ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውርን የሚቃወም ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውርን የሚቃወም ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት  

ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውርን የሚቃወም ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት

“ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር የሌለበት ኤኮኖሚ” በሚል መሪ ቃል በበይነ መረብ አማካይነት ሰኞ የካቲት 1/2013 ዓ. ም. የሚደረገውን ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ምዕመናን እንዲካፈሉ ጥሪ ቀረበ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

መላው ምዕመናን እንዲካፈሉ ጥሪ የተደረገበት 7ኛ ዙር ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር አስከፊ ገጽታ ላይ የሚያስተነትን መሆኑ ታውቋል። የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን ያስተባበረው “ታሊታ ኩም” የተሰኘ፣ ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውርን የሚቃወሙ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ኅብረት የበላይ አለቆች ጥምረት ሲሆን በጥምረቱ ውስጥ ካሪታስ ኢንተርናሽናል፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊክ ሴቶች ኅብረት፣ የፎኮላሬ እንቅቃሴ እና ሌሎች ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት የተዋቀሩ በርካታ እንቅስቃሴዎች መጠቃለላቸው ታውቋል። የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ አስተባባሪ ኮሚቴ እንዳስተወቀው ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ  በበይነ መረብ አማካይነት በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ፣ ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውርን በግል ሆነ በማኅበር የተደራጁ ማኅበራት በጋራ እንዲሳተፉ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።  

ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር የሌለበት ኤኮኖሚ

ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ኮሚቴ በድረ-ገፁ እንዳስነበበው፣ እ.አ.አ 2021 የሚከበረው ዓለም አቀፍ ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር ቀን መሪ ቃል “ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር የሌለበት ኤኮኖሚ” የሚል መሆኑን አስታውቆ፣ ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር የተስፋፋበት ዋናው ምክንያት፣ ገደቦች እና ተቃርኖዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲባባስ የተደረገው የዘመናችን ዋነኛው የኢኮኖሚ ሞዴል መሆኑን አስታውቋል።

ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የጸሎት እና የአስተንትኖ ሥነ-ሥርዓት ዋና ዓላማ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ማንኛውንም ብዝበዛን የመቃወም አዲስ የኤኮኖሚ ሥርዓትን ለማሳደግ የሚጋብዝ መሆኑ ታውቋል። የጸሎት ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ኮሚቴው በማከልም ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር የሚታወስበት የካቲት 1፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት በባርነት ሕይወት ስትሰቃይ የኖረች ባኪታ ቅድስና የታወጀበት ዕለት እና ቤተክርስቲያኒቱ ባርነትን ለመዋጋት መሆኑን አስታውቆ፣ ቤተክርስቲያኗ ባርነትን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነት የምትገልጽበት ዓለም አቀፋዊ ምልክት መሆኑ ታውቋል።

“ታሊታ ኩም” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ኅብረት አስተባባሪ የሆኑት እህት ገብርኤላ ቦታኒ የዘንድሮውን ተነሳሽነት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ባቀረቡት የኤኮኖሚ ሥርዓት ሃሳባቸው፣ በዓለማችን የተዘረጋውን ታላቁን የኢኮኖሚ ሞዴል ቤተክርስቲያኗ ቆም ብላ እንድታስብ እና አማራጭ መንገዶችን እንድትፈልግ መጠየቃቸውን አስታውሰው

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ከፍተኛ የኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚታይበት፣ ትክክለኛ የገበያ ስርዓትን የሚያፈርስ፣ በሰብዓዊ ክብር ላይ የተመሠረተውን የማኅበራዊ ሕይወት እሴቶችን የሚሸረሽር ከመሆኑ በተጨማሪ የአካባቢ ጥበቃን አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን አስረድተዋል። ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ኅብረት አስተባባሪ እህት ገብርኤላ ቦታኒ በማከልም የኅብረቱ ዋና ጥረት፣ የሰውን ልጅ ሕይወት የሚያሳድግ ኢኮኖሚን ​​መገንባት እና የሚያስከብር ሥራን ለሁሉ ሰው መፍጠር መሆኑን አስረድተዋል።   

በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ስለ መሳተፍ

አስተባባሪ ኮሚቴ እንዳስተወቀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በበይነ መረብ አማካይነት እንዲካሄድ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በዓለማችን ተስፋፍቶ በሚገኘው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መሆኑን ገልጿል። ሰኞ የካቲት 1/2013 ዓ. ም. የሚከበረው ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር ቀን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ከእኩለ ቀን ጀምሮ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን፣ በየአህጉራቱ የሚገኙ የ“ታሊታ ኩም” ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ኅብረት በአንድነት የሚያቀርቡት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል። የጸሎት አስተባባሪ በማከልም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዕለቱን ምክንያት በማድረግ የቪዲዮ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ገልጾ በዩቲዩብ ማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት በቀጥታ የሚተላለፍ መሆኑን አስታውቋል። ዓለም አቀፍ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀንን በተመለከተ መረጃዎችን “#PrayAgainstTrafficking” በሚለው “ሃሽ ታግ” ማኅበራዊ አውታረመረብ በኩል ማግኘት የሚቻል መሆኑን አዘጋጅ ኮሚቴው ጨምሮ አስታውቋል።

08 February 2021, 11:19