የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ፣ ክቡር አባ ማኑኤል ፕሬቶ ገልጸዋል የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ፣ ክቡር አባ ማኑኤል ፕሬቶ ገልጸዋል 

አባ ማኑኤል፣ በአውሮፓ ውስጥ የስደተኞችን ችግር እና አያያዝ በማስመልከት ማብራሪያ ሰጡ

የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ በክልሉ የሚገኙ ስደተኞች ያሉበትን ሁኔታ እና ስደተኞችን ተቀብለው ማስተናገድ ያለባቸውን አገሮች በማስመልከት ውይይት ካደረገ በኋላ ለአውሮፓ ኅብረት አገሮች ምክር ቤት ጠቃሚ ሃሳቦችን ማካፈሉን የጳጳሳቱ ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አባ ማኑኤል ፕሬቶ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለስደት የሚዳረግ ሰው ከተወለደበት አካባቢ ከመፈናቀል አልፎ ተርፎም ከባሕሉ እና ከሃይማኖቱ ተለይቶ በእንግድነት በሌላ አገር ይኖራል። የሚሰደዱ ሰዎች ብዙን ጊዜ ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ በመሆናቸው በደረሱበት አካባቢ አድልዎ ፣ አለመቻቻል ፣ ኢ-ሰብአዊ እና አዋራጅ የኑሮ ዓይነት ሊያጋጥማቸው ይችላል። በተመሳሳይ መልኩ ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር ለመቀላቀል በሚያደርጉት ጥረት መካከል ትኩረት የማይሰጣቸው ቢሆንም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በጽናት እና በቆራጥነት የሚያሸንፉበትን እና የሚቋቋሙበትን መንገዶች ሊያገኙ ይችላሉ። እነዚህ እና ሌሎች ችግሮች መኖራቸውን በመገንዘብ የአውሮፓ ኅብረት ስደተኞችን ተቀብሎ ለኑሮ ምቹ የሆኑ ዕድሎችን ለማመቻቸት፣ የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከአውሮፓው ቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር ጋር በመተባበር፣ “ሰብዓዊ ክብር፣ ስደተኞች እና የስደተኛ አስተናጋጅ ማህበረሰቦች” በሚል ርዕስ አንድ አውታረ-መረብ ላይ አውደ-ጥናት አዘጋጅቷል። የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ የስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ድምጽ እንዲሁም የሚያጋጥማሟቸውን ችግር እና ያገኙትን የችግር ማቃለያ መንገዶችን ለአስተናጋጅ አገር ለማሰማት እና ለማሳወቅ በመሆኑ፣ የአውደ-ጥናቱ መሪ እና የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አባ ማኑኤል ባሪዮስ ፕሬቶ እንዲህ በማለት ያስረዳሉ፥

በአውታረ-መረብ በኩል በተካሄደው አውደ-ጥናት አማካይነት የስደተኞችን ምስክርነት፣ ልምድ እና ወደ አውሮፓ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጋጠሟቸውን ችግሮች እና ወደ አውሮፓ ከደረሱ በኋላም በሚስተናገዱባቸው አገሮች ውስጥ ያጋጠማቸውን እንቅፋቶችን እንዲያስተነትኑ ለማገዝ የተዘጋጀ አውደ-ጥናት መሆኑን አባ ማኑኤል አስታውቀዋል። የስደተኞችን የሕይወት ልምድን እና ምስክርነት ከመስማት ባሻገር በአውሮፓ ኅብረት አገሮች የሚገኙ የፖለቲካ አመራር አባላትም ለርካታ ሰዎች መሰደድ ዋና ምክንያት ምን እንደሆነ የደረሱበት የውይይት ውጤት እና የመፍትሄ ሃሳቦች ካላቸው ለማወቅ መሆኑን አባ ማኑኤል በማከል አስረድተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እንደ ቤተክርስቲያን የስደተኞችን ሕይወት ለመቀየር፣ በመልካም አቀባበል ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆኗን ገልጸው፣ ስደተኞች ይህ ከተመቻቸላቸው ለሚኖሩበት የአውሮፓ አገሮች ውድ ሃብት እንጂ ሸክም አይሆኑም በማለት አስረድተዋል። አባ ማኑኤል ጨምረውም ወደ አውሮፓ የሚመጡት ስደተኞች የሥራ ዕድልን ይሻማሉ፣ የችግር ምክንያት ይሆናሉ፣ ወንጀል እንዲበራከት አስተዋጽዖን ያደርጋሉ የሚሉት አስተሳሰቦች ከአውሮፓዊያኑ አዕምሮ መወገድ እንዳለበት አሳስበዋል። አውሮፓ የራሷ ችግሮች አሉባት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ታክሎባታል ያሉት አባ ማኑኤል፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እንድተናገሩት ሁሉ ስደተኞችን መቀበል ብቻ ሳይሆን ማስተናገድንም ማወቅ ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰው፣ ቤተክርስቲያን በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙትን በርካታ ችግሮች በመገንዘብ በችግር ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ከችግራቸው ለማውጣት ድምጿን ከፍ አድርጋ ማሰማት እንዳለባት እና ሌሎች ማኅበራዊ ተቋማትም በበኩላቸው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከሌሎች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ጋር በመተባበር፣ በዘርፉ በቂ ዕውቀት ያላቸውን ባለሞያዎችን በማሳተፍ፣ አንዳንድ ጥርጣሬዎች ቢኖሩም እንኳ መልካም ውጤቶችን በማየት ላይ መሆናቸውን ክቡር አባ ማኑኤል አስረድተዋል።

አንድነትን መግለጽ እና ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ አቅም እና ገንዘብ ሲኖር ብቻ ሳይሆን በችግር ወቅት እና ሁል ጊዜ በተግባር መገለጽ እንዳለበት አባ ማኑኤል አስረድተው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአውሮፓ ውስጥ የተቸገረን መርዳት፣ ስደተኛን በክብር ተቀብሎ ማስተናገድ እና ሰብዓዊ ክብሩን መጠበቅ፣ በችግር ወቅት እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስጨነቀ ባለበት ባሁኑ ጊዜም ቢሆን በተግባር መታየት አለበት በማለት ያስተላለፉትን መልዕክት አባ ማኑኤል አስታውሰዋል። ወደ አውሮፓ የሚመጡት ስደተኞች የባልካን አገራትን ጨምሮ ከሌሎችም በርካታ አገሮች መሆኑን የገለጹት አባ ማኑኤል፣ ስደተኞቹ በተለይም ከአፍጋኒስታን፣ ፓክስታን፣ ባንግላዲሽ እና ከአፍሪካ መሆኑን አስታውሰዋል። ወደ አውሮፓ ከሚያቀኑት ስደተኞች ብዙዎቹ በቦስኒያ እና በክሮዋሺያ ድንበሮች ተደናቅፈው እንደሚቀሩ አስታውሰው፣ ከባድ የብርድ ወራት በጀመረበት ወቅትም ብዙ ስደተኞች ለብርድ መጋለጣቸውን ገልጸው፣ አውሮፓ እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ የበለጠን ለማድረግ ጥሪ ያለበት መሆኑን አስረድተዋል።

በአውሮፓ ኅብረት አገሮች ውስጥ የምትገኝ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤዎች ጋር በመተባበር፣ በብራሴልስ ከተማ ከሚገኝ የአውሮፓ ኅብረት አገሮች አምባሳደር ጋር በመመካከር የሚጠበቅባቸውን እገዛ ለማድረግ፣ በበኩላቸው የሚያዩትን አንዳንድ የአውሮፓ ውስጥ እውነታቸውን እና ክርስቲያናዊ አመለካከቶችን ለመጋራት ዝግጁ መሆናቸውን አባ ማኑኤል ገልጸዋል። የአውሮፓ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር የኮሮና ወረርሽኝ በአውሮፓ ያስከተለውን ቀውስ የተመለከተ እና የመፍትሄ ሃሳብን የያዘ ሰነድ ለአውሮፓ ኅብረት አገሮች አምባሳደር ማቅረባቸውን አስታውሰዋል። የስደተኞችን ሁኔታ አስመልክቶ የወቅቱ ፕሬዝደንት አገር ፖርቹጋል በግንባር ቀደምትነት የምታቀርበውን የአውሮፓ ኮሚሽን መመሪያ ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤያቸው ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።                   

የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ፣ ክቡር አባ ማኑኤል ፕሬቶ በመጨረሻም፣ እንደ ቤተክርስቲያን ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና ምን ለማድረግ እንደሚያስቡ በግልጽ ያስቀመጡ መሆኑን ገልጸው፣ በስደተኞች ጉዳይ ላይ የዳብሊን ጉባኤ ያስተላለፈውን ስምምነት ተግባራው ለማድረግ፣ በአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች ቢኖሩም በድጋሚ በመመልከት፣ በተለይም ለስደተኞች በሚደረግ የመጀመሪያ መስተንግዶ ላይ፣ ከሌላ አገር ወደ አውሮፓ የመጣ አንድ ሰው ስደተኛ፣ ተፈናቃይ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ መሆኑን ማረጋገጥ የሚሉት ጉዳዮች ለአውሮፓ ቤተክርስቲያን መሠረታዊ እና አስፈላጊ በመሆኑ ጉባኤያቸው በሚገባ አስቀድሞ የተመለከተው መሆኑን ገልጸዋል። 

18 February 2021, 13:11