ኢየሱስ 12 አመት በሞላው ጊዜ በቤተመቅደስ ከጠቢባን ጋር ሲነጋገር እና ስያስተማራቸው ኢየሱስ 12 አመት በሞላው ጊዜ በቤተመቅደስ ከጠቢባን ጋር ሲነጋገር እና ስያስተማራቸው  

የጥር 30/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘጥምቀት - አስተርእዮ 3ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.    ገላ. 4፡21-31

2.   1ጴጥ 2፡1-8

3.   ግ.ሐዋ. 5፡17-28

4.    ሉቃ 2፡42-52

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ወላጆቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ። በዓሉን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹ ግን መቅረቱን አላወቁም ነበር። አብሮአቸው ያለ መስሎአቸው፣ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላ ግን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ዘንድ ይፈልጉት ጀመር፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር። ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።

እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። እነርሱ ግን የተናገራቸው ነገር አልገባቸውም። ከዚያም አብሮአቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር። ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።

 

የእለቱ አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር  ዘጥምቀት - አስተርእዮ 3ኛ ሰንበትን እናከብራለን። በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ መልእክቶቹ እና ወንጌሉ አማካኝነት ወደ እያንዳዳችን በመምጣት የሚያስፈልገንን ይሰጠናል የጎደለውን ሁሉ ይሞላልናል በእርሱም ቃል እንድንኖር ያበረታታናል።

እያንዳንዳች ከእግዚአብሔር ጋር እንድንነጋገር የእግዚአብሔር ቃል ይገፋፋናል ይጠራናልም፤ የሚናገር እግዚአብሔር እኛ ለእርሱ እንዴት መናገር እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ እዚህ ላይ በዘልማድ ስለ መዝሙረ ዳዊት እናስባለን እዛው ውስጥ እግዚአብሔር ለእርሱ እንድንናገር ቃላትን ይሰጠናል፣ ሕይወታችንን ለእርሱ አደራ እንሰጣለን፤ ሕይወት ራሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመራን መንገድ ነው።

በመዝሙር እንደምናየው የሰው ልጅ እያንዳንዱ ፍላጎት በእግዚአብሔር ፊት ግልጽ ሆኖ ይገኛል፤ ደስታና ስቃይ፣ ጭንቀትና ፍስሐ፣ ፍርሐትም ጭምር ተገልፆ እናገኛለን፤ ከመዝሙረ ዳዊት ውጭ ወደ እግዚአብሔር እንድንመለስ የሚረዱን የመማጸኛ ጸሎት መፅሐፎችም በብዛት እንዳሉ እናውቃለን (ዘጸ 33፡ 12-16) በድል ጊዜ የሚደረግ የደስታ መዝሙር (ዘጸ 15) ፣ ተልዕኮአችንን ለመወጣት የሚያግዱን ጉዳዮች ሲያጋጥሙን ስለሚሰማው ሐዘንና (ኤር 20፡7-18) የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በዚህ ሁኔታ የእኛ ቃል ለእግዚአብሔር የእግዚአብሔር ቃል ይሆናል፡፡ ይህም የሚያረጋግጠው የክርስቲያን ግልጠት ውይይታዊ ባህርይ እንዳለው ይገልጻል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያ መልዕክቱ ኃጢአትን ከማድረግ መጠበቅ እንዳለብን እና በደህንነታችን እንደ አዲስ እንደተወለደ ህፃን ንጹሐን እንደንሆን ይመክረናል። እግዚአብሔር ሁልጊዜ ልባችንን ይመረምራል ኃጢአታችንና መተላለፋችንን ይመለከታል ይህንንም በመዝሙረ ዳዊት 90፡8 “ኃጢአታችንን በፊትህ ታኖራለህ፣ የተሰወረውንም በደላችንን ለአንተ በሚታይ ቦታ ታስቀምጣለህ” በማለት ይገልጸዋል። ይህም በእግዚአብሔር ፊት ሁሉም ነገራችን ግልጽ እንደሆነ የምንገነዘበት ከመጸሐፍ ቅዱስ  አንዱ ክፍል ነው።

ኃጢአት የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ይቃወማል የሰው ልጅ የገዛ ነጻነቱ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ካለንና እኛም ለእርሱ ከተፈጠርንለት ከኪዳናዊ ውይይት በተቻለ መጠን በአሳዛኝ ሁኔታ ወደ ኋላ እንደሚያፈገፍገው የእግዚአብሔር ቃል በማያጠራጥር ሁኔታ ይገልጻል፡፡ ኃጢአት በሰው ልጅ ልብ ውስጥ አድፍጦ እንደሚቀመጥም መለኮታዊ ቃል ይገልጻል፡፡ ኃጢአት የእግዚአብሔርን ቃል እንዳንሰማ የሚቃወም ነገር እንደሆነና፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያቀራርበንና ከእርሱ ጋር ኅብረት እንዲኖረን ከሚጠራን እግዚአብሔር ጋር ያለን ኪዳን የሚሰብር መሆኑን ሁለቱም የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት በብዛት ይዘረዝራሉ፡፡

ስለዚህም ዛሬ ላይ የእያንዳንዳችን ሕይወት በእርሱ ፊት ምን ትመስላለች ብለን የምንጠይቅበት አጋጣሚ በቃሉ አማካይነት በመፈጠሩ፤ በአኗኗራችን ሁሉ የእርሱ ክብር የሚገለጽበት ይሆን ዘንድ ዘወትር በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንድንተጋ በቃሉም እንድንኖር ይመክረናል።   

የዛሬው የወንጌል ክፍል ሕጻኑ ኢየሱስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ከወላጆቹ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለፋሲካ በዓል እንደሔደ እና ከበዓሉም በኋላ እሱ በቤተ መቅደስ እንደቀረ፣ ወላጆቹም ከሦሰት ቀናት ፍለጋ በኋላ እንዳገኙት የሚተርክ ነው። ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ማርያም ይህ የእግአብሔር አደራ አለባቸውና እንደገና ወደኋላ ተመልሰው መፈለግና ማገኘት ግድ ሆኖባቸው ነበር፡፡

እኛም የአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር አደራ አለብን፤ ልጁን ልኮልናል፣ብዙ በረከትን በእቅፋችን ውስጥ አስቀምጧል፣ጸጋን ሰጥቶናል፤ ይህን ክቡር የሆነውን የአምላክ ስጦታ እንዴት ነው የያዝነው? ኢየሱስ ከሕይወታችን የራቀ ሲመስለንስ እንዴት ነው ወደ ፍለጋ የምንወጣው? የት ነው ኢየሱስን የምንፈልገው?

ለኢየሱስ ያለን ፍቅር እሱን ለመፈለግ በምናደርገው ጥረት እና በምንደክመው ድካም ይለካል፡፡ ከሁሉ በማስቀደም ኢየሱስን ለመፈለግ ስንነሣ ራሳችንን ማዘጋጀት ይገባናል ምክንያቱም ይህ ጉዞ ተጀምሮ ግማሽ መንገድ ላይ የሚተው አይደለም፡፡ ከኢየሱስ ወላጆች ይህን ጽናት ነው እንደ አብነት መውሰድ የሚገባን፡፡ እነሱ እንደሚያገኙት አምነው ነው የወጡት፡፡ በመጨረሻም የፈለጉትን አገኙ፡፡ እግዚአብሔር በቅን ልብ ለሚፈልጉት ጊዜውን ጠብቆ ይገለጣል፣በልባቸውም በመገኘት ደስ ያሰኛቸዋል፤ይህን አምላክ በተረጋጋ ልብ እና መንፈስ መፈለግ፣ፍለጋውም በእምነት እና በተስፋ የታገዝ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በትንሹም በትልቁም ማጉረምረም እና ማማረር ሳይሆን እንደነዚህ ሁለት ቅዱሳኖች በትዕግስት በመጽናት መጓዝ ነው፣ክርስቶስን የራስ እስከ ማድረግ ድረስ መትጋት፣ለጸሎት እና ከእግዚአብሔር ጋር ለሚያገናኙን መንፈሳዊ ሰዓታትና መንፈሳዊ ተግባራት ታማኝ መሆን፡፡

ቀላልና የተመቻቸ ሕይወት የለመደች ነፍስ ግን በመንፈስ እንቅልፋም ትሆናለች፤ ድካምን፣ተጋድሎን፣ መስዋዕትነትን የምትጠላ፣መስቀልንም የምትጸየፍ ከሆነ  ወይም ከላይ እንደተጠቀሰው ማጉረምረም ብቻ የሚቀናት ነፍስ ኢየሱስን ማግኘት አትችልም፣የክርስትናው መንገድ ይከብዳታል፡፡

አምላካችን ግን ራሱንም ሆነ በእኛ ላይ ያለውን ዕቅድ፣ፍቃዱንም የሚገልጽልን ተግዳሮቶችን በትዕግስት መቀበልና ማስተናገድ ስንችል ነው፤ እሳት ሸክላን እንደሚያጠነክር ፈተናም ነፍስን፣እምነትንና ክርስትናን ያጠነክራል፤ በዚህ በእምነት ጉዞ፣በየዕለቱ ክርስቶስን የበለጠ ለማግኘትና የራሳችን ለማደረግ በምንደክመው ድካም ፈተና እንዳይገጥመን የምንሻና የምንመኝ ከሆነ መንገድም ምርጫም ተሳስተናል፤ ይህን ስላወቁ ነው ዮሴፍና ማርያም እነዚያን ፈታኝ ቀናት በትዕግስትና በእምነት የኖሯቸው፤በዚህ በፈተና መንገድ በመራመዳቸው የበለጠ በእምነት ጠንካሮች ሆኑ፡፡ ስለዚህ ማንም ሳይፈተን አይቀርም፤ እንኳን እኛ ክርስቶስ ራሱ መስቀልና ፈተና በበዛበት መንገድ ነው የተጓዘው፤ «ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ» እስከማለት ደረሶ ነበር፤ ጌታችን ግን እዚያ ላይ አላቆመም፣ጉዞውን አላቋረጠም  “ያንተ ፍቃድ ይሁን” ብሎ እስከ መጨረሻው የመስቀል መስዋዕትነት ራሱን አቅርቧል፡፡ ምክንያቱም የመጣው በአባቱ ቤት ለመገኘትና የአባቱን ፍቃድ ለመፈጸም ነው፡፡

ስለዚህ ኢየሱስን ስንፈልግ እንደ ዮሴፍና ማርያም እምነትንና ትዕግስትን ስንቅ አድርገን ነው፡፡ ተራ እና ቀላል መንገድንማ እምነት የሌላቸውም ሰዎች ሊጓዙት ይችላሉ፤ እንዲህ ዓይነቱን  ሕይወት መኖር ለማን ያዳግተዋለ? ይህ ተራና ቀላል መንገድ ግን ክርስትናውን አያጣፍጠውም፡፡ እነዚህ የኢየሱስ ወላጆች ባለፉበት መንገድ ማለፍና ወደ ቅድስና ለመድረስ ግን አድካሚውንና ተራራማውን መንገድ በትዕግስት፣በእምነትና በተስፋ መጓዝ የግድ ነው - ክርስቶስን ለማግኘትና ከእርሱ ጋር ለመወገን፤ ከኢየሱስ መልስም የምንማረው ትልቅ ትምሕርት አለ፡፡

እርሱ ከወላጆቹ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አታወቁምን?” ነበር ያላቸው ከአባቱ የተቀበለውን ተልዕኮ ሲያመለክት፤ በወንጌልም “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ፈልጉ” ነውና የተባለው (ማቴ 6፡33)፡፡ በእንዲህ ያለ መንፈስ፣በየዋህ ልብና በክርስቲያናዊ ፍቅር የሚመላለስ አማኝ እንደ ብላቴናው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት በጥበብና በጸጋ እንዲሁም በሞገስ ያድጋል፣ ጣፋጭ የሆነ የክርስትና ሕይወትን መኖር ይችላል፣ ከእግዚአብሔርም ጋር በቅርብ ይተዋወቃል፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእከቱ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል የሚለን” (ያዕ 4፡8)።

ስለዚህ ታዲያ፡ የእኛ አጠቃላይ የመኖር ምስጢሩ ከሚናገረን፤ ከሚሰማንና ለሕይወታች አቅጣጫ ሊሰጠን ከሚጠራን እግዚአብሔር ጋር በውይይት መቆራኘት ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ የእኛ ሕይወት በሙሉ መለኮታዊ ጥሪ ሥር እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃል ይገልጻል።

ስለሆነም ይህንን ለማድረግ እና በክርስትና እምነታችን ጠንካሮች ሆነን ለመጓዝ እንድንችል ዘወትር የሁላችን እናትና አጋዥችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋንና በረከትን ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ታማልደን።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

06 February 2021, 11:54