አሮጌ ሰውና አዲስ ሰው አሮጌ ሰውና አዲስ ሰው 

አሮጌ ሰውና አዲስ ሰው

“ወንድሞቼ ሆይ አሮጌ ሰውነታችን ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ ሞቶአል” (ሮሜ 7፡7) በኃጢአት የተበላሸ አሮጌ ሰውነታችሁን አስወግዱ፣ መንፈሳችሁንም አሳድሱ፡፡ ያለጽድቅ በእውነት በንጽሕና በእግዚአብሔር የተፈጠረ አዲስ ሰውነት ልበሱ´ እያለ ያሳስበናል ያስጠነቅቀናልም፡፡ የቀድሞ አሮጌው ማነው; የባሕርያዊ የምድራዊ ሰው ነው፣ በኃጢአት የተበከለ አዳም ነው፣ በተፈጥሮ ባሕርይ ሕግ የሚሄድ በግዙፍ ነገር የሚኖር ግዙፍ ነገርን የሚፈልግ ሰው ነው፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህ ሰው የመንፈስ ነገር አይገባውም፣ በመንፈስ አያብብም፣ አሮጌ ሰው የዓለምና የኃጢአት ባሪያ ነው፡፡ የድሮ ሰው ገና ከኃጢአት ሥር የሚኖር የደኀንነት ጸጋ ያልደረሰው ነው፣ የእርግማን የጥፋት ልጅ ነው፡፡ አዲስ ሰውስ ማነው; የአሮጌ የቀድሞ ሰው ተቃራኒ ነው፣ የቡራኬና የደኀነት ጸጋ ልጅ ነው፣ የእግዚአብሔር ልጅና የመንግሥተ ሰማያት ወራሽ አዲስ ሰው መንፈሳዊ የእግዚአብሔርን የሚፈልግ ነው፣ ከክርስቶስም ጋር ከኃጢአት ሞት የተነሣ ነው፣ በክርስቶስ ጸጋዎች የተሸለመ ያጌጠ በብርሃን የሚገኝ የክርስቶስ ኢየሱስ አምላኪና ተከታይ ነው፡፡ የአሮጌ ሰው ፍጻሜ ጥፋትና ሃዘን ነው፣ የአዲስ ሰው ፍፃሜ ግን ደኀንነትና የመንግሥተ ሰማያት ደስታ ነው «አሮጌውን ሰውነታችሁን አስወግዳችሁ አዲሱን ልበሱ´ እያለ ይመክረናል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡

ከክርስቶስ ከአሮጌ ሰው ኑሮ ሊያወጣን ወደ አዲስ ሰውነት ሊለውጠንና ከፍ ሊያደርገን ወደ ምድር መጣ፡፡ በዚህ ሐሳብ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ሰጠ፡፡ አሮጌ ሰውነት የሰይጣን ልጅና የኃጢአት ባሪያ ከክርስቶስ ጋር ተሰቀለ፣ ከእርሱ ጋር ሞተና ተቀበረ፡፡ በዚያውም ቀረ አዲስ ሰው ብቻ ነው ከእርሱ ጋር አብሮ የተነሣ፡፡ ሰውነታችንም በሞት ከእርሱ ጋር ታድሶአል፣ ይህን ያገኘነውን አዲስ ሕይወት እንዳናበላሸው እንድንጠነቀቅ ያስፈልገናል፡፡ በክርስቶስ ሞት ወደ ተሸነፈው አሮጌ ሰውነት መመለስ ያስነውረናል፣ ከዚህ አሮጌ ሰውነት ለመራቅ ከኃጢአት ኑሮ መሸሽ አለብን፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የመጣውን አዲስ ሰውነት እንልበስ በዚህ አዲስ መንፈስ እንመላለስ፡፡

26 February 2021, 12:20