በማሌዥያ የሚገኝ አንድ ካቶሊካዊ ቁምስና በዓለማችን ቀዳሚ “አረንጓዴ” ቁምስና ተባለ

የጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ. ም. የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተባለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመላው ዓለም በልዩ ትኩረት የሚታይበት ዓመት እንዲሆን መታወጁ ይታወሳል። በዚህ መሠረት በማሌዥያ የሚገኝ አንድ ካቶሊካዊ ቁምስና፣ በአገሪቱ ውስጥ ሆነ በመላው ዓለም ቀዳሚ አረንጓዴ ቁምስና ተብሎ መመረጡ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማሌዥያ የሚገኝ የመለኮታዊው ምህረት ቁምስና፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚል አርዕስት ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን በልዩ ስሜት ማክበሯ ታውቋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ ከመሆኑ ከሁለት ዓመታት አስቀድሞ በማሌዥያ የሚገኝ የመለኮታዊው ምህረት ቁምስና ምዕመናን ለአምላካቸው ያለውን ከፍተኛ ፍቅር በፍጥረታቱ በኩል መግለጻቸው ታውቋል።

የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚበዙባት ማሌዥያ፣ የቅዱስ ፍራንችስኮስ መንፈስ እንዲሰርጽ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት የቁምስናው መሪ ካህን ክቡር አባ ማርቲን፣ ቁምስናቸው በአረንጓዴ ተክል እንዲያጌጥ መፈለጋቸውን ገልጸዋል። ክቡር አባ ማርቲን የቁምስናቸው የመጀመሪያ መሪ ካህን ሆነው ለሰባት ዓመታት ማገልገላቸው ታውቋል። በቁምስናው ምክር ቤት ውስጥ ለፍጥረት የሚሰጥ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ማዳሌና በቁምስናው ውስጥ አረንጓዴ ተክሎችን እየተንከባከቡ መሪ ካህኑን የሚያግዙ መሆኑ ታውቋል።

የፍጥረታት ወዳጆች
የፍጥረታት ወዳጆች

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚል አርዕስ የሚታወቀው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ ለፍጥረታት ሊደረግ ከሚገባው እንክብካቤ እና ጥበቃ በተጨማሪ ስለ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምሮ፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ ሰው ልጅ ብልጽግና፣ ስለ ሰላም እና ስለ ሰብዓዊ መብት ጭምር በመተንተን ጠቃሚ መልዕክቶችን የሚያስተላልፍ መሆኑ ይታወቃል። እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች በሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ በዘላቂነት የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ በመጠቀም፣ አስፈላጊ ያልሆኑ ፍጆታዎችን በመቀነስ ለፍጥረታት ተገቢውን ክብር መስጠትን ያካትታል። በማሌዥያ የሚገኝ የመለኮታዊው ምህረት ቁምስና ተልዕኮ ሌላ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፍቅር በመገንዘብ በተለያዩ አደጋዎች ምክንያት ጉስቁልና የደረሰበት ዓለማችንን ከጉዳት ለማዳን የሚያግዙ የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮን በተግባር መተርጎም ነው። የመለኮታዊው ምህረት ቁምስና መሪ ካህን፣ ክቡር አባ ማርቲን፣ ረዳታቸው ከሆኑት ከወ/ሮ ማዳሌና ጋር በመተጋገዝ በአካባቢው ነዋሪዎች መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው እና ምቹ እና ተስማሚ የመኖሪያ ሥፍራ እንዲኖራቸው ለማድረግ ተስፋን የሚሰጡ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

ከምዕመናኑ ውስጥ አብዛኞቹ በቁምስናቸው ዙሪያ እንደሚኖሩ የገለጹት ወ/ሮ ማዳሌና፣ እነዚህ ምዕመናን ጊዜያቸውን ለአትክልት ሥራ ለማዋል እንደሚቸገሩ ገልጸው፣ ቢሆንም የምግብ ትራፊን በማይገባ ቦታ ከመጣል ይልቅ ለማዳበሪያነት እንዲጠቀሙ የሚያበረታቱ መሆኑን አስረድተዋል።

በአረንጓዴ ተክል የተዋበ ቁምስና
በአረንጓዴ ተክል የተዋበ ቁምስና

ያላቸውን በመጠቀም አካባቢን ማልማት

ትንሽ መሬት እንዳላቸው የገለጹት ክቡር አባ ማርቲን እና ረዳታቸው ወ/ሮ ማዳሌና፣ የቁምስናው ምዕመናን ላሳዩት ብርታት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ምዕመናኑ ለመሬት አጠቃቀም ሳይንሳዊ የመስኖ ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ፣ የዝናብ ውሃን በመጠቅም ተክሎችን ማሳደግ መቻላቸውን አስረድተዋል።

ጥራጊን በመሰብሰብ ማዳበሪያን ማዘጋጀት
ጥራጊን በመሰብሰብ ማዳበሪያን ማዘጋጀት

ቆሻሻ የተባሉ ቁሳቁሶች ሃብት ናቸው

አባ ማርቲን እና ረዳታቸው ወ/ሮ ማዳሌና የአካባቢው ነዋሪዎች ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉ ለመርዳት ባወጡት እቅዳቸው፣ የማይጠቅም ቆሻሻ ተብሎ የሚጣሉ የቤት ውስጥ ጥራጊዎች ለሕይወት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ለቁምስናው ምዕመናን በየጊዜው ያስረዳሉ። በዚህ መሠረት ከሚጣሉ ነገሮች ጀምረው አካባቢያቸውን ለመቀየር እና የኤኮኖሚ ገቢያቸውን ማሳደግ መቻላቸው አስታውቀዋል። ሰዎች የቤት ውስጥ ጥራጊን መሰብሰብ እስከቻሉ ድረስ እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል መቸገራቸው አይቀርም። ነገር ግን በማሌዥያ ለሚገኝ የመለኮታዊ ምህረት ቁምስና ምዕመናን፣ የሚጣል ቆሻሻ እና የቤት ውስጥ ጥራጊ ውድ ሀብታቸው ሆነዋል።

ሐይማኖታዊ ተግባራት

በማሌዥያ የሚገኝ የመለኮታዊ ምህረት ቁምስና የተለያዩ ጥናታዊ ሥራዎች የሚከናወንበት ቦታ ብቻ አይደለም። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእስልምና እምነት ተከታይ ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ ጥቂት የክርስቲያን ማኅበረሰብ የሚገኝበት ቁምስና ነው። ይህ ደግሞ ብዙ ነገርን የሚያካትት ሲሆን ከእነዚህ መካከል፣ ዕለታዊ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የሚካሄድበት፣ የጋራ ጸሎት የሚቀርብበት እና ምዕመናን አብረው የሚኖሩበት ነው። ስለሆነም ፕሮጀክቱ የበጎ አድራጎት ወይም ማኅበራዊ ድጋፍን ለመስጠት ብቻ የተወጠነ ሳይሆን፣ ሐይማኖታዊ ተግባራት የሚፈጸምበት፣ አንድ የእህል ዘር እንኳን መለኮታዊ ጸጋ መሆኑን በመረዳት ምስጋና የሚሰጥበት ነው።

በቁምስና የሚደረጉ መንፈሳዊ ጉባኤዎች
በቁምስና የሚደረጉ መንፈሳዊ ጉባኤዎች

ከልጆች ጋር መማማር

ሌላው የቁምስናው ዓላማ ሕጻናት የጋራ መኖሪያ ለሆነች ምድራችን እንክብካቤን እና ጥበቃን እንዲያደርጉ ማስተማር ሲሆን በተጨማሪም ለሚያጋጥማቸው ችግሮች ትክክለኛ መፍትሄን እንዲያገኙ ማስተማር ነው። “ሕጻናትን ማስተማር ማለት እኛው ተመልሰን የምንማርበት ነው” በማለት ክቡር አባ ማርቲን ያስረዳሉ። “የጋራ ሕይወት በጨዋታ እና በትምህርት የተመሠረተ ነው” የሚሉት አባ ማርቲን፣ ሕጻናት የኑሮ ሥርዓትን ከወላጆቻቸው ማየት፣ መማር እና በተግባር መግለጽ እንዳለባቸው ይገልጻሉ።

ከሕጻናት ጋር ሆኖ መማማር
ከሕጻናት ጋር ሆኖ መማማር

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት

በማሌዥያ የሚገኝ የመለኮታዊው ምህረት ቁምስና መሪ ካህን አባ ማርቲን በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት ሁሉንም የቁምስናቸውን ምዕመናን በአካል ማግኘት ባይችሉም፣ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ባዘጋጁት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ፣ ስለ አየር ንብረት ለውጥ እና ስለ ተፈጥሮ ጥበቃ የሚያስረዱ የተለያዩ ቪዲዮዎችን በማካፈል ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። የቁምስናውን ልምላሜ የወደዱት በርካታ ምዕመናን በመኖራቸው፣ በቁምስናቸው ውስጥ በሚገኝ የአትክልት ሥፍራ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓትን እንደሚፈጽሙ አባ ማርቲን ገልጸዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ ከመሆኑ ሁለት ዓመታት አስቀድመው በየዕለቱ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ክቡር አባ ማርቲን ገልጸዋል።  

14 January 2021, 20:37