በሚያንማር አንዲት መንኩሴ የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ነፍስ እንዳያጠፉ ተንበርክከው ሲለምኑ  በሚያንማር አንዲት መንኩሴ የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ነፍስ እንዳያጠፉ ተንበርክከው ሲለምኑ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ከእህት አን የምስጋና መልዕክት መድረሳቸው ተገለጸ

በሚያንማር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መነኩሴ የሆኑት እህት አን ታዋንግ የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች፣ ራስን መከላከል በማይችሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚፈጽሙት የግድያ ተግባር እንዲቆም በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመደገፋቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአገሪቱ ውስጥ ከጥር 1/2021 (እ.አ.አ) ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የሕዝብ  ተቃውሞ ዋና ምክንያት ከፍተኛ የሕዝብ ድምጽን በማግኘት አገርን እንዲመሩ የተመረጡት የቀድሞ ፕሬዚደንት አውንግ ሳን ሱ ኪ እንዲፈቱ እና በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲረጋገጥ የሚል መሆኑ ሲታወቅ የሕዝብን ተቃውሞ እና አመጽ ለማስቆም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የወሰዱት ከባድ ጥቃት በርካታ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን ይህም ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ትኩረትን መሳቡ ተገልጿል።  

“ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን እናመሰግናለን”

“ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ 2017 ወደ ሚያንማር ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረጋቸው የሚያንማርን ሕዝብ ያውቃሉ” በማለት ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸው ምስጋናቸውንም አቅርበውላቸዋል። ከባድ የጦር መሣሪያን የታጠቀ የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይል የካቲት 21/2013 ዓ. ም ሰልፈኞችን ለመበተን ተኩስ በከፈቱ ጊዜ ከሰልፈኞቹ መካከል በርካታ ወጣቶች መሸሸጊያን ፈልገው ወደ ክሊኒካቸው መምጣታቸውን እህት አን ለቢቢሲ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል። የጸጥታ አስከባሪ ኃይሉ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጽሙ በማለት ወደ ጸጥታ አስከባሪዎች ቀርበው “ራስን መከላከል በማይችሉ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም” በማለት ተንበርክከው ለምነዋል።  

“እኔን ግደሉኝ”

የጸጥታ አስከባሪዎች በበኩላቸው እህት አንን እንደሚያከብሯቸው፣ ነገር ግን ሰልፈኞቹ ሥርዓት እንዲይዙ ለማድረግ እንደሚፈልጉ አስረድተው፣ እህት አን በከባድ አደጋ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል። እህት አን በበኩላቸው ጥያቄያቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚያቀርቡ ሰልፈኛን በጦር መሣሪያ ማጥቃት ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተው “ከፈለጋችሁ እኔን ግደሉኝ” በማለት ተንበርክከው መለመናቸው በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በመላው ዓለም ተሰራጭቶ የብዙዎችን ድጋፍ ማግኘቱ ታውቋል።   

ቅዱስነታቸው፡ “እኔም ተንበርክኬ እጠይቃለሁ”

እህት አን ተንበርክከው ያቀረቡት ጥያቄ ልባቸውን እንደነካቸው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሳምንታዊው የረቡዕ ዕለት ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአችው ወቅት ገልጸው፣ የመነኩሴዋን ጥያቄ በድጋሚ አቅርበዋል። ቅዱሰነታቸው ሐዘናቸውን በመግለጽ ባስተላለፉት መልዕክታቸው የሚያንማር ሕዝብ ስቃይ በአስቸኳይ እንዲያበቃ ድምጽ ማሰማት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት በተለይም የወጣቶችን ሕይወት ከሞት በማትረፍ ለአገሪቱ ተስፋን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን መልዕክት ሲያጠናክሩ “እኔም በሚያንማር ጎዳና ላይ ተንበርክኬ እጆቼን በመዘርጋት ሁከት ቆሞ ውይይት እንዲደረግ እጠይቃለሁ!” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የእያንዳንዱ ክርስቲያን ተግባር

ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎችን ተንበርክከው የለመኑት እህት አን፣ የሕዝብ አመጽ እና ጥያቄ በሰላማዊ ውይይት ምላሽ እንዲያገኝ በማለት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ጥሪ በማስተወስ፣ የቅዱስነታቸው የርኅራሄ ስሜት የእያንዳንዱ ክርስቲያን ስሜት እንዲሆን አሳስበዋል። “ከሕዝባችን ጎን ሆነን ስቃያቸውን እንካፈላለን” ያሉት እህት አን፣ በሚያንማር የሕዝብ ተቃውሞ ከቀን ወደ ቀን እያደገ በመምጣቱ የተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል። በአካባቢያቸው አገልግሎት የሚሰጡ ክሊኒኮች መዘጋታቸውን እህት አን አስታውሰው፣ በአካባቢው የተጎዱትን ተቀብሎ መጠነኛ የሕክምና አገለግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የማኅበራቸው ክሊኒክ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ጉዳት ከደረሳባቸው ሰልፈኞች መካከል በቂ ሕክምናን ካለማግኘት ብዙዎች እየሞቱ መሆኑን እህት አን አስረድተዋል።

የተስፋ ምልክት

ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከተላከላቸው መልዕክት ተስፋን ማግኘታቸውን የገለጹት እህት አን፣ የቆሰለን ማከም ተልዕኮአቸው በመሆኑ እንደማያቋርጡ ገልጸው፣ ዓላማቸውም የተጎዱትን ማፅናናት እና ሕይወትን ከሞት ማዳን መሆኑን ተናግረዋል።  

23 March 2021, 15:25