ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ በወሰዱት ወቅት ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ በወሰዱት ወቅት  

የየካቲት 14/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘጥምቀት - አስተርእዮ 5ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ

እራሳችንን ለእግዚአብሔር መስጠት

የዕለቱ ንባባት

1.    1ኛ ጢሞ 5፡5-10

2.   ያዕ 5፡13-20

3.   ሐዋ.ሥ 3፡ 17-26

4.   ሉቃ 2፡22-34

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በሙሴ ሕግ መሠረት፣ የመንጻታቸው ወቅት በተፈፀመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ፤ ይኸውም በጌታ ሕግ፣ “ተባዕት የሆነ በኵር ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ለመፈጸምና ደግሞም በጌታ ሕግ፣ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፣” መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር።

በዚያን ጊዜ ጻድቅና ትጒሕ የሆነ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው በኢየሩሳሌም ይኖር ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን መጽናናት የሚጠባበቅና መንፈስ ቅዱስ በላዩ ያደረሰው ነበር። ደግሞም የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር፤ እርሱም በዚህ ጊዜ በመንፈስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ የልጁም ወላጆች በሕጉ ልማድ መሠረት ተገቢውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ኢየሱስን ይዘው በገቡ ጊዜ፣ ስምዖን ተቀብሎ ዐቀፈው፤ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲህ አለ፤

“ጌታ ሆይ፤ ቃል በገባኸው መሠረት፣ አሁን ባሪያህን በሰላም አሰናብተው፤ ዐይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን፣

ማዳንህን አይተዋልና። ይህም ለአሕዛብ መገለጥን የሚሰጥ ብርሃን፣ ለሕዝብህ ለእስራኤልም ክብር ነው።” አባቱና እናቱም ስለ እርሱ በተነገረው ነገር ተገረሙ። ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፤ “ይህ ሕፃን በእስራኤል ለብዙዎች መነሣትና መውደቅ ምክንያት እንዲሆን፣ ደግሞም ክፉ ለሚያስወሩበት ምልክት እንዲሆን ተወስኖአል።

የእለቱ አስተንትኖ

 

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

በቅድድሚያ ከአባታችን ከእግዚአብሔር ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋና ምሕረት ሰላምም ከሁላችሁጋር ይሁን።

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር  ዘጥምቀት - አስተርእዮ 5ኛ ሰንበትን እናከብራለን ፡፡

በዛሬው ዕለተሰንበት በተነበቡት መልዕክቶችና ወንጌል አማክይነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሳችንን ለእግዚአብሔር ስለመስጠት እንድናስተነትን ይጋብዘናል። አሁን ያለንበት ዘመን በይበልጥ ወደ እግዚአብሔር አምላካችን እንድንቀርብ እና ወደ እርሱ እንድንጠጋ የምንገደድበት ወቅት ነው። በየዕለቱ እንደምናየው እና እንደ ምንሰማው በዓለማችን ውስጥ ጦርነት፣ ስደት፣ እረሃብ፣ በሽታ እና ብዙ አስከፊ ነገሮች ማየት የየዕለት ሕይወታችን ሆኗል፤ በመሆኑም ከመቼውም ጊዜ በላይ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አዋቂዎች እንዲሁም በተለያየ የእድሜም ሆነ የሕይወት ክፍል ውስጥ ያለን ሁሉ እራሳችንን ለእግዚአብሔር የተለየን እና የተሰጠን እንድንሆን ይመክረናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ እንዲህ ይለዋል፤ “በእርግጥ መበለት የሆነችና ብቻዋን የምትኖር ተስፋዋን በእግዚአብሔር አድርጋ ሌሊት እና ቀን የእግዚአብሔርን እርዳታ በመለመን በጸሎት ትኖራለች።” 1ጢሞ 5፡5 በየትኛውም የሕይወት ዘይቤ ውስጥ ብንገኝ እራሳችንን ለእግዚአብሔር ቅርብ ማድረግ ይገባናል፤ ምክንያቱም ሕይወታችን ለእርሱ የተሰጠ ከሆነ የሁሉ ነገር ባለቤት እርሱ ከስጦታ በላይ የሆነውን ስጦታ ይሰጠናል።

በዘመናችን በተለየ ሁኔታ የሚታየውን የተለያዩ ጥይቄዎችን ለመመለስ በሚደረግ ውጣ ውረድ ውስጥ ለብቻችን  በተናጥል የምናደርገው ጉዞአችን ከመድከም ባለፈ ውጤት አልባ በመሆኑ ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ተስፋችን መና ሆኖ የቀረ የሚመስለን እራሳችንን ለእግዚአብሔር በመስጠት እና በማመስገን ሕይወት ውስጥ ስለማናገኘው ነው። ይህንንም ቅዱስ ያዕቆብ በመለክቱ እንዲህ ይለናል “ከእናንተ መካከል ችግር የደረሰበት ሰው ቢኖር ይጸልይ ደስያለውም ሰውም ቢኖር እግዚአብሔርን በማመስገን ይዘምር” ያዕ 5፡13

ለእግዚአብሔር የተሰጠ ሕይወት ሲኖረን ማንኛውንም አይነት ፈተና እና የሕይወታችንን ተግዳሮቶች በቅድሚያ ለእርሱ እናቅርብለታለን እግዚአብሔርም ለእኛ እንደ ተራራ ከብዶ የሚታየንን ችግር ያቃልልናል፤ በእዚህም ማንኛውም አይነት ፈተናዎች ሊያሸንፉን አይችሉም፤ ምክንያቱም ከእኛጋር ያለው ከዓለም ካለው ይልቅ ስለማይበልጥ ነው። ዘማሪው ዳዊት ሕይወቱ ለግዚአብሔር የሰጠ ስለሆነ በእርሱ ተማምኖ ስለሚኖር እንዲህ ብሎ ዘመረ፡ “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው በለመለመ መስክ አንዳችም አይጎድልብኝም” መዝ 23፡1  ለእግዚአብሔር የተሰጠ ህይወት ካለን ምንም የሚያሳነን ነገር የለም ሁሉም የሚሆነውና ይሚከናወነው በእርሱ ነውና።

እራሳችን የምንሰጠው ወደ ምሕረቱ ዙፋን በእምነት በመቅረብ በንስሃ በመንጻት ነው። ሰው እንደመሆናችን መጠን በየጊዜው ኃጢአትን እንሠራለን ሆኖም በኃጢአት ስንወድቅ መደናገጥ እና ከፊቱ ለመሸሽ መሞከር የለብንም። ቀና ብለን መሄድ የምንችለው ከኃጢአታችን በላይ እኛን እንደሚወደን በመተማመን የማይወድልንን ኃጢአታችንን ከእግሩ ስር ስናራግፈው የዛኔ ከእርሱ ጋር የሚኖረን ግንኙነት በይበልጥ ይጠነክራል።

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል መልዕክትም ይህንን ሃሳብ የሚያጠናክርልን ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና በተወለደ በስምንተኛው ቀን እናቱ ማርያም እና አባቱ ዮሴፍ ህፃኑን ለእግዚአብሔር ሊሰጡት ወደ ቤተመቅደስ ወሰዱት፤ ይህም መሰጠት ሁለት መልዕክት ይሰጠናል፤ የመጀመሪያው በሙሴ ህግ መሠረት ወንድ የሆነ በኩር ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር ተሰጥቶ የተቀደሰ ይሆናል የሚል ትዕዛዝ ያለ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአባቱን ተልዕኮ ለመፈፀም ለዓለም ሁሉ የተሰጠ መሆኑን ለማሳየት ነው።

ይህንን የተስፋ ቃል ለማየት ዘመኑን ሙሉ በመጠባበቅ ላይ የነበረው የእግዚአብሔር አገልጋይ ስምኦን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተመቅደስ ሲሰጥ ሲያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ በራዕይ ገልጦለት ነበረና ይህንን የተስፋ ቃል ሲፈፀም በቤተመቅደስ ቆሞ በዐይኖቹ አየ “በዚያን ጊዜ ሕፃኑን አቅፎ እግዚአብሔርን በማመስግን እንዲህ አለ፤ ጌታ ሆይ እነሆ የሰጠኸኝ የተስፋ ቃል ተፈፀመ እንግዲህ አሁን እኔን አገልጋይህን በሰላም አሰናብተኝ፤ ምክንያቱም ማዳንህን በአይኔ አይቻለሁ፤ እርሱም በሕዝቦች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው። እርሱ ለአረማውያን እውነትን ይሚገልጥ ብርሃን ይሆናል፤ ለሕዝብህም እስራኤል ክብር ነው።” ሉቃ 2፡29-32

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ አምላክ ሆኖ ሳለ እራሱን ለአባቱ ሰጠ፣ አቀረበም ይህም የሆነው እርሱ ለእኛ የተሰጠ የመዳኛችን መንገድ ስለሆነ እና የአባቱን ትእዛዝ ለመፈፀም ብቻ ወደ እዚህ ዓለም መምጣቱን ለማመልከት ነው።

በምድር ላይ በኖረባቸው ዓመታት እራሱን ለአባቱ ተልዕኮ አስገዝቶ በዲያቢሎስም ሲፈተን በእግዚአብሔር ቃል በማሸነፍ እስከመጨረሻ ሕይወቱን ለአባቱ ተልዕኮ የተሰጠ አደረገ።

እኛም ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የምንማረው ይህንን ነው ይህም የህይወታችን ባለቤት እና መሣርያችን እግዚአብሔር ስለሆነ ማንነታችንን ለእርሱ ብቻ በማስገዛት እንስጠው። በዓለም ሳለን በፈተና እንፈተናለን እንወድቃለንም ሆኖም ከውድቀታችን ተነስተን እንድንራመድ እራሳችንን ለእርሱ እንስጠው።

ይህንንም ለማድረግ እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ፀጋና በረከት ታማልደን የሰማነውን በልባችን ያሳድርልን።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

 

20 February 2021, 09:16