ቅዱስ ገብርኤል ማርያምን ስያበስራት፣ የኢየሱስ መወለድ አስቀድሞ ተነገረ ቅዱስ ገብርኤል ማርያምን ስያበስራት፣ የኢየሱስ መወለድ አስቀድሞ ተነገረ 

የታኅሳስ 25/2013 ዓ.ም 4ኛው የስብከተ ገና ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.      2ኛ ሳሙኤል 7፡1-5፣ 8-12፣14፣16

2.    መዝሙር 88

3.    ሮሜ 16፡25-27

4.    ሉቃስ 1፡26-38

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የኢየሱስ መወለድ አስቀድሞ ተነገረ

በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ከተማ ላከው፤ የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት።

ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደን ግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤ መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። 32እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።”

ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተ እርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።” ማርያምም፣ “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቶአት ሄደ።

የእለቱ አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

በዚህ በአራተኛው እና በመጨረሻው የስብከተ ገና ሳምንት ሰንበት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል የኢየሱስ መወለድ አስቀድሞ የተነገረበትን ሁኔታ እንደገና ያስታውሰናል። መልአኩ ማርያምን “ደስ ይበልሽ” ካላት በኋላ “እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ”  (ሉቃ 1፡28, 31) በማለት ያናገራታል። ድንግል ማርያም ደስ እንዲላት የታሰበ የንጹህ ደስታ ብስራት ይመስላል። በዚያን ጊዜ ከነበሩት ሴቶች መካከል የመሲሑ እናት የመሆን ሕልም ያልነበራት የትኛው ሴት ናት? ነገር ግን እነዚህ ቃላት ከደስታ ጋር ማርያም ታላቅ ፈተና እንደ ሚገጥማት ይተነብያሉ። እንዴት? ምክንያቱም በዚያ ቅጽበት እሷ “ታጭታ ነበር” (ሉቃስ 1፡ 27)፣ አላገባችም ነበር፣ ነገር ግን ለዮሴፍ ታጨችታ ነበር። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የታጨ ሰዎች የሙሴ ሕግ እንደ ሚለው በዝምድና መልክ ወይም አብሮ መኖር እንደሌለበት ደንግጓል። ስለሆነም ወንድ ልጅ በመውለዷ ማርያም ህጉን ትተላለፍ ነበር፣ እናም በሴቶች ላይ የሚደርሰው ቅጣት አሰቃቂ ነበር (ዘዳግም 22፡20-21)። በእርግጠኝነት መለኮታዊው መልእክት የማርያምን ልብ በብርሃን እና በብርታት ይሞላት ነበር። ሆኖም እራሷን ወሳኝ የሆነ ውሳኔ የማደረግ አጋጣሚ ገጥሟት ነበር - ለእግዚአብሔር “እነሆኝ” ለማለት ፣ ሁሉንም ነገር ፣ ሕይወቷን እንኳን አደጋ ላይ በመጣል ፣ ወይም ግብዣውን ላለመቀበል እና ተራ ህይወቷን ለመቀጠል በእነዚህ ጭንቀቶች ውስጥ ገብታ ነበር።

ታዲያ ምን አደረገች? እሷም “እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” (ሉቃ 1 38) በማለት ትመልሳለች። ነገር ግን ቅዱስ ወንጌል በተጻፈበት ቋንቋ በቀላሉ “ይሁን” ማለት አይደለም። አገላለፁ ጠንካራ ፍላጎትን ያሳያል ፣ የሆነ ነገር እንዲከሰት ፍላጎቱን ያሳያል። በሌላ አገላለጽ ማርያም “መከሰት ካለበት ይከሰት ... አለበለዚያ መሆን ካልቻለ ደግሞ…” በማለት አልመለሰችም። በምፍጹም እንዲህ አላለችም። እሷ ደካማ እና ታዛዥነትን ቀለል አድርጋ መቀበሏን አይገልጽም ፣ ይልቁንም ጠንካራ የሆነ ፍላጎት እንዳላት ትገልጻለች። እሷ አላቅማማችም፣ ነገር ግን በንቃት ትቀበላለች። እራሷን ከእግዚአብሄር ጋር ታስተሳስራላች። ጌታዋን ሙሉ በሙሉ እና ወዲያውኑ ለማገልገል ተዘጋጅታ በፍቅር ላይ ያለች ሴት ናት። እሷ ስለእሱ ለማሰብ ትንሽ ጊዜ ወይም ምናልባትም ስለሚሆነው ነገር ተጨማሪ ማብራሪያዎችን መጠየቅ ትችል ነበር። ምናልባት አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን ማዘጋጀት ትችል ነበር ... ይልቁኑ ጊዜ አልወሰደችም ፣ እግዚአብሔር እንዲጠብቅ አላደረግችውም፣ እንዲዘገይ አልፈለገችም ወዲያውኑ እሺ አለች።

ምን ያህል ጊዜ - አሁን ስለራሳችን እናስብ - ህይወታችን ስንት ጊዜ ነው ጊዜያትን በማራዘም በመንፈሳዊ ሕይወትም ጭምር ማለት ነው የተገነባው! ለምሳሌ መጸለይ ለኔ ጥሩ እንደሆነ አውቃለሁ፣ ነገር ግን ዛሬ “ነገ ፣ ከነገ ወዲያ” በማለቴት ዛሬ… ነገ ጊዜ የለኝም፣ ነገሮችን ለሌላ ጊዜ አስተላልፈናል-ነገ አደርገዋለሁ እያለን ራሳችንን የምናታልለው ስንት ጊዜ ነው? አንድን ሰው መርዳት አስፈላጊ እንደሆነ አውቃለሁ ፣ አዎ እኔ ማድረግ አለብኝ ነገ አደርገዋለሁ በማለት ጉዳዩን እናሸጋግረዋለን። ዛሬ የገናን በዓለ ለማክበር በምንዘጋጅበት ወቅት ማርያም ነገሮችን ለሌላ ጊዜ እንዳናስተላልፍ እና “እነሆኝ” እንድንል ተጋብዘናለች። “መጸለይ አለብኝ!” “አዎ ፣ እሻለሁ እናም እጸልያለሁ”። ሌሎችን መርዳት አለብኝ? አዎ"። እንዴት ላድርገው? አሁኑኑ ሳልዘገይ ማድረግ አለብኝ። እያንዳንዱ “እነሆኝ” አንድ ነገር ያስከፍላል ፣ እያንዳንዱ “እነሆኝ” የራሱ ዋጋ አለው ፣ ነገር ግን ሁልጊዜ ያ ደፋር እና ፈጣን “እነሆኝ” ከአስከፈላት ዋጋ ባሻገር “እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” በማለቷ ለእኛ መዳንን አስገኝቶልናል።

ታዲያ እኛ “እነሆኝ” የምንለው ምንድነው? በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት የበሽታው ወረርሽኝ ምንም ነገር እንዳናከናውን በሚያደርገን ወቅት ከማጉረምረም ይልቅ ለተቸገረ አንድ ሰው አንድ ነገር እናድርግ፣ ለራሳችን እና ለጓደኞቻችን እጥፍ ድርብ የሆነ ስጦታ ማደረግ ሳይሆን የተቸገረ አንድ ሰው እንርዳ። ሌላ አንድ ተጨማሪ ምክር ደግሞ ኢየሱስ በእኛ ውስጥ እንዲወለድ ፣ ልባችንን እናዘጋጅለት፣ ወደ ፀሎት እንሂድ ፣ እራሳችንን በሸማችነት መጠመድ አንፍቀድ። “አህ ስጦታዎችን መግዛት አለብኝ ፣ ይህንን እና ያንን ማድረግ አለብኝ” አንበል። ነገሮችን የማድረግ እና በብዛት የመሸመት እብደት የበለጠ እና የበለጠ ተጋላጭ እንድንሆን ያደርገናል። አስፈላጊ የሆነው ኢየሱስ ብቻ ነው። ሸማቾች በቤተልሔም በግርግም ውስጥ አይገኙም-እውነታው የሚያሳየን በእዚያ የሚገኙት ድሆች እና ፍቅር ብቻ ነው። እንደ ማሪያም እንዲሆን ልባችንን እናዘጋጅ ፣ ከክፉ ነገር ነፃ የወጣን እግዚአብሔርን ለመቀበል ዝግጁ የሆንን ሰዎች እንሁን።

“እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” የሚለው ቃል  ይህ የስብከተ ገና የመጨረሻ እሁድ (የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት ማለት ነው) የድንግል ማርያም የመጨረሻ ቃል ነው ፣ እናም ወደ ገና በዓል እውነተኛ እርምጃ ለመውሰድ የቀረበልን ግብዣ ነው። ምክንያቱም የኢየሱስ ልደት ሕይወታችንን የማይነካ ከሆነ - የእኔ ፣ ያንተ ፣ ያንቺ ፣  የእኛ ፣ የሁላችን - ሕይወታችንን የማይነካ ከሆነ በከንቱ ያልፋል ማለት ነው። አሁን በምንጸልየው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት እኛም “ቃልህ በእኔ ይፈጸም” በማለት እንጸልያለን፣ እራሳችንን ለገና በዓል በደንብ ለመዘጋጀት ወደነዚህ የመጨረሻ ቀናት በምንመጣበት አቀራረብ  እመቤታችን በሕይወታችን እንድንናገር እንድትረዳን አማለጅነቷን ልንማጸናት ይገባል።

ምንጭ፡ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በታኅሳስ 11/2013 ዓ.ም ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

አቅራቢ፡ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

02 January 2021, 12:20