እጃችንን ወደ እግዚአብሔር እንዘርጋ እጃችንን ወደ እግዚአብሔር እንዘርጋ  

ራስህን መናቅ

በእውነት ቅዱሳን ለመሆን ብንፈልግ ባለማወላወል ክርስቶስን ለመከተል እንፈልጋለን; አዎ እንግዲህ እርሱ የሚለንን እንስማ፡፡ «እኔን ለመከተል የሚፈልግ ራሱን የካድ፣ ያለውን ሁሉ ያልናቀ የእኔ ደቀ መዝሙር ሊሆን አይችልም´ (ሉቃ. 14፣33 )፡፡ ይህንን ሳናደርግ በይበልጥ ክርስቶስን ልንከተለውና ፍጹማን ክርስቲያኖች ለመሆን አንችልም፡፡ ራሳችንን ከፍ ከፍ እያደረግን በፈቃዳችን እየሄድን እንዴት የክርስቶስ ነን ለማለት እንችላለን; ምኞታችንንና ሐሳባችን እየተከተልን እንዴት አድርገን ከእርሱ ጋር እንስማማለን; ይህ መጥፎ አመል እስካለብን ድረስ የክርስቶስን መንገድ መከተል የማይታሰብ ነው፡፡ በእውነት እንድንከተለው ከፈለግን የግዴታ ራሳችንን መካድና መናቅ አለብን፣ራስን መካድና መናቅ ከባድ ነገር ነው፡፡ ራስህን መካድ ትልቅ መንፈሳዊ ጀግንነት ነው፡፡ እኛ ስንት ጠላቶቻችንን እናሸንፋለን; በዚህም ረገድ ከፍተኛ ሚና እንጫወታለን ራሳችንን ማሸነፍ ግን ያቅተናል፣ ኃይል ያጥረናል፣ የሚቋቋመንን ሁሉ ለማሸነፍ እንታገላለን፣ ብርቱ ጥረት እናደርጋለን፣ ራሳችንን ለማሸነፍ ግን ቀላላ መከራን እንኳ አንጋፈጥም፣ ጥረት አናደርግም፡፡ ትልቁ ጠላታችን ራሳችን ነን፣ የሚበልጠው ጉዳት ራሳችንን ካለማሸነፋችን የሚመጣ ነው፡፡ ራሳችንን ካለመካድና ካለመናቅ የተለየ ኃጢአት፣ ትዕቢት፣ ራሳችንን ከፍ ከፍ ማድረግ፣ ቅናት፣ ጥላቻ፣ በቀል፣ ወዘተ … ይወለዳሉ፡፡ ለራሳችን እንዲመቸን እንዋሻለን፣ አመጽ እንፈጽማለን፣ እናወናብዳለን፡፡ ራሳችንን ከተነካን እንቆጣለን፣ እናዝናለን፡፡ ይህም ራሳችንን ስለምንወድ ነው፡፡ ሀብታሞችና ከበርቴዎች ለመሆን እንፈልጋለን፣ በጣምም እንመኛለን፣ ከተጋድሎና ከዝቅተኛ ወራዳ ሥራ እንሸሻለን፡፡ የራሳችንን ፍቅር ስለሚያይልብን ትዕግሥት፣ ትሕትና፣ የዋሕነት፣ ምሕረት፣ ድህነት መታዘዝ ይከብደናል፡፡

የኃጢአት ሥራ ራስን ከፍ ከፍ በማድረግ ነው፡፡ ይኸውም ከአርስተ ኃጢአት የመጀመሪያ ቦታ ከያዘ ትዕቢት የሚመነጭ ነው፡፡ እንግዲህ ተመላልሰን በኃጢአት የመውደቅ ምክንያት ራሳችንን ማሸነፍ ካለመቻላችን የመጣ ነው፡፡ ቁርጥ ፈቃዳችን አንድ አፍታ ሳይቆይ እንደ ጉም በኖ የሚቀረው በመንፈሳዊነት የማንቀጥለው ራሳችንን መናቅ ስላቃተን ነው፡፡ መንፈሳችን ቀዝቅዛ፣ ሕይወታችን ቀላልና ቸልተኛ ሆኖ የሚገኘው በራሳችን ፍቅር ነው፡፡ የራሳችን ፍቅር ወደ የት እንደሚደርሰን እንመርምር፡፡

ራሳችንን መናቅ ከቻልን ግን የትዕግሥት፣ የፍቅር፣ የሰላም ሰዎች እንሆናለን፣ ትሕትና፣ ተጋድሎ፣ ድህነትን እንወዳለን፣ መስቀላችንን በደስታ እንሸከማለን፡፡ በመንፈስ ጠንቃቆች፣ አስተዋዮች፣ ትጉሆች እንሆናለን፡፡ ራሳችንን ስናሸንፍ ኃይለኛ የቅድስና ፍላጐት በልባችን ያድራል፣ በመንፈስም ወደ ፊት እንሄዳለን፡፡

ፍጹም ክርስቲያኖች እንድንሆን ታማኝ የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን ፍላጐት ካለን ራሳችንን እንናቅ፡፡ የቅድስና መሠረት ራስን ማሸነፍ መቻል ነው፡፡

01 February 2021, 13:59