የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፣ ክርስቲያኖች ልባቸውን አንድ እንዲያደርጉ አሳሰበ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤቱ ከነሐሴ 25 - ጳጉሜ 3/2014 ዓ. ም. የሚካሄደውን 11ኛ ጠቅላላ ጉባኤን በማስመልከት ባለ 24 ገጽ የአስተንትኖ ሰነድ ማሳተሙ ታውቋል። ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተወጣጡ በርካታ የባሕል ጠበብት ሥራ ውጤት የሆነው ጽሑፉ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያን ማኅበረሰብ በሙሉ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ እርግጠኝነት የሌለው ዓለማችን፣ የዲጂታል አብዮት አሻሚነት ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፣ ማህበራዊ ኢፍትሃዊነት እና እየጨመረ የመጣው ጥላቻ እና ዘረኝነት በሚታይበት ባሁኑ ጊዜ አዲስ የሐዋርያው አገልግሎት ዘዴን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ያሳስባል።
ከዚህ በፊት በየስምንት ዓመታት በልዩ ልዩ አገራት ከተሞች ሲካሄድ የቆየው ጠቅላላ ጉባኤው፣ “የኢየሱስ ፍቅር መላው ዓለምን ለእርቅ እና ለአንድነት ይመራል በሚል መሪ ቃል” በመስከረም ወር 2013 ዓ. ም. ለማካሄድ የታቀደ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደሚቀጥለው ዓመት እንዲዛወር መደረጉ ታውቋል።
የፍትህና የሰላም ንግደት
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት በ2005 ዓ. ም. በደቡብ ኮሪያ፣ ቡሳን ከተማ ባካሄደው 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት የጀመረውን የፍትህ እና የሰላም መንፈሳዊ ጉዞን በ2014 ዓ. ም. የሚቀጥ መሆኑን አስታቆ፣ በቀጣይ መንፈሳዊ ጉዞም ወቅትም ለመጀመሪያ ጊዜ የእግዚአብሔር ፍቅር የሆነው ቅድስት ስላሴ በኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ ፍቅር በሰው ልጆች እና በመላው ፍጥረት መካከል የሚመላለስ መሆኑን ሰነዱ አመልክቷል።
ቅዱስ ወንጌልን መሠረት ያደረገው መሪ ቃሉ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተክርስቲያን የምትመራው በኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እና ይህም የክርስቲያኖችን የልብ አንድነት የሚገልጽ መሆኑን የአስተንትኖ ሰነዱ አስታውቋል። በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙ በርካታ ምዕመናን ለክርስቲያን አንድነት ያለን ምኞት በዕውቀትን እና በተቋማት ግንኙነት ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን በልባዊ ግናኑነት፣ በጋራ ጸሎት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በእርስ በእርስ ፍቅር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያስፈልጋል በማለት ሰነዱ አስተያየቱን ገልጿል።
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት እንደገለጸው የአንድነት ጥሪ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ግልጽ ባደረገው በራስ መተማመን እና መመካት እንዲሁም ስለ ራስ ብቻ ማሰብ ምኞት እንጂ ወደየትም እንደማያደርስ፣ የሰው ልጅ አቅመ ደካማ የሆነ የፍጥረት ወገን መሆኑን እና በተጨማሪም በዓለም ላይ ያሉ ብዙ የኑሮ አለመመጣጠኖችን የበለጠ ወደ ብርሃን ማውጣቱ ታውቋል።
አብያተ ክርስቲያናት ምሳሌ እንዲሁኑ ተጠርተዋል
በዚህም መሠረት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፣ ክርስቲያኖች ከመቸውም በበለጠ ምሳሌ በመሆን ለዓለም ደኅንነት ሲሉ፣ ድምጻቸውን በማስተባበር እውነተኛ ተስፋን በመናገር በመሆን፣ የአንድነት መንፈስን በማደስ፣ የደበዘዘ የፖለቲካ ንግግሮች ባዶ ተስፋን ወደ ጎን በማድረግ፣ በራስ ወዳድነት ላይ ከተመሠረተ ቁሳዊ ፍላጎቶች በመራቅ፣ የተፈጥሮ ሃብትን ለጋራ ጥቅም በማዋል፣ የኑሮ አለመመጣጠንን ግልጽ በማድረግ፣ ሁሉን ሰው የሚያቅፍ አዲስ ሰብዓዊ ክብርን መገንባት እንደሚያስፈልግ የአስተንትኖ ሰነዱ ገልጿል። ተደብቀው የሚኖሩ እና የሚጸልዩ አብያተ ክርስቲያናት፣ ግለኛ ማኅበረሰብ፣ ተለያይተው የሚኖሩ አብያተ ክርስቲያናት፣ ከሞት የተነሳውን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪን ሰምተው ወደ ዓለም ዘንድ እንዲሄዱ አክሎ አስታውቋል።
ዓለም ፍቅርን፣ ማኅበራዊ አንድን፣ ፍትህን እና ተስፋን ተጠምቷል ያለው ሰነዱ፣ ልዩነት በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ወደ አንድነት መድረክ ቀርበው ለሰው ዘር በሙሉ እና ለፍጥረታት በሙሉ አዲስ መጻዒ ዕድልን በማመቻቸት፣ በራዕይ ላይ እንደተገለጸው ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ዓለምን ወደ እርቅ እና አንድነት ሊያቀርብ ይገባል በማለት የአስተንትኖ ሰነዱ አሳስቧል።