“ሥነ-ጥበብ፣ አብይ ጾምን እና የኢየሱስን የሕይወት ምስጢራት በተግባር እንድንኖር ያስተምረናል”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የአብይ ጾም ወቅት በአራተኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ፣ የጥምቀት ምስጢርን ለመቀበል የሚዘጋጁትን ሰዎች የሚያበረታታ የመንፈስዊ ጉዞ ወቅት ነው። ይህን ወቅት ምዕመናን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ መታሰቢያን በመጠባበቅ፣ በየዓመቱ በጸሎት፣ በጾም እና የተቸገሩትን እየረዱ በትጋት እንዲጓዙት በማለት ቤተክርስቲያን ታሳስባለች። በዚህ የአብይ ጾም ወቅት ምዕመናን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንዲገነዘቡ ለማድረግ እና የአምልኮ ሥርዓት ትርጉሞችን በተጨባጭ ሁኔታ እንዲያውቁ ለማገዝ ቅዱሳት ምስሎችን ማቅረብ የቤተክርስቲያን የአገልግሎት ድርሻ ነበር። በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የባሕል አገልግሎት ፋካልቲ ዳይሬክተር የሆኑት ብጹዕ አቡነ አንድሬያ ሎናርዶ፣ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ787 ዓ. ም. የተካሄደውን ሁለተኛውን የኒቂያ ጉባኤ ሰነድን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ ኢየሱስ ክርስቶስን በሥነ-ጥበብ ሥራዎች አማካይነት ወደ ሰዎች ዘንድ ማቅረብ እና ስጋ የመልበሱ እውነት የሚረጋገጥበት መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ አንድሬያ ሎናርዶ በማከልም ስለ እግዚአብሔር ለመመስከር ቅዱሳት ምስሎች የሚያበረክቱት አገልግሎት ከቃላት የበለጠ በመሆኑ በቤተክርስቲያን ውስጥ እነዚህን ምስሎች መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።
“ምስጢራቶቹ”
ክርስቲያናዊ ምስሎች፣ እግዚአብሔር አብ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በስጋ መገለጡን ያመለክታሉ። በመሆኑም ቅዱሳት የሥነ-ጥበብ ሥራዎች በቤተክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት እና መንፈሳዊ በዓላት ወቅት የኢየሱስ ክርስቶስን የአገልግሎት ሕይወት እና ምስጢራትን ለማብራራት እና ለማስተማር ያገለግላሉ። መንፈሳዊ የጥበብ ሥራዎች የአምልኮ ሥርዓት መልዕክቶችን በታማኝነት በስዕል ያስተላልፋሉ። ብጹዕ አቡነ አንድሬያ ሎናርዶ የአብይ ጾም ወቅትን በማስመልከት ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ በአሥራ አንደኛው ክፍለ ዘመን የተሳለው የፎርሚስ ቅዱስ መልአክ የቤተ-መቅደስ ሥዕሎች፣ ከብርሃነ ትንሳኤው በፊት ባሉት የእሑድ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ የሚነበቡትን የቅዱስ ወንጌል ክፍሎች የሚያብራሩ ናቸው።
ሥነ-ጥበብ እና ስርዓተ አምልኮ
መንፈሳዊ ሥነ-ጥበብ፣ የአምልኮ ሥርዓትን ደረጃ በደረጃ እንደሚገልጽ ያስረዱት ብጹዕ አቡነ አንድሬያ ሎናርዶ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የፈተና ጊዜን በማስታወስ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ”? ተብሎ መጠየቁን አስታውሰው ቀጥሎም በኢየሱስ ክርስቶስ መለውጥ፣ ከዚያም በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር መገናኘቱን፣ ቀጥሎም ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው መፈወሱን እና አልዓዛርን ከሞት ማስነሳቱን እንደሚገልጽ አስረድተው፣ ከቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል የተወሰዱ የኢየሱስ ክርስቶስ የአገልግሎት ክፍሎች፣ ከጥንት ቤተክርስቲያን ጀምሮ ሰዎችን ለምስጢረ ጥምቀት ለማዘጋጀት ያገለግላሉ መሆኑን አስረድተዋል።
በዐመድ የመቀባት ስርዓት
የዐቢይ ጾም መጀመሪያ የሆነው በዐመድ የመቀባት ስርዓት ለምን በመንፈሳዊ ሥነ-ጥበባት በኩል አልተገለጸም? ለሚለው ጥያቄ ብጹዕ አቡነ አንድሬያ ሎናርዶ ሲመልሱ “በዐመድ የመቀባት ስርዓት ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች አንዱ እንጂ በአገልግሎት ሕይወቱ ውስጥ የተከናወነ አይደለም” በማለት አስረድተዋል። አክለውም “ኪነ-ጥበብ ክርስቶስ በተናገረን ቃል ላይ ፣ በክርስቶስ ሕይወት እና በክርስቶስ ምስጢራት ላይ ያተኮረ ነው” ብለዋል፡፡
ጸሎት፣ ጾም እና ምጽዋት
ጸሎት፣ ጾም እና ምጽዋት፣ የአብይ ጾም ወቅት ምርኩዞቻችን፣ በኪነ-ጥበብ ውስጥ ሰባት የምሕረት ሥራዎች የተገለጹባቸው ናቸው። መንፈሳዊ ሥራዎችን የሚገልጹ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች በጣሊያን፣ ናፖሊ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የካራቫጆ ድንቅ ሥራዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው ፡፡
የምህረት ሥራዎች
የሮማ ሀገረ ስብከት የባሕል አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት ብጹዕ አቡነ አንድሬያ ሎናርዶ “ፒዮ ሞንቴ ዴላ ሚዜሪኮርዲያ” የሸራ ላይ ቅብ፣ በጣሊያን የናፖሊ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ሰባት ምዕመናን፣ የቸርነት ሕይወትን ለመኖር በማለት ራሳቸውን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እ.አ.አ በ1602 ዓ. ም. በማቅረብ ያቋቋሙትን ተቋም የሚያስታውስ ነው። እውቁ ጣሊያናዊ የኪነ-ጥበብ ሰው ካራቫጆ፣ በዚህ የሸራ ቅብ ስዕሉ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከወንድ እና ሴት የናፖሊ ምዕመናን መካከል ሰባቱን መምረጧን ያመለክታል። ሰባቱ የምህረት ሥራዎችም በአምስት ክፍሎች ተለይተው ተመልክተዋል። የታረዙትን የሚያለብስ፣ የታመሙትን የሚጎበኝ ቅዱስ ማርቲን፣ የእግዚአብሔርን ፊት ለመመልከት ወደ ሳንቲያጎ ደ ኮምፖስቴላ የሚደረግ ንግደት አስፈላጊነት ለማጉላት፣ ሙታንን የሚቀብር፣ ሳምሶን ከእግዚአብሔር ውሃን ተቀብሎ አህያውን ማጠጣት፤ በመጨረሻም እስረኞችን መጎብኘት እና የተራቡትን መመገብ፣ በእስር ቤት ውስጥ ለሚገኙት ቺሞን የተባለ አዛውንት የቸርነት ሥራን ማበርከትን፣ በረሃብ ምክንያት ለሞት የተዳረጉ ሰዎችን አንዲት ሴት ልጅ ከጡቷ ወተት እንዳቀረበችላቸው፣ እውቁ ጣሊያናዊ የኪነ-ጥበብ ሰው፣ ካራቫጋጆ በስዕሉ አመልክቷል።
የአብይ ጾም ወቅት በጎ አድራጎት ጊዜ ነው
የሮማ ሀገረ ስብከት የባሕል አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት ብጹዕ አቡነ አንድሬያ ሎናርዶ፣ የአብይ ጾም ወቅት፣ ድሆችን እና የተቸገሩትን በቸርነት ዓይን በመመልከት ዕርዳታችንን የምንለግስበት ወቅት መሆኑን ገልጸው፣ ጾም፣ መልካም ተግባር ለሌሎች ማድረግን እንድንማር የሚያግዘን መሆኑን እና ጸሎትም የሰው ልጅ በእንጀራ ብቻ አለመኖሩን የምንማርበት መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ አንድሬያ ሎናርዶ በመጨረሻም ቤተክርስቲያን የምታስተምረን ሰባቱ የምሕረት ተግባራት፣ የሚጠራጠሩትን ማጽናናት፣ አላዋቂዎችን ማስተማር፣ ኃጢአተኞችን መገሰጽ፣ የተጎዱትን መርዳት፣ የበደሉንን ይቅር ማለት፣ ችግር የሚፈጥሩትን መታገስ፣ በሕይወት ላሉት እና ለሞቱ ሰዎች መጸለይ እንደሆኑ አስረድተው፣ እነዚህን ተግባራት እያንዳንዱ ምዕመን በአብይ ጾም ወቅት በተግባር ሊያከናውናቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።