሮአቸው አልነበረም።

ከተራራው ላይ በሚወርዱበትም ጊዜ፣ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። እነርሱም የተናገራቸውን ቃል በልባቸው አሳደሩት፤ ነገር ግን፣ “ከሙታን መነሣት” ምን ማለት እንደሆነ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። (የማርቆስ ወንጌል 9፡2-10)

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ይህ ሁለተኛው የዐብይ ጾም እሁድ (የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ማለት ነው) በሦስቱ ደቀ መዛሙርት ፊት በተራራው ላይ የኢየሱስን መለወጥ እንድናስብ ይጋብዘናል (ማርቆስ 9፡ 1-10)። ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ከፍተኛ ሥቃይ እንደሚደርስበት ፣ ተቀባይነት እንደ ሚያጣ እና እንደሚገደል አስታውቆ ነበር። በጓደኞቹ ፣ በእነዚያ የቅርብ ወዳጆቹ ፣ በደቀ መዛሙርቱ ልብ ውስጥ ምን እንደነበረ መገመት እንችላለን - የኃይለኛ እና የድል አድራጊ መሲህ ምስል ወደ ቀውስ ውስጥ ገብቷል ፣ ህልሞቻቸው ተሰብረዋል ፣ እናም በጭንቀት ተውጠዋል ያመኑበት መምህር እንደ መጥፎ በደለኞች ይገደላል። በዚያው ቅጽበት በዚያ ነፍስ ጭንቀት ኢየሱስ ጴጥሮስን ፣ ያዕቆብን እና ዮሐንስን ጠርቶ ከእነርሱ ጋር ወደ ተራራ ላይ ወጣ።

ቅዱስ ወንጌል “እርሱ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ይዞአቸው ወጣ” ይላል (ማርቆስ 9፡2)። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተራራ ሁል ጊዜ ልዩ ጠቀሜታ አለው-ሰማይና ምድር የሚነካኩ የሚመስልበት ከፍ ያለ ቦታ ነው ፣ ሙሴ እና ነቢያት እግዚአብሔርን በተራራ ላይ የመገናኘት ልዩ ልምድ ነበራቸው። ተራራውን መውጣት በተወሰነ ደረጃ ወደ እግዚአብሔር መቅረብን ያመለክታል። ኢየሱስ ከሶስቱ ደቀ መዛሙርት ጋር ወደ ተራራ ላይ ወጣ እና እነሱ በተራራው አናት ላይ ቆሙ። እዚያ በፊታቸው ተለወጠ። ፊቱ እንደ ጸሐይ የሚያንፀባርቅ እና ልብሶቹም እጅግ ነጭ በመሆን እርሱ ከሞት እንደ ሚነሳ አስቀድመው እንዲረዱ እና ቅድመ እይታ እንዲኖራቸው፣ ለእነዚያ ፍርሃት ለዋጣቸው ሰዎች ብርሃንን ፣ የተስፋ ብርሃንን ፣ በጨለማ ውስጥ ለማለፍ የሚያስችላቸውን ብርሃን ይሰጣል - ሞት የሁሉም ነገር መጨረሻ እንደ ማይሆን እና ለትንሳኤ ክብር መንገዱን ይከፈታል። ስለዚህ ኢየሱስ እንደ ሚሞት ያስታውቃል፣ ወደ ተራራው ያወጣቸዋል ከዚያም በኋላ የሚሆነውን ትንሳኤ ያሳያል።

ሐዋርያው ​​ጴጥሮስ እንደተናገረው በተራራው ላይ ከጌታ ጋር ቆም ማለቱ ፣ ይህንን “የቅድመ እይታ” በዐቢይ ጾም ልብ ውስጥ ለመኖር ጥሩ ነው። በተለይም በአስቸጋሪ ፈተና ውስጥ ስናልፍ ይህንን ነገር ማስታወሱ ጠቃሚ የሚሆን ነገር ሲሆን - እናም ብዙዎቻችሁ በአስቸጋሪ ፈተና ውስጥ ማለፍ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንድታውቁ ይረዳል- ጌታ ተነስቷል እናም ጨለማ የመጨረሻው ቃል ሳይሆን ወደ ብርሃን የምንሻገርበት መንገድ ነው።

አንዳንድ ጊዜ በግል ፣ በቤተሰባችን ወይም በማህበራዊ ህይወታችን ውስጥ የጨለማ ጊዜዎችን በማሳለፍ እና መውጫ መንገድ እንደሌለ አድርገን በፍርሃት ውስጥ እናልፋለን። እንደ ህመም፣ ስቃይ ወይም የሞት ምስጢር ካሉ ታላላቅ እንቆቅልሾች በፊት ፍርሃት ይሰማናል። በዚሁ የእምነት ጉዞ ውስጥ ህይወታችንን በአገልግሎት እንድናሳልፍ እና በፍቅር እንድንበለጽግ የሚጠራን የመስቀል ላይ ስቃይ እና የቅዱስ ወንጌል ጥያቄዎች ሲያጋጥመን ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን። ስለዚህ የሕይወትን ምስጢር በጥልቀት የሚያበራ እና ከምልከታችን ባሻገር እና ከዚህ ዓለም መመዘኛዎች እንድንሻገር የሚረዳን የተለየ እይታ ያስፈልገናል። እኛም በሕይወታችን ውስጥ በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ የብርሃን ብልጭታዎችን በመፈንጠቅ እና የፋሲካን በዓል ድል ጀምሮ ታሪክን ለመተርጎም የሚረዳንን የተነሳውን ውበት ለማሰላሰል እኛ ወደ ተራራው እንድንወጣ ተጠርተናል።

ሆኖም ጥንቃቄ እናድርግ-ያ የጴጥሮስ ስሜት “እዚህ መሆናችን መልካም ነው” የሚለው ስሜት መንፈሳዊ ስንፍና መሆን የለበትም። በተራራው ላይ መቆየት እና በእራሳችን የዚህ ገጠመኝ ውበት መደሰት አንችልም። ኢየሱስ ራሱ በወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መካከል ወደ ሸለቆው እና ወደ ዕለታዊ ኑሮ ይመልሰናል። ከመንፈሳዊ ስንፍና መጠንቀቅ አለብን - ጸሎታችን እና ስርዓተ አምልኮዋችን ብቻ በራሱ በቂ ነው ብለን መዘናጋት የለብንም። በፍጹም እንዲህ ማድረግ የለብንም! ወደ ተራራ መውጣት ማለት እውነታውን መርሳት ማለት አይደለም፣ መጸለይ የሕይወትን ችግሮች ማስወገድ ማለት በጭራሽ አይደለም፣ የእምነት ብርሃን ውብ መንፈሳዊ ስሜቶችን ለማቅረብ የተሰጠን አይደለም። የለም በፍጹ እንዲህ አይደለም። ይህ የኢየሱስ መልእክት አይደለም። እኛም በእርሱ ብርሃን የበራነው እኛም ያንን ብርሃን ወስደን በሁሉም ቦታ አንፀባርቀን እንድንኖር የተጠራነው ከክርስቶስ ጋር የገጠመንን ሁኔታ እንድንለማመድ ነው። በሰዎች ልብ ውስጥ ትናንሽ መብራቶችን ማቀጣጠል፣ ትንሽ ፍቅር እና ተስፋ የሚሸከሙ የወንጌሉ ትናንሽ መብራቶች መሆን ይህ የክርስቲያን ተልእኮ ነው።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 21/2013 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት አስተንትኖ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

27 March 2021, 19:52